እግዚአብሔር “ሰማይ ዙፋኔ ነው፣ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤የምትሠሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው? የማርፍበትስ ስፍራ ምንድር ነው?” (ኢሳይያስ 66፡1) ብሎ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ቢናገርም፣በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሰውን ልብ መቅደሱ ሊያደርግ እንደ መረጠ በተለያዩ ቦታዎች ተናግሯል፡፡ለምሳሌ ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህንኑ ቃል ጠቅሶ “ሰማይ ዙፋኔ ነው ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ለእኔ ምን ዓይነት ቤት ትሠራላችሁ? ይላል ጌታ፣ወይስ የማርፍበት ስፍራ ምንድር ነው? ይህንስ ሁሉ እጄ የሠራችው አይደለምን? እንዳለ፣ልዑል የሰው እጅ በሠራችው አይኖርም” (ሐዋ.ሥራ 7፡48-50፣አጽንዖት የእኔ) ብሎ ተናግሯል፡፡
“ልዑል የሰው እጅ በሠራችው ያለ መኖሩና” የሰው ልብን ለመቅደስነቱ መፈለጉ አስደናቂ የአዲስ ኪዳን ምስጢር ሲሆን፣ለብዙዎች ይህንን ከልብ መረዳቱ ከባድ እንደ ሆነ እገምታለሁ፡፡ነገር ግን እኔ ዘወትር ሳስበው የሚገርመኝ፣በቃላት ከምንገልጸው በላይ ግዙፍ የሆነ አምላክ በአንድ እጅግ ትንሽ በሆነ ሰው ውስጥ መኖሩ ነው፡፡በፍጹም አይገባም፡፡ስለዚህ ነገር የእግዚአብሔር ቃል ሲናገር እንዲህ ይላል፡-
“ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁ በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን?” (1 ቆሮንቶስ 6፡20)
ጌታችንን እንደ ግል አዳኛችን ከተቀበልንበት ሰዓት አንስቶ፣ክርስቶስ በውስጣችን ይኖራል፡፡ይህንን አጥብቆ መረዳት ለክርስትና ሕይወታችን እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ተመሳሳይ ሐሳብ ያላቸውን ምንባቦች ለአብነት መጥቀሱ ተገቢ ነውና እነሆ፡-
“ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ ቢሆን፣ሰውነታችሁ በኃጢአት ምክንያት የሞተ ነው” (ሮሜ 8፡10)
“ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ፤እኔም ሕያው ሆኜ አልኖርም፣ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል”(ገላትያ 2፡20)
“ክርስቶስ ሁሉ ነው፣በሁሉም ነው” (ቆላስይስ 3፡11)
ክርስቶስ በአማኝ ውስጥ የመኖሩ ምስጢር፣በግሌ የክርስትና ሕይወቴን በኃይል የቀየረ መረዳት መሆኑን ልገልጽ እወዳለሁ፡፡መንፈሳዊ ሕይወቴ በሚገባ ባልቆመበት ሰዓት፣አንድ መጽሐፍ እጄ ላይ ወደቀ፡፡መጽሐፉም “የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእኛ ውስጥ የመኖሩን” (ቆላ 1፡27) የአዲስ ኪዳን ምስጢር በሚገርም ሁኔታ ያብራራል፡፡በመጽሐፉ ላይ ያለው መልዕክት ሲበራልኝ፣የተደሰትሁት ደስታ እጅግ ከፍ ያለ ነበር፡፡ሐሳቡም የሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣አንዲህ ይላል፡-
“ስለ እናንተ እንደ ተሰጠኝ እንደ እግዚአብሔር መጋቢነት፣የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽሜ እንድሰብክ እኔ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆንሁ።ይህም ቃል ከዘላለምና ከትውልዶች ጀምሮ ተሰውሮ የነበረ ምሥጢር ነው፣አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጦአል። ለእነርሱም እግዚአብሔር በአሕዛብ ዘንድ ያለው የዚህ ምሥጢር ክብር ባለ ጠግነት ምን እንደ ሆነ ሊያስታውቅ ወደደ፣ምሥጢሩም የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእናንተ ዘንድ መሆኑ ነው(Christ in you the hope of glory)።” (ቈላስይስ 1: 25-27፣አጽንዖትና ጭማሪው የእኔ)
ክርስቶስ በውስጣችን እንዳለ መረዳቱ፣ለራሳችን የምንሰጠውን ዋጋ፣ከጌታ ጋር ያለንን ሕብረት እና ከማኀበረሰቡ ጋር ያለንን ግንኙነት በእጅጉ ይቀይረዋል፡፡ስለዚህ ይህንን ሐሳብ ደጋግሞ ማሰላሰሉ እጅግ ይመከራል፡፡ለዚህ ነው ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ለነበረችው ቤተ ክርስትያን ምዕመን ከጸለየላቸው ጸሎት አንዱ “ክርስቶስም በልባቸው በእምነት እንዲኖር” (ኤፌሶን 3፡16) የሚል ነበር፡፡
እስቲ አስቡት፣አንድ አማኝ ክርስቶስ በልቡ በእምነት እንደሚኖር አጥብቆ ከተረዳ፣እንዴት ተራን ነገር ማሰብ ይችላል? እንዴት ተራ ሰፈርስ ይገኛል?
No comments:
Post a Comment