Saturday, January 31, 2015

ግሩም ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁ



January 31, 2015
ግሩም ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁ

ብዙ ሰዎች “ሳይንስና እምነት አብረው አይሄዱም፣አይስማሙም ” ተብሎ ሲነገር እሰማለሁ፡፡እኔ ግን ሳይንስና እምነት ይደጋገፋሉ ብዬ አስባለሁ፣አምናለሁም፡፡ሳይንስ የእግዚአብሔርን ሥራ በሚገባ ጎልቶ እንዲታይ ያደርጋል የሚልም አመለካከት አለኝ፡፡ዕውቁ ሳይንቲስት አልበርት አንስታይን “Science without religion is lame,religion without science is blind”/ “ሳይንስ ያለ እምነት አንካሳ ነው፤እምነት ያለ ሳይንስ እውር ነው” ብሏል፤ሳይንስና እምነት አብረው እንደሚሄዱና እንደሚደጋገፉ ለማሳየት!


የሕክምና ባለሙያ ስለሆንሁ ስለ ሰው አፈጣጠር፣የአካል ቅንብርና አሠራሮችን ለማጥናት ዕድለኛ ሆኛለሁ፡፡በነዚህ አጋጣሚዎች የሰው ልጅ እጅግ ከፍ ባለ ጥበብ እንደተፈጠረ ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡ከአእምሮ በላይ የሆነ እውቀት እንደሠራውና እንዳበጀው ምንም ጥርጥርም የለኝ፡፡ዘወትርም የሰውን አካላዊ ቅንጅትና አሠራር ሳስብ፣እግዚአብሔርን በነገሮቹ ውስጥ ስለማይ በምስጋናና በግርምት እሞላለሁ፡፡እጅግ የሚገርመው እያንዳንዱ በየቦታው የተሰካካው የአካል ክፍል በዓላማ የተሰካና ከሌላው ጋራ በሕብር ተስማምቶ የሚሠራው ሥራ መኖሩ ነው፡፡እነዚህን የላቁ አካላዊ ቅንብሮችና ቅንጅቶች ማሰላሰሌም ለአምነቴ መጠንከርና መነቃቃት ግሩም ምክንያት ሆኖኛል፡፡ብዙ ጊዜም ምስጋና ፈንቅሎኝ፣“ተመስገን የጥበብ ሁሉ አምላክ ተባረክ” እላለሁ፡፡እስቲ ሥራዎቹን በተናጠል ለአብነት ልዳስስ፡፡

የልብ ያለ ማቋረጥ መምታቱ፣ደም ከአንዱ የልብ ክፍል ወደ ሌላው ሂደቱን በጠበቀ መልኩ መፍሰሱ፣እያንዳንዱ የልብ ክፍል ክዳኖች በራሳቸው ጊዜ መከፈት መዘጋታቸው፣እናም ልብ ያለ ማቋረጥ እየሠራ አለ መድከሙ እጅግ ይገርመኛል፡፡


አንድ ሳይንቲስ “ኩላሊት እጅግ በጣም የረቀቀ የኬሚካል እንደስትሪ ነው” ብለው ተናግረዋል፡፡እስማማለሁ፡፡በሰውነታችን ውስጥ ባለው ሂደት ደም ውስጥ ያለው አብዛኛው ንጥረ ነገር ቆሻሻን ጨምሮ፣መጨረሻ ላይ የሚያልፈው በኩላሊት በኩል ነው፡፡ኩላሊት ደግሞ ለሰውነት የሚጠቅምና የማይጠቅመውን ለይቶ፣ የማይጠቅመውን ብቻ ያስወግዳል፡፡ሰውነታችንን የሚጠቅሙ ንጥረ ነገሮችና ኬሚካሎች፣ወደ ደም ተመልሰው ሰውነታቸንን ያገለግላሉ፡፡ይገርማል፡፡


ሌላ እጅግ የሚገርመኝ ነገር፣የማሰባችን ጥበብ ነው፡፡አንድ ሰው ስለ አንድ ጉዳይ ጠይቆን ለጊዜው ማስታወስ ባንችልም፣ከተጠየቅንበት ሰዓት ጀምሮ አእምሮአችን ያንን ጉዳይ ሊያስታውሰን በመፈለግ ይባትላል፡፡ከዚያም ያ ለማስታወስ የተቸገርነው ነገር ከሰዓታት ወይም ከቀናት በኋላ ትዝ ይለናል፡፡አእምሮ ከድብቅ ማሕደሩ (subconscious) ሲፈልግ ከርሟላ!


