Saturday, January 10, 2015

ለመንገዱ ፍለጋ የለውም

                                  

ለመንገዱ ፍለጋ የለውም

የእግዚአብሔር ሥራ እጅግ ረቂቅ ነው፤“አወቅነው በቃ” ተብሎ አይደመደምም፤ምክንያቱም ሥራውን ሁሉ የሚሠራውን ከምናስበው በላይ ከፍ ባለ ጥበብ ነውና ነው፡፡ስለዚህ ነው በሁሉን ቻይነቱና አዋቂነቱ ታምነን መሠማራት የሚያስፈልገን፡፡ቃሉ ይህንን ሐሳብ ያስረግጥልናል፡-“በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል” (ምሳሌ 3፡5-6) “በራስህ ማስተዋል አትደገፍ” ሲል ነፋስንና ደመናን አትመልከት ማለቱ ነው፡፡ሁኔታዎችን አትይ ማለቱ ነው፡፡በራስህ አተያይ አትሂድ ማለቱ ነው፤ነፋስንና ደመናን የሚመለከት፣እንደማያጭድም ተጽፏልና(መክብብ 11፡4)!

አዎ! የእግዚአብሔር አሠራር እጅግ ጥልቅ ነው፤ለሰው ብዙ አይገባም፡፡እግዚአብሔር እንዲህ ነው የሚሠራው ብሎ መቀመርና መወሰን አይቻልም፡፡እሱ ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፡፡አካሄዱና አቀነባበሩ በጭራሽ አይለመድም፡፡ነቢዩ ሚልክያስ የምትፈልጉት ጌታ ባሰባችሁበት ሰዓት ወደ መቅደሱ ይመጣል አይደለም ብሎ የተናገረው፤የምትፈልጉት ጌታ በድንገት ወደ መቅደሱ ይመጣል(ሚልክያስ 31) ብሎ ነው፤የሰው ጣልቃ ገብነት እንደሌለበት፣በራሱ ሉዓላዊነትና ጊዜ ነገሮችን እንደሚፈጽም ሲያሳይ!

ሐዋርያው ጳውሎስ የሰው ልጅ ውድቀት፣በክርስቶስ የተፈጸመው ቤዛነት፣የአሕዛብ የዚህ ድግስ ተካፋይ መሆን፣የወንጌል ሰዎችን የማዳን ኃይል ወዘተ አስገርሞትና የእግዚአብሔር አሠራር ጥልቅ መሆኑን አስተውሎ፣እናም ከሚጽፈው ረጅም መልዕክት አቋርጦ እንዲህ ብሎ ነበር አድናቆቱን የገለጸው፡-“የእግዚአብሔር ባለጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፤ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፤ለመንገዱ ፍለጋ የለውም”(ሮሜ 11፡33) “ለመንገዱ ፍለጋ የለውም”  የሚለውን የእንግሊዝኛው አምፕሊፋይድ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ነው የሚገልጸው፡- “How untraceable are His ways(methods,paths)መንገዱ ወይም አሠራሩ እንዴት ምስጢራዊ ነው?በቃ አገኘነው የማይባል” 

አሠራሩ ግራ ይገባል፣ያስደንቃልም፡፡ዘገየ ሲሉት አይዘገይም፡፡ነገርን በራሱ ጊዜ ውብና ድንቅ አድርጐ መከወን ያውቅበታል፡፡ያበቃለት የሚመስልን ነገር በራሱ ጊዜ ውብ አድርጐ መለወጥ ይችልበታል፡፡በእኔም ሆነ በምቀርባቸው ሰዎች ሕይወትያለቁና አበቃላቸው የተባሉ ነገሮችን ነፍስ ሲዘራላቸው ደጋግሜ ዐይቼ ተገርሜአለሁ፡፡ሞቱ የተባሉ በርከት ያሉ ሁኔታዎች አንሰራርተው፣በሕይወት ለመዋጣቸው ሕያው ምስክር ነኝ፡፡እንዴት አገጣጥሞ ሠራው የሚለው እስኪያስደንቀኝ ድረስ፣እጄን በአፌ ላይ ጭኜ አውቃለሁ፡፡ለዚህ  ነው ኢዮብ እነሆ፣እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤እኛም አናውቀውም (ኢዮብ 3626) ብሎ የተናገረው፤አስቦ አውርዶና አሰላስሎ ነገሩ ሁሉ ከትንሽ አእምሮው ቢገዝፍበት!

እርግጥ ነው፣ሁሉን የሚሠራውን የአምላክ ሥራ አናውቅም፡፡ብዙ መመራመርም ልብን ያደክማል፡፡ታዲያ እግዚአብሔርን በዚህ መልኩ ከገለጽነው፣የእኛ ድርሻ መሆን ያለበት የሚለው ላይ ነው መነጋገር ያለብን፡፡በግሌ የእኛ ድርሻ መሆን ያለበት፣ሁሉን አዋቂነቱንና ቻይነቱን አምነንና የራሳችን ፍልስፍናና አስተሳሰብ ሳይማርከን፣ ቃሉን ተደግፈን መቆም ነው፡፡ዙሪያችን ያለው ሁኔታ ባይመሰክርም፣ጥበቡና አሠራሩ ከፍ ያለ እንደ ሆነ አምነን ራሳችንንን በሱ ላይ መጣል ነው፡፡ለአሠራሩ ለመመቸትም በብዙ ትሕትና ልባችንን በጸሎት መክፈት ነው፡፡ለዚህ ነው ንጉሡ ዳዊትእናንተ መኳንንቶች በሮችን ክፈቱ፣የዘላለም በሮች ይከፈቱ፤የክብርም ንጉሥ ይግባ፡፡ይህ የክብር ንጉሥ ማን ነው?እግዚአብሔር ነው ብርቱና ኃያል፤እግዚአብሔር ነው በሰልፍ ኃያል (መዝሙር 247-8) ያለው፡፡እስቲ ለሰከንድ አስቡት፤እጅግ አስደናቂው ነገር  ይኼ እኮ ነው፡-ብርቱና ኃያል ሆኖ ሳለ በታላቅ ትሕትና ልባችሁን ክፈቱልኝ ብሎ መለመኑ…. ይገርማል!!!

የነገሬ መደምደሚያ ይኼ ነው፡፡ችሎታችን እጅግ ውሱን ነውና፣እንዴት ነገሮች እንደሚሠራና እንደሚያቀናጅ ዝርዝሩን አናውቅምና፣ለአሠራሩ እንድንመች እንመነው፣በሁሉን ቻይነቱ እንደገፍ፣ቢያመንም የራሳችን አካሄዶች እንተው! እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፡-“የነፋስ መንገድ እንዴት እንደ ሆነች፣አጥንትም በእርጉዝ ሆድ እንዴት እንድትዋደድ እንደማታውቅ፣እንዲሁም ሁሉን የሚሠራውን ሥራ አታውቅም” (መክብብ 11፡4-5)!!
ቸር እንሰንብት !




No comments:

Post a Comment