May 9, 2014
ቀላይ
ቀላይን ትጠራለች/Deep calls deep (መዝ 42፡7)ረዘም ያለ ጸሎትን ስናስብ ምንም ብዙ ጊዜ በስጋ ብንጀምርም በመንፈስ እንደምንጨርስ ልናምን ይገባናል፡፡በጽኑነት እንደ ጌታ መንፈስ ምሪት ከቀጠልን በጸሎታችንም ድንቅ ነገሮችን እንደምናይ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡እዚህ ላይ ሊታሰብ የሚገባው ነገር፣ቶሎ እንድናቋርጥ እና ወደ ሌሎች ጉዳዮች እንድንሄድ ወደ ነፍሳችን ግብዣዎች ይመጣሉ፡፡ እነዚህን መንፈስን የማያረጋጉ መልእክቶች ወደ ጎን በማድረግና ጸሎታችን ላይ በሚገባ ትኩረት በማድረግ ብንገሠግሥ የጉትጐታው አስቸጋሪነት እየቀለለ መንፈሳችንና አእምሮአችን እየተወረሰ ወደ ድንቅ ሁኔታ ውስጥ እንገባለን፡፡“Start is always difficult” የሚባለውም እውነትነት ያለው ለዚህ ነው፡፡
ስለ ጸሎት ጥሩ ግንዛቤ ያላቸው ሰዎች ጸሎት ከሶስት በላይ እርከኖች (dimensions)እንዳሉት ይናገራሉ፡፡እንደዚህ ማሰቡም ብዙ ጊዜ ሲጠቅመኝ አይቻለሁ፡፡እነርሱም፡-
1.የውጨኛው አደባባይ(the outer court) ደረጃ
2.የመሀከለኛው አደባባይ(holy/the middle court) ደረጃ
3.የውስጠኛው አደባባይ/ቅድስተ ቅዱሳን(holy of holies) ደረጃ
ብዙዎቻችን በጸሎት ጊዜያችን የውጨኛውን አደባባይ ተሳልመንና የጌታን ጸጋ በሚገባ ሳንካፈልና በረከቱን ሳናይ ነው የምናቋርጠው ምንም እንኳ ዲሲፕሊን እንደሚያስፈልገን ብናምንም፡፡ለዚህ መፍትሔው በጽናት ወስኖ መቀጠል ነው፡፡አዘውትረንና ደጋግመን ስናደርገው ትግል መሆኑም ይቀራል፡፡እዚህ ደረጃ ላይ አእምሮአችን አስሩን ነገር ያስባል፣ይረግጣልም፡፡በዚህ ጊዜ የእንቅልፍ ስሜት፣ለመጸለይ ያለመነሣሣት እና ሌሎች ተቃራኒ ስሜቶች በሀይል ይታገሉናል፤የጠላት ከበባም ይኖራል፡፡
የመሀከለኛው አደባባይ የጸሎት ደረጃ የጌታ ህልውና የሚታወቀንና ለቀጣይ ጸሎት የምንነሣሣበት ደረጃ ነው፡፡“ሳበን ካንተም በኋላ እንሮጣለን” እያልን የጌታን ፊት በጨመረ ሁኔታ የምንፈልግበት የጸሎት ደረጃ ነው፡፡በዚህ ደረጃ ላይ የረካን መስሎንና በቂ ጸሎት የጸለይን
መስሎንና አንዳንዴም ተታለን ከጸሎት ልናቋርጥ አንችላለን፡፡እንደ መጀመሪያው ባይሆንም ጸሎታችንን የማቋረጥ ፈተናው እዚህም ደረጃ ላይ ቢሆን ከባድ ነው ማለቴ ነው፡፡ነገር
ግን ጨክነን በጽኑነት ከቀጠልን ወደ ሶስተኛው ደረጃ እንሻገራለን፡፡
የውስጠኛው አደባባይ የጸሎት
ደረጃ ብዙ ዝምታ የሚበዛበት፣በመንፈስ የምንቅታትበት፣እንባ ቋንቋችን የሚሆንበት፣ሮሜ
8፡26-27 ተግባራዊ የሚሆንበት፣ድንቅ ነገሮችን የምናይበትና በውስጣችን የሚታተምና የማይረሳ ክስተት የሚፈጠርበት የጸሎት ደረጃ
ነው፡፡እንደ እግዚአብሔር ፈቃድም በመንፈስ ስለምንጸልይ ጸሎታችን በሚገባ ይሰማል ብዬ አምናለሁ፡፡ይህ የጸሎት ደረጃ በህይወታችን
