Thursday, May 8, 2014

ለዕረፍት ተጠርተናል





ለዕረፍት ተጠርተናል

ጌታ በተለያየ በሚገባን መንገድ “ዕረፍት” እንዲህ ነው ብሎ ያሳየናል፣ይጠቁመናል፣ያቀምሰናል፡፡ቢሆንም ሙሉ የሆነ ዕረፍት የሚመጣው፣በትጋት በፊቱ በመሆን የጌታ ጸጋ በሕይወታችን እየጨመረ ሲመጣ እንደ ሆነ ልብ ይሏል፡፡

በሕይወቴ አንዳንዴ በመባከን እከርምና በማስተዋል መለስ ብዬ፣ ከእሱ ጋር ግሩም የሆነ ሕብረት ሳደርግ የሚገርም ሰላም፣ደስታና መረጋጋት እንደ ወንዝ ውስጤ ሲፈስ እገረምና መልሼ በራሴ አዝናለሁ፡፡ያለመባከን በዚህ ዓይነት ትጋት ያለማቋረጥ ብቀጥል፣ ይህ ቅምሻ የዘወትር በረከቴ ይሆን ነበር ብዬም ራሴን እታዘባለሁ፡፡

ጌታችን የዕረፍት አምላክ ነውና ሊያሳርፈን ይፈልጋል፡፡ለእኛ ያለው ግልጽ የሆነው የልብ ሐሳቡም እንዲህ የሚል ነው፡-

እኔ ሕይወት እንዲሆንላችሁ እንዲበዛላችሁ መጣሁ” (ዮሐንስ 10፡10)

ነገር ግን የብዙዎቻችን አኗኗር ሲታይ የዚህን አስደናቂ የተስፋ ቃል ምንነትና በውስጡ የያዘውን በረከት በሚገባ የተረዳነው አይመስልም፡፡ዋናው ችግራችንም ልባችን ስቷል፡፡ልባችን መሳቱን የሚያረጋግጥልን ደግሞ በማያሳርፉ ነገሮች ለማረፍ ሲቧጥጥና ሲያልም ማደሩ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ስለ እስራኤላውያን የምድረ በዳ ሕይወት ሲናገር “ሁል ጊዜ ልባቸው ይስታል፤እነርሱም መንገዴን አላወቁም አልሁ፡፡ወደ ዕረፍቴም እንዳይገቡ በቁጣዬ ማልሁ” (መዝ 95 ፡10-11) ይላል፡፡አዎ ልባችን ስቷል እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? የጌታ መንፈስ በተለያየ መንገድ “ዕረፍት ይህች ናት የደከመውንም አሳርፉ ይህችም ማረፊያ ናት አላቸው እነርሱ መስማትን እንቢ አሉ” (ኢሳ 28፡12) እንደሚል ሆኖብናል፡፡

የእግዚአብሔር ቃል“ይሳኮር አጥንተ ብርቱ አህያ ነው፤በበጎች ጉረኖም መካከል ያርፋል፡፡ዕረፍትም መልካም መሆንዋን አየ” (ዘፍጥረት 49፡14-15) ይለናል፡፡የውስጣዊ ዕረፍት መልካምነት ምንም አያጠያይቅም፤በሁሉም መልኩ ይጠቅማል፡፡መንፈሳችን ከእግዚአብሔር ለመስማት ይመቻቻል፤የአእምሮአችንን የመሥራት እና የፈጠራ ችሎታ ይጨምረዋል፤የእግዚአብሔርን ሥራ በቅጡ እንድሠራ ያስችለናል፤ማኅበራዊ ሕይወታችንን እንዲስተካከል አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል፤ዕረፍቱ በራሱ ለሰዎች የሚታይ ጠንካራ መልዕክት ነው (በተለይ ለማያምኑ ሰዎች) ፡፡

