Tuesday, May 20, 2014
የጸሎት ሦስቱ ሂደቶች
የጸሎት ሦስቱ ሂደቶች
1. “ነፍሴ አንተን ተጠማች” (መዝሙር 63፡1)
2. “ነፍሴ በኋላህ ተከታተለች” (መዝሙር 63፡8)
3. “ነፍሴ በቅቤና በስብ እንደሚጠግቡ ትጠግባለች” (መዝሙር 63፡5)
ከላይ ያሉት ጥቅሶች ከመዝመረ ዳዊት ምዕራፍ 63 ላይ የተወሰዱ ሲሆን በከፊልም ቢሆን የጸሎትን ደረጃ ያሳያሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ ጸሎት ወደ ውስጠኛው የእግዚአብሔር ማደሪያ የሚደረግ ግሥገሣ እንደ ሆነ ‹‹አምላኬ አምላኬ ወደ አንተ እገሠግሣለሁ›› (መዝ 63፡1) የሚለው ቃል ያመለክተናል፡፡ጉዞ መነሻ እንዳለው ሁሉ ጸሎታችንም ከውጨኛው የጸሎት አደባባይ ወደ ውስጠኛው የጸሎት አደባባይ ያነጣጠረ ነው፡፡ለዚህም ነው ዳዊት ‹‹ኃይልህንና ክብርህን አይ ዘንድ እንዲሁ በመቅደስህ ውስጥ ተመለከትሁ››(መዝ 63፡2) ብሎ የሚናገረው፡፡
ከላይ የጠቀስኩትን ክፍል ስናነብ የምንገነዘበው ነገር አለ፡፡እሱም ጸሎታችን እየጠለቀ በሄደ ቁጥር፣የእግዚአብሔርን ኃይልህንና ክብር የማየት በረከታችን እየጨመረ እንደሚሄድ ነው፡፡ለዚህ ነው በግልብ (superficial) ጸሎት‹‹ነፍሴ በቅቤና በስብ እንደሚጠግቡ ትጠግባለች›› (መዝ 63፡5) ማለት የማንችለው፡፡
‹‹እገሠግሣለሁ›› (ቁ.1) ስንልም የጸሎት ርምጃችን ጽናት፣ትግዕስት፣ንቁነት ወዘተ እንደ ግብዓት እንደሚያስፈልጉት መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ብዙ ጊዜ ለጸሎት ስንደረደርና ለመገሥገሥ ስናስብ ‹‹ነፍሴ አንተን ተጠማች፤ሥጋዬ አንተን እንዴት ናፈቀች›› (መዝ 63፡1) የሚል መንፈስን ይዘን ነው የምንቀርበው፤በተጓዳኝ ተግዳሮቶቻችን እያሰብን፤ሕመማችን እያሰብን፤ፈተናዎቻችን እያሰብን፣መከራዎቻችን እያሰብን ወዘተ፡፡ባለፉት የጸሎት ጊዜያት የነበሩንን ግሩም ልምምዶች እያሰብንም አምላካችን አሁንም እንዲደግመው በመማጸን በፊቱ እንሆናለን፡፡
ጸሎትን ስንጀምር የመጸለይ ፍላጎታችን እጅግ ዝቅ ያለ ስለሚሆን፣ቶሎ እንድናቋርጥ ፈተናዎች ይመጣሉ፡፡ድካም ይጫጫነናል፤አእምሮአችን ይበታተናል ሌላም ሌላም፡፡ነገር ግን በጽናት ይህንን ተግዳሮት አሸንፈን ከዘለቅን፣የእግዚአብሔር ሕልውና የሚታወቀን ደረጃ ውስጥ እንገባለን፡፡በዚህ ደረጃ ላይ ሆነን ነው ‹‹ነፍሴ በኋላህ ተከታተለች››(መዝ 63፡8) የምንለው፡፡በዚህ ደረጃ ላይ ሆነን ነው‹‹ሳበን ካንተም በኋላ እንሮጣለን…..ከወይን ጠጅ ይልቅ ፍቅርህን እናስባለን››(መኃልይ 1፡4) የምንለው፡፡በዚህ ጊዜ ትንሽ ትንሽ ዝማሬና ምሥጋናም ያምረናል፤ጸሎታችንንም ሳናቋርጥ መቀጠል ያምረናል፡፡ቢሆንም ብዙ ሰዎች በሚገባ የጸለዩ ስለሚመስላቸው እዚህ ደረጃ ላይ ያቋርጣሉ፡፡እንዳውም ስለነበራቸው ድንቅ የጸሎት ጊዜም ለሰዎች ሊመሰክሩም ይችላሉ ብዬም አስባለሁ፡፡ይህንን ደረጃ ስናልፍ ሦስተኛው ደረጃ ውስጥ እንገባለን፡፡
ሦስተኛው የጸሎት ደረጃ፣ከጌታ ጋር እጅግ አስደናቂ ሕብረት የምናደርግበት የጸሎት ደረጃ ሲሆን፣እውነተኛ የሕይወት ለውጥ(transformation) ለማየት መልካም ዕድሎችን ይፈጥርልናል፡፡በዚህ የጸሎት ደረጃ አዘውትረን ስናሳልፍ ነው ‹‹ነፍሴ በቅቤና በስብ እንደሚጠግቡ ትጠግባለች፤ከንፈሮቼም ስምህን በደስታ ያመሰግናሉ››(መዝ 63፡5)ብለን በእውነት እና በድፍረት መናገር የምንችለው፡፡ይህ ደረጃ ‹‹መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት የሚማልድበት››(ሮሜ 8፡27) የጸሎት ደረጃ ነው፤እንደ እግዚአብሔር ፈቃድም የምንጸልይበት፡፡እንባ ቋንቋችን ይሆናል፡፡ይሄ ደረጃ ሲጠልቅ፣ዝምታ ይበዛል፡፡እውነተኛ ንሥሓ ከአንደበታችን ይወጣል፡፡የከረምንበትን መንፈሳዊ ሕይወት በመንፈስ ስለምናየው ከልብ እናዝናለን፡፡ከጌታ ጋር ያለ ግብዝነት ለመራመድ የምንወስንበት ጊዜም ይሆናል፡፡ይህ ዓይነት ጸሎት በሕይወታችን ሲበዛ ነው፣መንፈሳዊ ለውጦችና ፍሬዎች የሚበዙት፡፡
ጌታ ሆይ እባክህ ወደ ጠለቀ ጸሎት ሳበን!
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment