ከክቡር ዕንቁ ይልቅ ይወደዳል
በመጽሐፍ ቅዱሳችን የእግዚአብሔር ቃል በወተት፣በእንጀራ፣በማር እና በጮማ ተመስሎ እናገዋኛለን፡፡አዎ! ለጣፋጭነቱ ወደር የለውም፡፡የነፍስ ምግብ ነው፡፡ሕይወትን ያስውባል፡፡ተስፋ የቆረጠችን ነፍስ ያለመልማል፡፡ውስጥን በብርሃን ይሞላል፡፡ልብን በደስታ ያሞቃል ወዘተበበኩሌ ወደ ጌታ የመጣሁት ከድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ነው፡፡ወደ እሱ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከመጣሁ በኋላ፣የእግዚአብሔር ቃል ሕይወቴን እንዴት እንዳስተካከለውና ቅርጽ እንዳስያዘው በቃላት መግለጽ ያቅተኛል፡፡ቃሉ “የጻድቃን መንገድ ቅን ናት፡፡አንተ ቅን ነህ፣የጻድቃንን መንገድ ታቀናለህ”(ኢሳይያስ 26፡7)እንደሚል፣የተወላገደ አስተሳሰቤን፣የተጣመመ ዕይታዬንና ያልተስተካከለ የሕይወት ምልልሴን ጠርቦና አርሞ፣ሰው አድርጐኛል፤ገና እጅግ ብዙ የሚቀረኝ ነገር ቢኖርም፡፡
ንጉሥ ዳዊት ለእግዚአብሔር ቃል ያለውን ፍቅር ሲገልጽ፣ “እጅግ በወደድኳቸው በትእዛዝህ ደስ ይለኛል” (መዝሙር 119፡47) ይላል፡፡ቋንቋ ያጠረው አይመስልም? እርግጥ ነው ስለ እግዚአብሔር ቃል ጣፋጭነትና ግሩምነት ለመግለጽ ቃላት ያጥራል፣ያንሳልም፡፡ዳዊት በሌላ ቦታ ስለ ቃሉ ውድነትና ውብነት ሲናገር “ከወርቅና ከክቡር ዕንቁ ይልቅ ይወደዳል፤ከማርና ከማር ወለላም ይጣፍጣል”(መዝሙር 19፡11) ይላል፡፡ “ከክቡር ዕንቁ ይልቅ ይወደዳል” የሚለውን አስምሩልኝ፡፡ለዚህ ነው ውድነቱ እንዲታየን፣በኃይል መጮህና መጸለይ የሚያስፈልገን፡፡አለበለዚያ ግን የሚገባውን ክብርና ትኩረት ላንሰጠው እንችላለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ዳዊት በሌላም ቦታ “ምስክርችህ ድንቆች ናቸው፣ስለዚህ ነፍሴ ፈለገቻቸው”(መዝሙር 119፡129) በማለት ከቃሉ ጋር ያለውን ቁርኝት፣ፍቅርና ትስስር ይገልጻል፡፡በግሌ ሁልጊዜ መዝሙር ዳዊት ምዕራፍ 119 ላይ ደርሼ ንጉሥ ዳዊት ለቃሉ ያለውን ከበሬታ፣ፍቅርና ራብ ሳይ “እንዴት መታደል ነው?” እላለሁ፡፡ለቃሉም የሚገባውን ክብር እንድሰጥ “እባክህ ጌታ ሆይ ዓይኖቼን ክፈት” ብዬ እጸልያለሁ፡፡
የእግዚአብሔር ቃል ሕይወትን በመለወጥ ረገድ ወደር የለውም፡፡ወደ ግድያ የሚገሠግሥን ልብ ይለውጣል፡፡በቂም የተሞላን ሕይወት ያሳርፋል፡፡ከክፋት ያስጥላል፡፡ስስትን በለጋስነት ይለውጣል፡፡ጥላቻን በፍቅር ይቀይራል፡፡ቸልተኛን በትጋት ይሞላል፡፡ኀዘንተኛንና ቆዛሚን በዝማሬና በሐሤት ያዘልላል፡፡የተከፈተና በትሕትና የቀረበ ልብ ያግኝ እንጂ፣ኧረ ምን የማያደርገው ነገር አለ?
No comments:
Post a Comment