የምናልፍባቸው
ጎዳናዎች
እግዚአብሔር እኛን ለመስራት በተለያዩ የህይወት ጎዳናዎች ወደድንም ጠላንም ያሳልፈናል፡፡የለቅሶ
ዘመን አለ፤የመከራ ዘመን አለ፤የጭንቅ ዘመን አለ፤የእጦት ዘመን አለ ደግሞም የእረፍት እና የበረከት ዘመን አለ፡፡ለዚህ ነው መዝ
84:6 ላይ ‹‹በለቅሶ ሸለቆ በወሰነው ስፍራ የህግ መምህር በረከትን ይሰጣልና ከሀይል ወደ ሀይል ይሔዳሉ›› በማለት የለቅሶ ጊዜ
እንዳለ የሚያበስረን፡፡
እግዚአብሔር ሊሰራን፣ሊያበጃጀን(መዝ 119፡73) እና ከእኛ ላይ አላስፈላጊውን እንደ እልህ፣በገዛ
ፈቃድ መሄድ እና ትዕቢትን ሊያራግፍ እና ሊያለዝበን በብዙ ነገሮች ውስጥ ያሳልፈናል፡፡ይህንን የሚገልጽ ግሩም ቃል መዝ 66፡10-12
ላይ እናገኛለን፡፡እንዲህ ይነበባል፡-
‹‹አቤቱ ፈትነኸናልና፤ብርን እንደሚያነጥሩት አንጥረኸናልና፡፡ወደ ወጥመድ አገባኸን፤በራሳችን
ላይ ሰውን አስረገጥኸን፤በእሳትና በውሀ መካከል አለፍን፤ወደ እረፍትም አወጣኸን››
አዎ የፈተና፣የንቀት፣የስድብ እና የመከራ ዘመን አለ፡፡የጌታ ጊዜ ሲደርስ ደግሞ ግሩም የሆነ
የእረፍት ጊዜ አለ፡፡የፈተናው እና የመከራው ዘመን ያማል፣አንገትን ያስደፋል፣ያስለቅሳል፣ግራ ያጋባል ወዘተ፡፡በእንደዚህ አይነቱ
ጊዜ ከእርሱ ጋር ተጣብቀንና አጥብቀን የጌታን ፊት የምንፈልግ ከሆነ እግዚአብሔር እንደሚደግፍ፣እንደሚያጽናና፣እንደሚረዳ በተግባር
ደረጃ የምናውቅበት ጥሩ አጋጣሚ ይሆንልናል፡፡
በሆሴዕ ምእራፍ ሁለት ላይ እግዚአብሔር እስራኤልን ከነበረችበት የሞራል ውድቀት ለመመለስ ወደ
መከራ ውስጥ እንደሚከታት እናያለን፡፡ በሆሴ 2፡16 ላይ እንዲህ ይላል ፡-
‹‹ አባብላታለሁ ወደ ምደረ በዳም አመጣታለሁ፤ለልብዋም እናገራለሁ››
እዚህ ቃል ላይ እንደምናየው ‹‹ለልብዋም እናገራለሁ››የሚለው ቃል ያስደንቀኛል፡፡ቃሉ በመከራ
ውስጥ ከእግዚአብሔር ጋር በመሆንና ጊዜን በማሳለፍ ስለሚመጣ ድንቅ ህብረትና በረከት ነው የሚናገረው፡፡በእኛም ህይወት እንዲሁ ነው
የሚሆነው፡፡የእግዚአብሔር ድምጽ ሲመጣ በብዙ ክብር ነው የሚመጣው(መዝ 29፡1-11 ያንቡ)፡፡ድምጹ ሲመጣና ለልባችን ሲናገረን ደግሞ
እምነታችን ያድጋል፣ይጠነክራል፤ሰላማችን ይበዛል፤ሕይወታችን ይታደሳል፤መንፈሳዊ ህይወታችን ይለወጣል ያድግማል፡፡
በዚሁ በሆሴዕ 2፡17-19 ላይ እግዚአብሔር ወደ ምድረ በዳ አባብሎ እስራኤልን ከከተታት በኋላ
በእስራኤል ላይ ስለሚመጣው አስገራሚና አስደናቂ መንፈሳዊ ለውጥ(transformation) እንዲህ ብሎ ይናገራል፡-
‹‹ከዚያም የወይን ቦታዋን የተስፋ በርም እንዲሆንላት የአኮርን ሸለቆ እሰጣታለሁ፤በዚያም ከግብጽ
ምድር እንደ ወጣችበት ቀን እንደ ህጻንነትዋ ወራት ትዘምራለች፡፡በዚያ ቀን ባሌ ብለሽ ትጠሪኛለሽ እንጂ ዳግመኛ በኣሌ ብለሽ አትጠሪኝም
ይላል እግዚአብሔር፤የበአሊምን ስም ከአፍሽ አስወግደዋለሁና በስማቸውም እንግዲህ አይታሰቡምና››
አዎ ከቃሉ እንደምንረዳው ያ ምድረ በዳ እና የመከራ ቦታ ለእስራኤል ትልቅ መንፈሳዊ ለውጥንና በረከትን እንዳመጣላት
እንገነዘባለን፡፡ህብረቷ፣አምልኮዋ፣ይዞታዋና ከጌታዋ ጋር ያላት ህብረት እና ግንኑነት እንደታደሰና እንደጠለቀም እናያለን፡፡