ሴት ልጅ ዘጠኝ ወር ማርገዟን እናውቃለን፡፡የሚደንቀው ነገር የሚከተለው ነው፡፡ሳይንቲስቶች ሴትየዋ ልክ የመውለጃዋ ጊዜ ሲደርስ፣ምጧ የሚጀመርምበትን መንስኤና ምክንያት እስከ አሁን ሊያውቁ አልቻሉም፡፡ሰዓቱን ጠብቆ ከች ማለቱ እጅግ ገራሚ ነውና፡፡ማህፀን ጊዜና ሰዓት የተገጠመለት ይመስል፣ምንም ሳያሳትት በትክክለኛው ጊዜ ልጁን ለማስወጣት መንቀሳቀስ ይጀምራል፡፡የምጥ አጀማመር ቅንብሩ፣እየጨመረ የሚሄደው የማህፀን አከፋፈት፣ማህፀን ከላይ ልጁን እየገፋ ጸንሱ እስኪወጣ ድረስ አለ ማቋረጡ ይገርማል፡፡ማህፀን ጽንሱን ካስወጣ በኋላ ወደ ቀድሞ ቦታው፣ቅርጹና መጠኑ መመለሱ ሌላው ገራሚ ነገር ነው፡፡ጸንሱ በማህፀን ሳለ የአመጋገብ ስርዓቱ፣በተመቸ ከባቢ ሳይጨናነቅ ተመችቶት በውኃ ላይ እየተንሳፈፈ ማደጉ እጅግ አስደናቂ ጥበብ ነው፡፡


በሰውነታችን ላይ የምግብ የማንሸራሸር ስርዓት ይገርመኛል፡፡ሰው በአፉ ጐርሶ ማኘክ የጀመረው ምግብ መድቀቅ የሚጀመረው እዛው አፉ ውስጥ ነው፡፡በተለያዩ ተፈጥሮአዊ ኬሚካሎች(ኢንዛይሞች) መሰባበርና መላም ቢጀምርም፣ብዙ ርቀት እየላመ ይጓዛል፡፡ጨጓራ ውስጥ አሲድ ባለው ከባቢ በማለፍ የበለጠ እየላመና እየተጨመቀ ይሄዳል፡፡በትንሹ አንጀትም ውስጥ እንዲሁ፡፡ብዙ ኬሚካላዊ ሂደቶች ውስጥ አልፎ፣እጅግ የላሙ፣ለሰውነታችን የሚጠቅሙ ነገሮች ሁሉ፣አንድም ሳይቀሩ ወደ ደማችንን ይገባሉ፡፡የማይጠቅመው ነገር በትልቁ አንጀታችን በኩል አልፎ ወደ ውጭ ይወጣል፡፡ይገርማል፡፡


ሳይንቲቶች የአእምሮአችንን ውስብስብ ተፈጠሮአዊ አሠራር፣ገና በሚገባ እንዳልተገነዘቡት በተለያዩ ጽሑፋቸው ላይ ይናገራሉ፡፡ባንዴ በጣም ውስብስብ ሥራን ከሚሠሩ ብዙ ኮምፒዩተሮች የበለጠ ልቀት አለው፡፡ከልጅነት እስከ ሽምግልና ያሉ ያወቅናቸውንና ያየናቸውን ክስቶቶች፣ታሪኮችን፣ቃሎች ወዘተ ማስታወስ ይችላል፡፡ባንዴ በርከት ያሉ ሥራዎችን የመሥራት ብቃት አለው፡፡እጆቻችን፣እግሮቻችን፣አይኖቻችንንና ጭንቅላታችን በሕብር እንዲንቀሳቀሱ ይመራል፣ያቀናጃልም፡፡እስቲ አስቡት አንድ መኪና የሚነዳ ሰው፣በውጭ ያሉ የሌሎች መኪናዎችን እንቅስቃሴ እያየ ይቆጣጠራል፡፡በእግሩ ደግሞ የነዳጅ መስጫና ፍሬኑን በእግሩ ይቆጣጠራል፡፡እግረ መንገዱን ሙዚቃ ወይም ዜና ከፍቶ እያዳመጠ ይሄዳል፡፡እጆቹ መሪ ይዘው የመኪናውን አቅጣጫ ይቆጣጠራሉ፡፡ይህንን ሁሉ በሕብር የሚያቀናጀው አእምሮ ነው፡፡ባንዴ ከስድስት በላይ ሥራዎች፡፡ይገርማል፡፡