ሲበዛ እድገትና ለውጣችን በዛኑ ያህል ይጨምራል፡፡እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት የጸሎት ደረጃዎች ሉቃስ 11፡9 ላይ በግልጽ ሁኔታ ተቀምጠዋል፡፡እነርሱም ፡-
1.የመጠየቅ ደረጃ(the asking realm)፡-የመጀመሪያው የጸሎት ደረጃ ሲሆን፣በአእምሮአችንና በሥጋ የምንጸልየው ጸሎት ነው፡፡ማለትም እንዲሆኑልን የምንፈልጋቸውን ጉዳዮች በአአምሮአችን የምናሳውቅበት የጸሎት ደረጃ ነው፡፡
2.የመፈለግ ደረጃ(the seeking realm)፡-የጌታን ፊት በሀይል የምንፈልግበት የጸሎት ደረጃ ሲሆን፣ጠንከር ያለ ፀሎት የምንጸልይበትና የጌታ መንፈስ እስኪሰማን ድረስ የምንጸልየው ጸሎት ነው፡፡
3.የማንኳኳት ደረጃ(the knocking realm)፡-ይህ ጸሎት ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ለመግባት የምንጸልየው ጸሎት ነው፡፡ይህ የጸሎት ደረጃ ትግዕስት ያለበት፣የመንፈስ ቅዱስን ምሪት በንቃት መከታተል ያለበት፣ምስጋና ያለበት፣ንስሀ እና እንባ መገለጫዎቹ የሆኑበት የጸሎት ደረጃ ነው፡፡ከዚያም አንዴ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ከገባን በኋላ ቃላት ውሱን ይሆናሉ፤ ዝምታ ይበዛል፡፡በዚህ ጊዜ በትክክል በመንፈስ እንጸልያለን፡፡በማይነገር መቃተት እንደ ጌታ ፈቃድ የምንጸልበትና የምንማልድበት ጊዜም ይሆናል፡፡
ግሩም የሆነ የጸሎት ሕይወት እንዲኖረን የሚያደርገን ውሳኔ ነው፡፡ከቤት ማልደን ተነስትን ሳናረፍድ መሥሪያ ቤታችን የምንሄደው በውሳኔ ነው፤አዘውተረን ስላደረግነው ተነስተን ለመሄድ ምንም አንቸገርም፡፡ያንን መርህ ጸሎታችን ላይ በተግባር ማዋል አለብን፡፡እኔ ቢሰማኝም ባይሰማኝም አልነሳም ከጸሎት ብዬ የምወስንባቸው ብዙ ጊዜዎች አሉ፡፡እንዳውም እንዳልጸልይ በከበደኝ ጊዜ ገፍቼ ብዙ ሰዓት በውሳኔ ስጸልይ ካሰብሁት በላይ አስደናቂ ጊዜን አሳልፌ አውቃለሁ፡፡ባብዛኛው በራሴ ህይወት እንደማየው ጸሎታችንን እንድናቋርጥ ወደ አእምሮአችን የማይመጣ የፈተና አይነት የለም ነገር ግን ተቁነጥንጠን ስንነሳ ያንኑ የምናውቀውን ሕይወትና ኑሮ ነው የምንቀጥለው፡፡ ከጌታ ጋር ብናሳልፍ ግን ሕይወታችን እየተለወጠና የጌታ ጸጋ በሕይወታችን እያደገ ይመጣል፡፡አለበለዚያ ግን ልንመኝ ልናስመስል እና ዝም ብሎ በባዶው ልንጓጓ እንችል ይሆናል እንጂ በነካ ነካ ጸሎት የእግዚአብሔርን ክብርና ጉብኝት አናይም፡፡ ስለዚህ መልካሚቱ እጁ በመካከላችን እንድትበዛ በጸሎት እንጋደል!
ጸሎት ፡-ጌታ ሆይ ከዳር ዳር ጸሎት እባክህ ክብርህን ወደምናይበት የጸሎት ጥልቀት ውስጥ ክተተን!
በቀለ በላቸው(ዶ/ር)
240-330-5004
No comments:
Post a Comment