ከልብህ ሀዘንን አርቅ
ወደ ስምንት አመት ገደማ ይሆናል፡፡በአንድ ከፍ ያለ የልብ ስብራት ውስጥ ሆኜ መቆዘም አብዝቼ ነበር፡፡ሐዘኔ ከበድ ያለ ስለነበር ከሰው ጋር መገናኘትና ማውራት አስጠልቶኝ ነበር፡፡በዛ ሁኔታ ውስጥ ሳለሁ የጌታ መንፈስ ደረሰልኝና አንድ ነገር አበራልኝ፡፡እርሱም ይህንን ያለሁበትን ሁኔታ የማራገፍ ሀላፊነት የኔ እንደ ሆነ በቃሉ ብርሃን ተገነዝብኩ፡፡የበራልኝ ቃል የሚገኘው መክብብ 11፡10 ላይ ያለ ቃል ሲሆን እንዲህ ይላል፡-
‹‹ከልብህ ሀዘንን አርቅ››
ይህ ቃል ልቤን ሰንጥቆ ነበርና የገባው ውስጤ በግርምት ነበር የተሞላው፤ለነበርሁበት ሁኔታም ‹‹የጊዜው ቃል›› ነበር፡፡አዝኜ የአጋንንት መጫወቻ ሆኜ እያላዘንሁ መቀመጥ እንደሌለብኝ በሚገባ ገባኝ፡፡ከዛም ከነበርሁበት ሁኔታ ለመውጣት ጌታ ጠንከር ያሉ ጸሎቶችን በመያዝ ትግል መጀመር እንዳለብኝ አመለከተኝ፡፡ባጋጣሚ የምኖርበት ቤት አጠገብ አንድ የመሠረተ ክርስቶስ አጥቢያ ቤ/ክ ነበርና እዚያ በፈረቃ ግቢውን የሚጠብቁትን ሰራተኞች እያስፈቀድሁ በጣም ረጅም ሰዓታት ባዶ አዳራሽ ውስጥ መጮህና መቃተት ጀመርሁ፡፡መጀመሪያ ይህንን ትግል ስጀምር ይሰማኝ የነበረው ስሜት ልክ ግምብ የመግፋት ያህል ነበር ፡፡የሚሰማኝ ስሜት ሳይበግረኝ በጸሎት መገሥገሥ ጀመርሁ፡፡በመሀል አንዳንዴ ካለሁበት ሁኔታ ጋር የሚሄዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን እያጠናሁና እያሰላሰልሁ ከዚያ ደግሞ ቀጥዬ በመቃተትና የጌታ መንፈስ እንዲረዳኝ በመማጸን ሳልፈወስ ከምሽጌ ላልወጣ ለራሴ ቃል ገባሁ፡፡ለተወሰኑ ቀናት እንዲህ ባለ ሁኔታ ካሳለፍኩ በኋላ ሁኔታው ሁሉ ተገልብጦ ሰላምና ደስታ በማያቋርጥ ሁኔታ በልቤ ውስጥ ይፈስ ጀመር፡፡ዝማሬ፣ አምልኮ፣ስግደት ፣ውዳሴ ወዘተ በሕይወቴ ተትረፈረፈ፡፡ከዚያም ለረጅም ወራት እየጸለይኩ ውዬ ባድር ፤ስለጌታ ሳወራ ብውልና ሳመስግን ባድር ደስ ይለኝ እንደ ነበር ትዝ ይለኛል፡፡እዚህ ምድር ላይ ሁሉ የምኖር አልመስለኝ አለ፡፡የእግዚአብሔር ህልውና በሚገርም ሁኔታ እላዬ ላይ ነበር፡፡ብቻዬን ሆኜ ማንም ሳያወራኝ ሁሉ ሳቅ ያስፈነድቀኝ እንደነበር ሁሉ ትዝ ይለኛል፡፡መለኮታዊ ነበርና የነበርኩበትን ሁኔታ በቃላት መግለጽ ያዳግተኛል፡፡ክርስትና ዝም ብሎ ስርዓትና ወግ እንዳልሆነ ያስገነዘበኝም ክስተት ነበር፡፡ከጌታ ጋር በሚደረግ ሕብረት አስደናቂ በረከቶች ማፈስ እንደሚቻል ልቤ ላይ ትልቅ የሕይወት ማህተም አትሞልኝ የሄደ ድንቅ ጊዜ ነበርና ባሰብኩት ቁጥር ለጸሎት እነሣሣለሁ፡፡
ኢሳ 35፡10 ላይ የነበርኩበትን ሁኔታ የሚገልጸው ይመስለኛል፡፡እንዲህ ይነበባል፡-
‹‹እግዚአብሔርም የተቤዣቸው ይመለሳሉ እየዘመሩም ወደ ጽዮን ይመጣሉ የዘላለም ደስታ በራሳቸው ላይ ይሆናል ሀሴትንና ደስታን ያገኛሉ ሀዘንና ትካዜም ይሸሻሉ››
አዎ ያ ሁሉ ሐዘንና ትካዜ የት አንደገባ እስገሚገርመኝ ድረስ በሀሴት ተጥለቀለቅሁ፡፡ለዚህ ነው ኢሳ 10፡27 ‹‹በዚያም ቀን ሸክሙ ከጫንቃህ ቀንበሩም ከአንገትህ ይወርዳል ቀንበሩም ከውፍረት የተነሳ ይሰበራል››የሚለው፡፡ጠንከር ያሉና የጠለቁ ጸሎቶችን ስናበዛ የጌታ ጸጋ በውስጣችን እየጨመረ ስለሚሄድ ማንኛውንም አዚምና ሐዘን ለመስበር የምንችልበትን አቅምና ጉልበት እናገኛለን፡፡በጽኑነት ከልብ ሆነንና በቀጣይነት ሳንታክት በምንጸልየው ጸሎት ብዙ ድንቅ መለኮታዊ ነገሮችንም እናያለን ብዬ አምናለሁ፡፡ስለዚህ ከነካ ነካ የጸሎት ሕይወት ጌታ ወደ ጠለቀ ልምምድ እንዲከተን ሳንታክት ፊቱን ያለማቋረጥ እንሻ፡፡እንዲህ ብናደርግ ያስደንቀናል፡፡ስሙ ለዘላለም የተባረከ ይሁን!
No comments:
Post a Comment