ጉልበቴን ይያዝ
ለጸሎት የሚያነሳሳኝና በልቤ ላይ በማይረሳ መልኩ ታትሞ የሚገኝ ቃል ኢሳይያስ 27፡5-6 ነው፡፡ብዙ ጊዜ ደጋግሜ ስላጠናሁትም፣ለነፍሴ መልሕቅ ሆኗል ማለት እችላለሁ፡፡እጅግ በጣም ግሩም ቃል ነውና እርሱን ላስቀድም፡፡እንዲህ ይነበባል፡-
ወይም ጕልበቴን ይያዝ፣ከእኔ ጋር ሰላም ያድርግ፤ ከእኔ ጋር ሰላም ያድርግ።በሚመጣው ዘመን ያዕቆብ ሥር ይሰድዳል፣ እስራኤልም ያብባል ይጨበጭብማል፤ በፍሬያቸውም የዓለሙን ፊት ይሞላሉ። (ኢሳይያስ 27፡5-6)
“ጉልበቴን
ይያዝ” የሚለው ቃል በሌሎች መጽሐፍ ቅዱሶች ላይ “መሸሸጊያው
ያድርገኝ” የሚል ትርጉምን ይዟል፡፡ “ጉልበቴን ይያዝ ከእኔም ጋር ሰላም ያድርግ” የሚለው ሐሳብ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ሕብረትና ቁርኝት ከሰላማችን ጋር የተያያዘ መሆኑን ያሳየናል፡፡አዎ! የጌታን ጉልበት በጸሎት በያዝን ቁጥር ሰላማችን እየበዛ፣እየተረጋጋን እና በመንፈሳዊ ሕይወታችን እየተለወጥን መምጣታችን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ይህንን ለ 16 ዓመት በተግባር ዳስሼ አይቼዋለሁ፡፡ኢየሱስ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣እኔም አሳርፋችኋለሁ”(ማቴዎስ 11፡28) ያለንም ለዚህ ነው፤ሌላ የሚያሳርፉ የሚመስሉ ነገሮች ከሽንገላ የዘለለ ዘለቄታዊ ዕረፍት እንደሌላቸው ሲያበስረን!
ከመቼውም ዘመን ይልቅ የእግዚአብሔርን ጉልበት በጸሎት መያዝ ያለበት ዘመን ቢኖር የአሁኑ ዘመን ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ለምን ቢባል የሰው ልጅ የክፋት መጠን በኃይል እየጨመረ ስለመጣ ነው፡፡ሰይጣን ከእያንዳንዱ ክፋት በስተጀርባ በታላቅ ቁጣ ምድሪቷን እያመሳት ስላለ ነው፡፡ይህ ሁኔታ ደግሞ በውጭ ባሉት በማያምኑ ሰዎች ሕይወት ብቻ ሳይሆን፣ጌታን እናውቃለን በሚሉት ላይ በገሃድና በብዛት ስለሚታይ ያለውን የክፋት መጠን በኃይል ያተልቀዋል፡፡በአሁኑ ሰዓት በክርስትያን ወገኖች መካከል፡፣ፍቅርና መዋደድ እጅግ ቀዝቅዟል፤ውሸት ነግሷል፤ግብዘኝነት ሰፍኗል፤ራስ ወዳድነት አግጦ ወጥቷል፤አለመተማመን በዝቷል ….ሌላም ሌላም(ዝርዝሩ ረጅም ነው)፡፡
ከዚህም የተነሣ የሰዎች ልብ ስብራት ከመጠን በላይ እየበዛ ነው፡፡እናም ያለንበትን ዘመን አስፈሪነት ቋንቋ የሚገልጸው አይመስለኝም፡፡ለዚህ ነው በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የነበሩትን የናሆም ዘመን ሰዎች የጌታ መንፈስ “የሚቀጠቅጥ ባንተ ላይ ወጥቷል፣ምሽግህን ጠብቅ፣መንገድህን ሰልል፣ወገብህን አጽና፣ኃይልህን እጅግ አበርታ” (ናሆም 2፡1) ብሎ የመከራቸው፡፡እጅግ ግሩም ምክር! “ኃይላችንን