ይህ ሁሉ የጠቀስሁት የጥበብ ሥራ ከላይ ፈጣሪና አቀናባሪ እንዳለ ይናገራል፡፡እንዲሁም ከፍ ያለ እጅና ጥበብ እንዳለ በሚገባ ይመሰክራል፡፡ለዚህ ነው ዳዊት ይህንን በመንፈስ አስተውሎ እንዲህ ያለው፡-

“አቤቱ፣አንተ ኵላሊቴን ፈጥረሃልና፣በእናቴም ሆድ ሰውረኸኛል። ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፣ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች። እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፣አካሌም በምድር ታች በተሠራ ጊዜ አጥንቶቼ ከአንተ አልተሰወሩም። ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ፤የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ”  (መዝመር 139፡13-16)

ዳዊት “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁ” ሲል ከላይ የጠቃቀስኳቸውን የሰው ልጅ ውስብስብ ተፈጥሮአዊ አሠራሮችን በመንፈሱ ተረድቶ እንደ ሆነ እገምታለሁ፡፡“ነፍሴም ታውቀዋለች” ብሎ የተናገረው አገላለጽ ያስደንቀኛል፤ውስጣዊ መረዳት እንደሚያስፈልገን ሲጠቁመን! እርግጥ ነው፣ይህን ለመረዳት የነፍስ እውቀት ይፈልጋል፡፡የዓይን ብርሃን ይፈልጋል፡፡


ሐዋርያው ጳውሎስም የእግዚአብሔር ጥበብ እጅግ አስደንቆት፣መልዕክቱን አቋርጦ፣እንዲህ ብሎ ውዳሴን አቅርቧል፡-
“የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፤ ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፥ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም። የጌታን ልብ ያወቀው ማን ነው? ወይስ አማካሪው ማን ነበር? ወይስ ብድራቱን ይመልስ ዘንድ ለእርሱ አስቀድሞ የሰጠው ማን ነው? ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነውና፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን። (ሮሜ 11፡33-36)


እግዚአብሔር ረድቶትና ዓይኑ ተከፍቶ ላስተዋለ፣የእግዚአብሔር የጥበብ ሥራ እጅግ አስገራሚ ነው፡፡አንድ ሽማግሌ  እንዳሉት “ልበ ብርሃን” መሆን ነው የሚያስፈልገው፡፡አዎ! የልቡናው ዓይን የበራለት ሰው፣እነዚህን የጥበብ ሥራዎች ዐይቶ፣ተገቢው የሆነውን ክብር ለአምላኩ ይሠጣል፡፡የምስጋና ሰው ይሆናል፡፡ሕይወቱ በአድናቆትና በመገረም ይሞላል፡፡ይህንን የጥበብ ጌታ ለማወቅ ከፍ ያለ ራብ ያድርበታል፡፡እናም ጌታውን በሚገባ እስኪያውቅና ነፍሱ በእውቀት እስትጥለቀለቅ ድረስ አይተኛም!
ጌታ ሆይ እንድናውቅህ እርዳን!!

መዝጊያ ጥቅስ ፡-
“ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፥ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል። 2 ቀን ለቀን ነገርን ታወጣለች፥ ሌሊትም ለሌሊት እውቀትን ትናገራለች።ነገር የለም መናገርም የለም፥ ድምፃቸውም አይሰማም።ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ፥ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ።” (መዝሙር 19፡1-4)



Saturday, January 24, 2015

ክርስቶስ በእኛ ውስጥ(Christ in Us)

ክርስቶስ በእኛ ውስጥ(Christ in Us)

እግዚአብሔርሰማይ ዙፋኔ ነው፣ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤የምትሠሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው? የማርፍበትስ ስፍራ ምንድር ነው?” (ኢሳይያስ 661) ብሎ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ቢናገርም፣በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሰውን ልብ መቅደሱ ሊያደርግ እንደ መረጠ በተለያዩ ቦታዎች ተናግሯል፡፡ለምሳሌ ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህንኑ ቃል ጠቅሶሰማይ ዙፋኔ ነው ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ለእኔ ምን ዓይነት ቤት ትሠራላችሁ? ይላል ጌታ፣ወይስ የማርፍበት ስፍራ ምንድር ነው? ይህንስ ሁሉ እጄ የሠራችው አይደለምን? እንዳለ፣ልዑል የሰው እጅ በሠራችው አይኖርም” (ሐዋ.ሥራ 748-50፣አጽንዖት የእኔ) ብሎ ተናግሯል፡፡

