ወዳጄ ማስተዋል
ሰሞኑን ከወትሮው በርከት ላሉ ሰዓታት፣
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይዤ ነበር፡፡የእግዚአብሔርን ቃል እያሰላሰልሁ ሳለሁ፣ከወትሮው ዓይኔ ተከፍቶ የእግዚአብሔርን ቃል
ሳስተውል ልቤ በደስታ ከነፈ፡፡ኢየሱስን ተረድቼው በማላውቀው መንገድ ድንገት በመንፈስ አስተዋልሁትና ደነቀኝ፡፡እናም ከልብ
በመንፈስ ሆኜ ሰገድሁ፡፡ከዚያም የጌታን መንፈስ “እባክህ የበለጠ ዓይኔን ክፈትልኝ፣ማስተዋልን አብዛልኝ” ብዬም ተማጸንሁት፡፡
ንጉሥ ዳዊት “የቃልህ ፍቺ
ያበራል፣ሕጻናትን አስተዋይ ያደርጋል”(መዝሙር 119፡130) ብሎ የተናገረው ቃልም ገባኝ፡፡እውነት ነው የቃሉ
ብርሃንና ማስተዋል በሚገባ ይያያዛሉ፡፡እርግጥ ነው መንፈስ ቅዱስ ቃሉን ሲፈታውና ሲተረትረው የሚከተለው ሂደት ይመጣል፡-
- ቃሉ ሲፈታ ------› ያበራል(ዓይንን ይከፈታል)-------›ማስተዋል------›ደስታ፣እርካታ፣ዕረፍት ወዘተ
አዎ የልባችን ዓይኖች ሲበሩ
በረከቱ ብዙ ነው፡፡የመጀመሪያው በረከት ግን አእምሮን የሚያልፍ ሰላምና ደስታ ነው፡፡ይህንን ሃሳብ የሚደግፉ ጥቅሶች ከምሳሌ
መጽሐፍ ላይ ላቅርብ ፡-
- ዓይንህን ክፈት እንጀራም ትጠግባለህ (ምሳሌ 20፡13)
- የዓይን ብርሃን ልብን ደስ ያሰኛል(ምሳሌ 15፡30)
ወገኖቼ ከላይ በመግቢያ
እንደጠቀስኩት የዛን ቀን የነበረኝ መለኮታዊ ጉብኝት አስደንቆኝ አልፏል፡፡እንዲህ ዓይነት ጊዜዎች ቢበዙልኝ በሕይወቴ ምን
ዓይነት ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል ተገንዝቤም “እባክህ ጌታ ሆይ ዳር ላይ ካለ ሕይወት ወደ ጠለቀ መረዳት ውስጥ እንድገባና ነፍሴ
እንድታርፍ እርዳኝ” ብዬ አምላኬን በኃይል ለመንሁት፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስትያኖች
“በማስተዋል ወደሚገኝበት ወደ መረዳት ባለጠግነት ”(ቆላስይስ 2፡2) እንዲደርሱ የጸለየላቸውም ጸሎት ትዝ አለኝ፡፡በዚህ ጥቅስ
መሠረት “ማስተዋል” ዋና ነገር እንደ ሆነና የመረዳት ባለጠጋ ሊያደርገኝ የሚችል ዋጋ ያለው ነገር እንደ ሆነ ገባኝ፡፡
ማስተዋል “የተሰወረ የዕውቀትና የጥበብ መዝገብ”(ቆላስይስ 2፡3) የሆነውን ጌታ እንዳውቅ የሚያደርገኝ ሃብት እንደ
ሆነም ተረድቼ በብዙ እንዳገኘሁ ቃተትሁ፡፡ንጉሥ ሰለሞን “ማስተዋልን፡- ወዳጄ ብለህ ጥራት (ምሳሌ 7፡4) ብሎ የመከረንም ቃል
ትዝ አለኝ፡፡በልቤም “ታዲያ ሌላስ ከዚህ የከበረ ጸሎት ሌላ ምን ይኖረኛል?” አልኩ፡፡
ከዚያማ መንፈሳዊውን ዓለም
በማስተዋልና ይህን የከበረ ጌታ በማወቅ የማገኛቸውን ወደ አእምሮዬ የመጡ ጥቅሞች በብዕሬ ዘረዘርሁ፡፡የዘረዘርኳቸውን ጥቅሞችም
አየሁኝና ይበልጥ ትልቅ ጉጉት አደረብኝ፡፡የማገኛቸው በረከቶች እነዚህ ናቸው ፡-
- ከጌታ ጋር ግሩም የሆነ ሕብረት
- ሰላምና መረጋጋት
- ጥልቅ የሆነ ርካታ
- ከመቅበዝበዝ ያረፈ ሕይወት
- በወጀብና በመከራ ውስጥ መጽናት ወዘተ
ወገኖቼ ዓይኖቼ የበለጠ
እንዲከፈቱ፣ማስተዋል እንዲመጣና ይህንን የክብር ንጉሥ ኢየሱስን በሚገባ እንድናውቀው አንድርምጃ ሄጄ ወስኛለሁ፡፡ይህንን
ሃሳብ የሚጋራና ከኔ ጋር የሚወስን አሜን ይበል !!!
No comments:
Post a Comment