Saturday, March 29, 2014

የምስጋና መጎናጸፊያ




March 29, 2014
የምስጋና መጎናጸፊያ

እለቱ ሰኞ ነበር፡፡ከስራ አድሬ ቤት የደረስሁት ማለዳ ጧት ነበርና ለአምስት ሰዓታት ገደማ ተኝቼ ነበር ካልጋዬ የተነሳሁት፡፡እንደተነሳሁም ቤት ያፈራውን ቀማምሼ ኮምፒዩተሬ ፊት ካለው ወንበር ላይ ተቀመጥሁ፡፡በቀደሙት ሰሞናት ያለምኳቸውና ያሰብኳቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ተከናውነው አላለቁምና ድንገት ትዝ ብለውኝ በሀይል አስተከዙኝ፡፡ምኑም አልጥመኝ ብሎኝ እጅግ ተጫጭኖኛል፡፡መግለጽ የማልችለው ስሜት ከብቦኝና ማሰብ አቅቶኝ ደንዝዤ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ዳዊት ይህንን የኔን ስሜት በመዝ 43፡2 ላይ እንዲህ ብሎ ገልጾታል፡-

‹‹አንተ አምላኬ ሀይሌም ለምን ትተወኛለህ ? ጠላቶቼ ሲያስጨንቁኝ ለምን አዝኜ እመላለሳለሁ?››

በእንደዚህ አይነት ስሜት ውስጥ ስከበብ የሚታየኝ ነገር መጸለይ ነው፡፡ነገር ግን መጸለይ አቅቶኛል፤አስጠልቶኛልም፡፡በቅጽበት አንድ የእግዚአብሔር ሰው የተናገሩት ነገር ትዝ አለኝ፡፡እንዲህ ነበር ያሉት ፡-

‹‹የመጸለይ ፍላጎት ስታጣና መጸለይ ሲያቅትህ ራስህን ካገኘኸው መጸለይ ያለብህ ያኔ ነው››

አዎ ትክክል ነበር የተናገሩት፡፡ከሰውየው ሀሳብ ጋር በመስማማት እንደምንም ሸርተት ብዬ ለጸሎት በጉልበቴ ተንበረከክሁ፡፡የምተነፍሰው ነገር ግን አንደበቴ ላይ አልነበረም፡፡ለረጅም ጊዜ ጸጥታ ሆነ፡፡ከብዙ ጸጥታ በኋላ አንድ አምልኮ መዝሙር ከፍቼ አብሬ በጸሎት መንፈስ መዘመርና መፍሰስ ጀመርሁ፡፡በመሀልም በልሳን ረዘም ላሉ ደቂቃዎች መጸለዬን ቀጠልሁ፡፡እላዬ ላይ የነበረው የከበደኝ ጉም እስኪገፈፍ ላልነሳ ጨከንኩ፡፡ታምኜ በእምነት እንጂ በማየት ላለመላላስ(2 ቆሮ 5፡6) በመንፈስ አይኖቼን ወደ ጌታዬ አነሳሁ፡፡ብዙ ሰዓታትን በመቃተት አሳልፌ ለደቂቃ ከተንበረከኩበት ተነስቼ መብራት ላበራ ስል የሆነ ለየት ያለ ቀድሞ ያልነበረ ጉልበትና መታደስ ወደ ውስጤ እንደመጣ ታወቀኝና ደነቀኝ፡፡

ከዚያም ሁኔታው ገርሞኝ የበለጠ እየተነቃቃሁ ለረጅም ጊዜ ጸለይሁ፡፡ግሩምና ድንቅ የሆነ የተለቀቀ አምልኮና ውዳሴም ውስጥ እራሴን አገኘሁት፡፡ከዚያ የጸሎት ሰአት ጅምሮ ይህንን መልእክት እስከጻፍኩበት ጊዜ ድረስ የማያቋርጥ የዝማሬ፣የደስታና የሰላምን መንፈስን ተጎናጽፌአለሁ፡፡ይህንን የእኔን ሁኔታ የሚገልጽ ቃል ኢሳ 61፡1-3 ላይ እናገኛለን፡፡እንዲህ ዘርዝሬ ባቀርበው ይፈቀድልኝ፡፡

‹‹የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው እግዚአብሔር ቀብቶኛልና(ስለ ኢየሱስ አገልግሎት ነው ነቢዩ የጻፈልን)፡፡ለመሆኑ ለምንድነው የተቀባው???መልሱ እንደሚከተለው ነው፡-

  • የተሰበረውን ይጠግን ዘንድ

  • ለተማረኩት ነጻነትን ለታሰሩትም መፈታትን  ይናገር ዘንድ

  • የሚያለቅሱትን ሁሉ ያጽናና ዘንድ

  • በአመድ ፋንታ አክሊልን፣በልቅሶም ፋንታ የደስታን ዘይት፤በሃዘንም መንፈስ ፋንታ የምስጋናን መጎናጸፊያ ይሰጥ ዘንድ››

የከበበኝ ጉም ተበትኖ እና ‹‹በሃዘን መንፈስ ፋንታ የምስጋና መጎናጸፊያ››ተደርቦልኝ በሚያማምሩ ድንቅ ዝማሬዎች ታጅቤ አመሻሹ ላይ ወደ ስራዬ አመራሁ፡፡ለመሆኑ ይህንን ህክምና የት አገኘው ኖሯል?እርሱን የሚወዳደር ሀኪምስ የት ይገኛል?

ዋናው መልእክቴም እንዲህ ነው፡-
ኢሳያስ 12፡3 ላይ ‹‹ውሀውንም ከመድሀኒት ምንጮች በደስታ ትቀዳላችሁ›› እንደሚል በእንደዚህ አይነት ማዕበል ውስጥ ስትገቡና ስትዳክሩ፣በነፍሳችሁ መታገሉን አቁማችሁ ወደ ጸጋው ዙፋን ኑ(ዕብ 4፡16)፡፡እናም ከዚህ ተዝቆ ከማያልቅ ፋርማሲ መድሀኒታችሁን እፈሱ!!! በመንፈሴ እንጂ በሀይልና በብርታት አይደለም(ዘካ 4፡6) ይላልና!!!

No comments:

Post a Comment