ልዑል የሰው እጅ በሠራችው ያለ መኖሩናየሰው ልብን ለመቅደስነቱ መፈለጉ አስደናቂ የአዲስ ኪዳን ምስጢር ሲሆን፣ለብዙዎች ይህንን ከልብ መረዳቱ ከባድ እንደ ሆነ እገምታለሁ፡፡ነገር ግን እኔ ዘወትር ሳስበው የሚገርመኝ፣በቃላት ከምንገልጸው በላይ ግዙፍ የሆነ አምላክ በአንድ እጅግ ትንሽ በሆነ ሰው ውስጥ መኖሩ ነው፡፡በፍጹም አይገባም፡፡ስለዚህ ነገር የእግዚአብሔር ቃል ሲናገር እንዲህ ይላል፡-

ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁ በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን?” (1 ቆሮንቶስ 620)

ጌታችንን እንደ ግል አዳኛችን ከተቀበልንበት ሰዓት አንስቶ፣ክርስቶስ በውስጣችን ይኖራል፡፡ይህንን አጥብቆ መረዳት ለክርስትና ሕይወታችን እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ተመሳሳይ ሐሳብ ያላቸውን ምንባቦች ለአብነት መጥቀሱ ተገቢ ነውና እነሆ፡-

ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ ቢሆን፣ሰውነታችሁ በኃጢአት ምክንያት የሞተ ነው” (ሮሜ 810)
ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ፤እኔም ሕያው ሆኜ አልኖርም፣ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል”(ገላትያ 220)
ክርስቶስ ሁሉ ነው፣በሁሉም ነው” (ቆላስይስ 311)

ክርስቶስ በአማኝ ውስጥ የመኖሩ ምስጢር፣በግሌ የክርስትና ሕይወቴን በኃይል የቀየረ መረዳት መሆኑን ልገልጽ እወዳለሁ፡፡መንፈሳዊ ሕይወቴ በሚገባ ባልቆመበት ሰዓት፣አንድ መጽሐፍ እጄ ላይ ወደቀ፡፡መጽሐፉምየክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእኛ ውስጥ የመኖሩን” (ቆላ 127) የአዲስ ኪዳን ምስጢር በሚገርም ሁኔታ ያብራራል፡፡በመጽሐፉ ላይ ያለው መልዕክት ሲበራልኝ፣የተደሰትሁት ደስታ እጅግ ከፍ ያለ ነበር፡፡ሐሳቡም የሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣አንዲህ ይላል፡-

ስለ እናንተ እንደ ተሰጠኝ እንደ እግዚአብሔር መጋቢነት፣የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽሜ እንድሰብክ እኔ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆንሁ።ይህም ቃል ከዘላለምና ከትውልዶች ጀምሮ ተሰውሮ የነበረ ምሥጢር ነው፣አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጦአል። ለእነርሱም እግዚአብሔር በአሕዛብ ዘንድ ያለው የዚህ ምሥጢር ክብር ባለ ጠግነት ምን እንደ ሆነ ሊያስታውቅ ወደደ፣ምሥጢሩም የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእናንተ ዘንድ መሆኑ ነው(Christ in you the hope of glory)” (ቈላስይስ 1: 25-27፣አጽንዖትና ጭማሪው የእኔ)

ክርስቶስ በውስጣችን እንዳለ መረዳቱ፣ለራሳችን የምንሰጠውን ዋጋ፣ከጌታ ጋር ያለንን ሕብረት እና ከማኀበረሰቡ ጋር ያለንን ግንኙነት በእጅጉ ይቀይረዋል፡፡ስለዚህ ይህንን ሐሳብ ደጋግሞ ማሰላሰሉ እጅግ ይመከራል፡፡ለዚህ ነው ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ለነበረችው ቤተ ክርስትያን ምዕመን ከጸለየላቸው ጸሎት አንዱክርስቶስም በልባቸው በእምነት እንዲኖር” (ኤፌሶን 316) የሚል ነበር፡፡

እስቲ አስቡት፣አንድ አማኝ ክርስቶስ በልቡ በእምነት እንደሚኖር አጥብቆ ከተረዳ፣እንዴት ተራን ነገር ማሰብ ይችላል? እንዴት ተራ ሰፈርስ ይገኛል?