ከድሎት ዘመን ይልቅ በዚህኛው ዘመን ውስጥ ብዙ ጸሎትና ፊቱን መፈለግ ይስተዋላል፡፡ጊዜው መርዘሙ
ቢያታክተንም ለመንፈሳዊ እድገት ግን ትልቅ አጋጣሚ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ለዚህም ነው በያዕ 1፡1-4 ላይ እንዲህ ብሎ ሀዋርያው
ያዕቆብ ገራሚ ምክርን የሚመክረን፡-
‹‹ወንድሞቼ ሆይ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግስትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ ልዩ ልዩ ፈተና
ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት፡፡ትዕግሥትም ምንም የሚጎደላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም››
ይህ የፈተናና የመከራ ወቅት የምንሰራበት፤ጌታን በግል በሚገባ የምናውቅበት፤ግንኙነታችን የሚጠልቅበትና
ዕውቀታችንን ወደ ጥበብ ለመለወጥ ጊዜ የምናገኝበት መልካም አጋጣሚ ነው፡፡፡በዚህ አይነት ሁኔታ ከጌታው ጋር ተስማምቶ በጌታ መንፈስ
እና ምሪት ይህንን የፈተና ጊዜ ዘልቆ የወጣ ሰውም ምስክርነቱ፣ህይወቱና ምልልሱ ጠንከር ያለ መልእክት ነው የሚሆነው፡፡
በተፈጥሮአችን ድሎተ-አፍቃሪ ስለሆንን በፍጹም እንዲህ አይነቱን ነገር ስንሸሽ ነው የምንኖረው፡፡በጣም
ነው የምንፈራውም፡፡ምክንያቱም አንድ ነገር ነው-ሰለሚያመን!ስለዚህ ነው ጌታ ወዳልጠበቅነው የህይወት ሁኔታ ውስጥ እያባበለና እየከተተ
ለእጆቻችን ሰልፍን የሚያስተምረን(መዝ 18፡34)፡፡ከድሎት ሰፈር ወደ ተግዳሮት ሰፈር እየወሰደ የሚቀርጸን!
በመከራና በተግዳሮት ውስጥ ሳለን ደስ የሚለው ነገር የአጽናኙ የመንፈስ ቅዱስ ድጋፍ አለን፡፡በፍጹም
ለደቂቃም ቢሆን አይለየንም፡፡በተለይ በጸሎት በሚገባ ለምንተጋ ሰዎች ተግዳሮቱን የምንጋፈጠው የጌታ ህልውና በሚታወቀን መጠን ስለሆነና
ልባችን በእግዚአብሔር ሰላም እየተጠበቀ ስለሆነ በተገላቢጦሽ በሕይወታችን የማይረሳ የበረከት ጊዜ ሁሉ ሊሆልንን ይችላል የሚል መረዳት
አለኝ፡፡እንዲህም አይነት ምስክርነት ያላቸው ብዙ ሰዎችንም አውቃለሁ፡፡
በእንደዚህ አይነት የፈተና ሰአት ሰዋዊ፣ስጋዊ፣እና ኢ-መጽሀፋፍ ቅዱሳዊ ስልቶችንና አካሄዶችን
በመጠቀምና ከእግዚአብሔር መለኮታዊ አጀንዳ እንዳናፈነግጥና የበረከታችን ዘመን እንዳይረዝም ከጌታ ጥበብና ጸጋ እንዲበዛልን ብዙ
መቃተትና መጮህ ያስፈልገናል፡፡ወደ ኮምፎርት ዞን የሚመልሱ አቋራጮችን ተጠቅመን ከመለኮታዊ አሰራሩ ሾልከን እንዳንወጣም በሀይል
ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡
በመጨረሻ በተግባር ደረጃ እንዲህ እናድርግ፡-
- በእርሱ ፊት ያለማቅማማት ጨክነን እንውደቅ
- እንጹም
- በተመሳሳይ የህይወት ሁኔታ ካሉና ካለፉ ሰዎች ጋር አብረን በመሆን የጌታን ፊት እንፈልግ
- ከቃሉ ጋር ያላሰለሰ ቁርኝት እናድርግ
ያለንበትን የህይወት ሁኔታ በድል እስክንወጣው ድረስ ክእርሱ ጋር እንጣበቅ!!
በቀለ በላቸው(ዶ/ር)
beke_abay@yahoo.com
240-330-5004
No comments:
Post a Comment