እንዲበረታ” የምናደርግበት ዋነኛው መንገድ ደግሞ የጌታን ጉልበት በጸሎት ስንይዝ ነው፡፡ድምጹን ስንሰማ ነው፡፡የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ተዕለት ሲታደስ (2 ቆሮንቶስ 4፡16) ነው፡፡ከቃሉም ጋር ስንጣበቅ ነው፡፡
ከላይ
እንደጠቀስሁት “ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና” (ኤፌሶን 5፡16) የጌታን ጉልበት በጸሎት መያዝን ግድ ይለናል፡፡ታዲያ ጉልበቱን ይዘን ሙጭጭ ስንል፣ካልባረክኸኝ አልለቅህም ስንለውና ጥራት ያለው ጊዜን በፊቱ ስናሳልፍ፣መንፈሳችን ይጠነክራል፤አረማመዳችን ይጸናል፤እምነታችን ያድጋል፤በምናየው ነገር መሸበራችን ይወገዳል፤መረጋጋት የሕይወታችን መገለጫ ይሆናል፤የራእይ ሰዎች እንሆናለን፤ለብዙዎች በረከት እንሆናለን፡፡
በመግቢያ ላይ የተጠቀሰው ምንባብ ላይ ያለው የመጨረሻው አስደናቂም ፍሬ “በፍሬአቸውም የምድርን ፊት ይሞላሉ” የሚል ነው፡፡እጅግ በጣም አስደናቂ ውጤት ነው፡፡እጅግ የሚገርም ተፅዕኖ ነው፡፡ እስቲ ይህ ተግባራዊ ሆኖ ለሰከንድ በዐይነ ሕሊናችሁ ዕዩት፡፡ይህ ሲሆን የማይነካ የማሕበረሰብ መዋቅር የለም፡፡ይህ ሲሆን ብዙ ሰዎች ጉልበታቸውን ለጌታ ያንበረክካሉ፡፡ይህ ሲሆን ብዙ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ችግሮች ይወገዳሉ፡፡ከሁሉም በላይ እግዚአብሔር በመካከላችንም ሆነ በውጭ ባሉት ዘንድ በሚገባ ይከበራል፡፡
ባጭሩ
በምንባቡ ውስጥ አራት መንፈሳዊ እመርታዎችን በግልጽ እናያለን(ማሳሰቢያ፡-ጐበዝ አራቱም እመርታዎች የተያያዙ ናቸውና መዝለል አይቻልም)፡-
o
የእግዚአብሔርን ጉልበት በጸሎት መያዝ
o
ከሱ ጋር ለመሄድ መስማማት
o
ጤናማ መንፈሳዊ ዕድገት
o
የተትረፈረፉ መንፈሳዊ ፍሬዎች
በቃሉ
ውስጥ
ያለው
መንፈሳዊ ሂደት እጅግ ድንቅ ነው፡፡እንደተጠቀሰው እመርታዎቹ ተያያዥነት ያላቸው ስለሆኑ፣የእርሱን ጉልበት በመያዝ ጀምረን ወደ ፍሬ እንደምንመጣ ሊስተዋል ይገባል፡፡በፍጹም ሌላ አቋራጭና አማራጭ መንገድ እንደሌለ ሊታወቅ ይገባል፡፡እዚህ ጋ ነው ዋጋ የምንከፍለው፡፡እዚህ ጋ ነው ዲሲፕሊን የምንጠየቀው፡፡እዚህ ጋ ነው ትልቁ ትግል ያለው፡፡እዚህ ጋ ነው ተስማምቶ ለመሄድ መወሰኛው፡፡እዚህ ጋም ነው ብዙ ረብ የሌላቸውን ነገሮች ለመጣል የምንገደደው፡፡እዚህ ጋ ነው እንደ ሃና በመንፈስ የምንቃትተው፡፡እዚህ ጋ ነው እንደ ያዕቆብ እስኪነጋ ነገር የምንፋለመው፡፡ስለዚህ እዚህ ጋ የሚከፈለውን ዋጋ ሳናቅማማ ብንከፍል፣ከኪሳራና ከውድቀት እንጠበቃለን፡፡እናም እሱ በፍሬና በበረከት ተገልጦ ያስደንቀናልና ጉልበቱን በጸሎት እንያዝ!!
No comments:
Post a Comment