Saturday, January 3, 2015

ቅርብነቱ





ቅርብነቱ

ጌታ ቅርብ ነው (ፊሊጵስዩስ 26) የሚለውን ቃል ዕውነታነትና ተጨባጭነት ለማረጋገጥ መንገዱ ቀላል ነው፡፡መጽሐፍ ቅዱሳችንን በሰከነ ሁኔታና በትሕትና ስናነበው፣ወደ ውስጣችን የሚነፍሰው ደስታና ሰላም በሚገባ ያረጋግጥልናል፡፡በተጨማሪም አንዳንዴ ነፍስን ከሚታገሉ የኑሮ ሐሳቦችና ውጣ ውረዶች የተነሣ ባዶነት ተሰምቶን ግራ ይገባናል፡፡ያኔ በነፍስ መታገሉን አቁመንና ድንገት ሁሉን ትተን በጸጋው ዙፋኑ ፊት በርከክ ብለን፣መንፈሱ ሲያረጋጋንና ተቃራኒ የሆነና በረከት የሞላበት ዓለም ውስጥ ሲከተን፣በመደነቅ ማንም ሊሰጠን የማይችለውን ሕክምና በሰከንድ ውስጥ ስናገኝ ቅርብነቱ ይበራልናል፡፡ለዚህም ነው ሐዋርያው ጴጥሮስ እርሱንም ሳታዩት ትወዱታላችሁ፤አሁንም ምንም ባታዩት በእርሱ አምናችሁ፣የእምነታችሁን ፍጻሜ እርሱም የነፍሳችሁን መዳን እየተቀበላችሁ ፣በማይነገር ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ይላችኋል (1ጴጥሮስ 18-9)ብሎ የተናገረው፡፡

አዎ ምንም እንኳ በአካል ባናየውም፣ አሠራሩን መንፈሳዊ ዓይናችን በርቶ ስናየውና ውስጣዊ ለውጡ ልባችንን ሲያሞቀን፣ከመደነቅ ሌላ ምንም ቋንቋ አይኖረንም፤ስግደት እንጂ! ክብር በሞላበት ሐሤት ዝማሬ እንጂ! እነዚህ የውስጥ ምስክርነቶች ሲበዙልን ነው፣እየተሳብን፣ሕብረታችን እየጠለቀና ሌሎች ነገሮች እያነሱብን የሚመጡት፡፡ንጉሥ ዳዊት ባንድ ቦታ  ጌታ ለነፍሴ ደጋፊዋ ነው ያለውም ለዚህ ነው፤በኑሮ ውስብስብ ውስጥ ሲያረጋጋው ስላየ!ከረግረግ ጭቃ ውስጥ ሲያወጣው ስላየ! ከብዙ ሞቶች ሲያስመልጠው ስላየ!

ወገኖቼ ቅርብነቱ አስደናቂ ነው፡፡ለእኛ የራቀ ቢመስልም፣በፍጹም ሊዘገይ በማይችልበት ሁኔታ ለያንዳንዳችን ቅርብ ነው፡፡በሱ ፊት ረፈደ የሚባል ነገር የለም፡፡በግሌ ለክብሩ መገለጫነት ይሆን ዘንድ፣የሞተ ነገርም ሕያው ሲሆን አይቻለሁ፡፡አለቀ በተባለ ነገር ውስጥ ሰበር ሰሚ ሆኖ ሲገባ ደጋግሜ አይቻለሁ፡፡ የራቀኝና የተወኝ መስሎኝ ግራ ገብቶኝ ያውቃል፡፡አለቀልኝ ብዬም ደንብሬ አውቃለሁ፤ብዙ ጊዜ! ግን ቅርብ ነውና የደጋፊነት በረከቱንም በተግባር ነፍሴ ደጋግማ አይታለች፡፡ዘማሪው ዳንኤል በአገልግሎቱና በኑሮው ቅርብነቱንና ደጋፊነቱን በሚገባ ስላየ፣ይረዳል ይደግፋል፣ጉልበት ይሆናል ጌታ  ብሎ ዘምሯል፤ቸርነቱና ታማኝነቱ ጠልቆ ገብቶት!

አዎ! የጌታ ቅርብነትና ደራሽነት አስገራሚ ነው፡፡ድንቅ ነው፡፡ባልተጠበቀ መንገድ ሲደርስ፣ባላየነው ስሌትና ቀመር ቋጠሮአችንን ሲፈታ፣በመለኮታዊው ቅንብሩ ቅጥሩን ሲያዘልለን አይተን ነው ቤቱ የቀረነው፤እንደ ሰማን እንዲሁ አይተን (መዝሙር 488) ነው ተገርመን የተከተልነው፡፡ከወንድም አብልጦ የሚጠጋጋ ወዳጅ መሆኑን (ምሳሌ 1824) ቀምሰንና ተማርከን ነው በቤቱ ያለነው፤

እጅግ ቅርብ ነውና!አልተውህም አልለቅም ብሎናልና(ዕብራውያን 135) ስሙ ከዘላለም እስከ ዘላለም የተባረከ ይሁን!!








                                                                     

No comments:

Post a Comment