ከጌታቸው የተማሩ እና ያረፉ ሰዎች ከሕይወት ምልልሳቸው ይታወቃሉ፡፡ሲቅበጠበጡና ሲባዝኑ አይታዩም፡፡እንዳውም ሕይወታቸው ከሩቅ ይናገራል፡፡በጌታቸው ያረፉ ሰዎች በቃሉ ጉልበት ውስጣቸው ስለተለወጠ ከማንኛውም ቀንበር ነጻ ናቸው፡፡ቅድሚያ የሚሰጡትን የሚያውቁ ሲሆን፣ምርጫዎቻቸውም ውሱን ይሆናሉ፡፡መረጋጋትና ሰላም የሚታይባቸው እና የምሥጋና ሕይወት ያላቸው(የማይነጫነጩ፣የማያጉረመርሙ) ስለሆነ፣የምድር ጨው ወይም የዓለም ብርሃን ናቸው፡፡ሰው እነርሱን አይቶ ልቡ ይነካል፡፡ሰው እነርሱን አይቶ የተለወጡበትን ምንጭ ያስተውላል፡፡ሰው እነርሱን አይቶ ወደ እዚህ ድንቅ የዕረፍት አምላክም ይመጣል፡፡

ስለዚህ ከመባከን ወጥተን በዕረፍት ለመመላለስ እና የዕረፍትን በረከቶች ለማፈስ ምን እናድርግ የሚለው ላይ ጥቂት ብዬ ጽሑፌን ልደምድም፡፡

ነጥብ አንድ ፡-በትጋት የጌታን ቃል እያሰላሰልንና እያጠናን ብሎም በጸጋው ዙፋን ፊት በቂ ጊዜን በጸሎት ስናሳልፍ፣ የጌታን ድምጽ ለመስማት ዕድል ይኖረናል፡፡እምነት ከመስማት (ሮሜ 10፡17) ስለሆነ፣የእግዚአብሔርን ድምፅ ስንሰማ ደግሞ እምነታችን በሚገባ ይጠነክራል፡፡ ቃሉ “የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል ከመከራም ሥጋት ያርፋል” (ምሳ 1፡33) ይላልና፣ ከመቅበዝበዝ፣ከመባከንና ከሥጋት እንድናለን፡፡
ነጥብ ሁለት፡-ጌታን በሚገባ ማወቃችንና የእሱ በሕይወታችን እየተገለጠ መሄዱ፣ዕረፍታችንን እየጨመረው ይሄዳል፡፡በማቴዎስ 11፡25-30 ያለው ክፍል ይህንን ሐሳብ በሚገባ ያብራራዋልና፣ነጥብ አንድ ላይ ያለውንም ሐሳብ ይደግፈዋልና ልጥቀሰው፡፡እንዲህ ይላል፡-
‹‹በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አለ። አባት ሆይ የሰማይና የምድር ጌታ፤ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ፤አዎን፤አባት ሆይ፤ ፈቃድህ በፊትህ እንዲህ ሆኖአልና።ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፤ከወልድም በቀር ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም።እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ።ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፤እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና››
ይህንን ቃል ብዙ ጊዜ ያነበብነው ቢሆንም፣በተግባር በሕይወታችን ያልተተረጐመ ቃል ነው ብዬ አምናለሁ፡፡የእርሱ ለእኛ መገለጥ እና የነፍሳችን ዕረፍት ማግኘት ትልቅ ትስስር እንዳለው ማየት ይቻላል፡፡ማለትም ወደ እርሱ የመቅረባችንና የመማራችን መጠን፣ለእኛ የመገለጡን መጠንና የዕረፍታችንን መጠን ይወስነዋል፡፡ለዚህ ነው “ከኔም ተማሩ ለነፍሳችሁ ዕረፍትን ታገኛላችሁ” ብሎ በትሕትና የሚጋብዘን፡፡ቃሉ “ለአሕዛብ የታወቀው ምሥጢር እንደ ተገለጠ መጠን ሊያበረታችሁ ለሚችለው” (ሮሜ 16፡26) የሚለውም ለዚህ ነው፤በተገለጠልን መጠን ዕረፍቱ እየበዛልን፣እየበረታን እንሄዳለንና፡፡ጌታ ሆይ፣የማሳረፍህን ብቃትና ችሎታ እንድናየው ዓይናችህን ግለጥልን!!

                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                               


                                                                                       

No comments:

Post a Comment