የዕረፍት ምስጢር
ሰው ሲፈጠር ነፍሱ በሰዋዊ፣ምድራዊና ሥጋዊ በሆነ ነገር እንዳትጠግብ ተደርጋ የተሠራች ይመስላል፡፡ለሰው የፈለጋችሁትን ገንዘብ፣ልብስ፣ክብርና ዝና ስጡት፣ካለው ነገር ላይ ትንሽ መጨመር ይሻል፡፡ሮክፌለር “ሰው ምን ያህል ገንዘብ ቢኖረው ይረካል?” ተብሎ ተጠይቆ ነበር ይባላል፡፡እሱም “ካለው ጥቂት ቢጨምር ” ብሎ መልሷል አሉ፡፡ንጉሥ ሰለሞን “የሰው ድካም ሁሉ ለአፉ ነው፣ነፍሱ ግን አትጠግብም” (መክብብ 6፡7) ያለውም ለዚህ ነው፡፡አዎ! ነፍስ ከፈጣሪዋ ሳትገናኝና መንፈሱ ሳያገኛት እንኳን ጥጋብና እፎይ ማለትስ እንዴት ይታሰባል?
ሥጋዊና ምድራዊ ነገር ነፍስን እንደማያረካ ለመግለጽ፣ተዘውትሮ የሚባል አባባል አለ፡፡ልጥቀሰው፡-
“ሥጋዊ ነገር ሥጋን ይነካል
የአእምሮ ነገር አእምሮን ይነካል
የመንፈስ ነገር መንፈስን ይነካል”
አዎ!የሰው ልጅ የሦስት ነገር ሕብር (ሥጋ፣ነፍስና መንፈስ) መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ለዚህም ነው ሰው የውስጥ ማንነቱን ዘልቆ ወይም ከመንፈሱ ደርሶ ሊነካውና ሊያረካው የሚችልን ነገር ለማግኘት ብዙ ነገር የሚሞክረው፡፡ቢሆንም የሚያደርጋቸው ነገሮች ነፍሱ ድረስ ይደርሱ እንደ ሆነ ነው እንጂ፣በመንፈሱ ላይ ያለውን ባዶነት በፍጹም አይሞሉለትም፡፡ለዚህ ነው የአይሁዶች የዳስ በዓል ማብቂያ ላይ፣በተለያዩ ግብዣዎች ሲንበሸበሽ ለከረመ ሕዝብ፣ኢየሱስ እንዲህ ብሎ አስደናቂ ግብዣ ያቀረበው፡-
“ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣ፣መጽሐፍ እንዳለ የሕይወት ውኃ ምንጭ ከሆዱ ይፈልቃል” ( ዮሐንስ 7፡37)
ይገርማል! እንደ ጉድ ሲበላና ሲጠጣ የከረመን ሕዝብ፣ “ማንም የተጠማ ቢኖር ” እንዴት ይባላል ? እየጠጡ ጥማት አለ እንዴ ?
በግሌ ምድራዊ ነገር እንደማያጠግብና እንደማያረካ በሚዳሰስ መልኩ አይቼዋለሁ፡፡ርካታ፣ዕረፍትና እፎይታ የማገኝ መስሎኝ ጫቱን፣መጠጡን፣ፊልሙን፣ወሬውን ምኑ ቅጡ…ያልቧጠጥኩት ነገር የለም፡፡ምን ያልነካሁት ነገር ነበረ? አሁን ምሕረቱ በዝቶልኝና አንዱም እንደማያረካ ገብቶኝ ባምላኬ ተረጋግቼአለሁ፡፡በሚገርም አገላለጽ፣የእግዚአብሔር ቃልም በግልጽ እንዲህ ብሎ ተናግሯል፡-
“እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ ወደ ውኃ ኑ፤ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ ብሉም፤ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ግዙ።ገንዘብን እንጀራ ላይደለ፥ የድካማችሁንም ዋጋ ለማያጠግብ ነገር ለምን ትመዝናላችሁ? አድምጡኝ፣በረከትንም ብሉ፣ሰውነታችሁም በጮማ ደስ ይበለው። ጆሮአችሁን አዘንብሉ ወደ እኔም ቅረቡ፤ ስሙ ሰውነታችሁም በሕይወት ትኖራለች” (ኢሳይያስ 55፡1-3 አጽንዖት የኔ)
ዛሬም እያንዳንዳንችንን የእግዚአብሔር መንፈስ እንዲህ ብሎ ይጠይቀናል፡- “የድካማችሁን ዋጋ ለማያጠግብ ነገር ለምን ትመዝናላችሁ?” (ክርስትያኖችንም ጨምሮ)
ይህ እስኪገባንና ዓይኖቻችን እስኪከፈቱ ድረስ፣ብዙ የነፍስ መዳከር አለ፤ብዙ ማውጣትና ማውረድ አለ፤ብዙ ዘዴዎችን መዘየድም ይኖራል፡፡ብዙ መታለልና መሳትም እንደ ልብ ነው፡፡ብዙ የከበሩ የሚመስሉ ነገሮችን መሞከርና መቀያየር እንደ ብልሃት ተቆጥሮ፣ገንዘብን፣ኃይልንና ጊዜን መጨረስም ይኖራል፡፡ትልቁ እውነታ ግን ይህ ነው፡፡ሰው ወደ ነፍሱ እረኛና ጠባቂ በትሕትና መጥቶ እራሱን ካላስረከበ በስተቀር እፎይታ የለም፤እረፍት የለም፡፡ሁከት ብቻ እንጂ!
የሰው ልጅ እጅ ወደ ላይ ብሎ ከአምላኩ ጋር ሲስማማና አብሮ ለመሄድ ሲወስን፣የሚያገኘው መንፈሳዊ ሕክምና እጅግ ነፍስን የሚያሳርፍና የሚያጠግብ ይሆናል፤እጅግ የሚያረካና የተወጠረውን ውስጣችንን የሚያረግብና ዘና ብለን እንድንኖር የሚያደርግ ይሆናል፡፡እንዲህ ብሎ እንደ ተጻፈ ፡-
“እናንተ ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፣እኔም አሳርፋችኋለሁ፡፡ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ፣ከኔም ተማሩ፤ለነፍሳችሁም እረፍትን ታገኛላችሁ” (ማቴዎስ 11፡28)
በቀለ በላቸው(ዶ/ር)
240-330-5004
No comments:
Post a Comment