Tuesday, October 28, 2014

መሪውን እንስጠው





Oct 29,2014
መሪውን እንስጠው

እጅግ በጣም አሳዛኝ ነው በመሃከላችን ብዙ የነፍስ ክሳት መኖሩ፣ከጌታ ዘንድ ድንቅ የሆኑ የግብዣ ጥሪዎች ሞልተውልን ሳለ፤የሚያረካ፣ነፍስን የሚያሳርፍ፣ልባችንን አእምሮን በሚያልፍ ሰላም የሚባርክ ጌታ ሳለ፤እንቆቅልሾቻችን የሚፈታ፣በከፍታዎች የሚያስሄደን ክንደ ብርቱ አምላክ ሳለ፡፡ለናሙና የሚከተሉት ድንቅ ግብዣዎችና ምስክርነትም ሳሉልን፡-

“ገንዘብን እንጀራ ላይደለ፣የድካማችሁንም ዋጋ ለማያጠግብ ነገር ለምን ትመዝናላችሁ? አድምጡኝ በረከትንም ብሉ ሰውነታችሁ በጮማ ደስ ይበለው” (ኢሳይያስ 55፡2)
“ወደ ዘለፋዬ ብትመለሱ መንፈሴን አፈስስላችኋለሁ”(ምሳሌ 1፡23)
“ልጄ ሆይ መልካም ነውና ማር ብላ፣ወለላም ለጣዕምህ ጣፋጭ ነው፡፡ጥበብም ለነፍስህ እንዲሁ እንደሚሆን እወቅ፤ብታገኘውም ፍጻሜህ መልካም ይሆናል፣ተሰፋህም አይጠፋም”(ምሳሌ 24፡13-14)
እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ፣እኔም አሳርፋችኋለሁ…….ከእኔም ተማሩ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ(ማቴዎስ 28-30)
በሕይወቴ ዘመን አመሰግንሃለሁ፤በአንተም ስም እጆቼን አነሣለሁ፡፡ነፍሴ በቅቤና በስብ እንደሚጠግቡ ትጠግባለች፤ከንፈሮቼም ስምህን በደስታ ያመሰግናሉ(መዝሙር 63፡5-6)

ደግሞ ደጋግሞ በተለያየ መንገድ የጌታ መንፈስ ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም (ዮሐንስ 15፡5)፤ከእኔ ጋር ተጣበቁ ብሎ ቢመክረንም፤እኛ ግን ሰዋዊ ነገሮችንና ዓለማዊ ዘዴዎችን አስቀደምንና ከመካከላችን አስወጣነው፡፡ነገር ግን ያለ እሱ ሕልውና ሕይወት ጣዕም-አልባ መሆኑ ሊታወቅ ይገባዋል፡፡እንደፈለገ ምድራዊ ነገሮች ቢኖሩን፣እንደፈለግን በዙሪያችን ሰዎች ቢከቡን፣እንደፈለግን ቁሳዊ ነገሮችን ቢተርፉን፣ያለ አብሮነቱ ኑሮ ባዶ መሆኑን መገንዘብ ይገባናል፡፡

እስቲ ጎበዝ ቆም ብለን እናስብ፡፡ግሩም ሆኖ የተዘረጋ እጅ እያለ ምነው በረሃብ ማለቃችን ? ምነውስ መንፈሳዊ ችግሮቻችን በዙ?በብዙ አሳዛኝ ሁኔታዎች ተከብበን፣ምንም ነገር እንዳልሆነ እየቆጠርንና ሁኔታዎችን እየካድን ዝም ብለን ነፋስን አንጎስም፡፡ጌታ በልባችን ደጅ ቆሞ ክፈቱልኝ ልግባና ልሥራ (ራዕይ 3፡20) እያለን ነው፤እኛ ግን በእምቢተኝነት አለን፡፡ወገኖቼ ይህ በየቦታው የሚታይ እምቢታና እልኸኝነት ካላስለቀሰን ሌላ ምን ሊያስለቅሰን እንደሚችል እኔ አይገባኝም፡፡እስቲ አስቡት ያለ እሱ የትኛው ሰልፍስ ይከናወናል? ያለሱስ ዘዴዎቻችንና ብልሃቶቻችን የት ያደርሱናል ? የትኛው የአምልኮ ጉባዔስ ያለ እሱ ይደምቃል? ያለሱ መገኘትስ የትኛው እንቆቅልሽ ይፈታል ? ኧረ እባካችሁ ወደ ልባችን እንመለስ! ደግሜ ላስታውሳችሁና እየሆነ ያለው እንዲህ ነው፡-

  • ልፈውሳችሁ በጸጋው ዙፋኔ ፊት ኑና ውደቁ ሲል ለደቂቃዎች እንኳ መገኘት አቃተን
  • ልምራችሁ ሲለን እምቢ አልን
  • ልቅደምና ልሥራ ተከተሉኝ ሲለን እኛ ቀደምነው
  • ታዘዙኝ ሲለን በልባችን እምቢተኝነት ሽምጥ ጋለብን

እሱ ግን እጅግ ትሑት ነውና አሁንም እጁን ዘርግቶ ይጠብቀናል(ኢሳይያስ 9፡12፣17)፡፡አስቀድሙኝ እያለ እየለመን አጠገባችን አለ፡፡እሺ በሉኝና ልሥራም እያለን ነው፡፡አዎ መሪውን ስጡኝና እኔ ልምራችሁ እያለ በብዙ እየተናገረን ይገኛል፡፡ነገር ግን ባዶ ዕውቀትና ፍልስፍና ይዞን አልቅን፤ማስተዋል እርቆን ሳትን፡፡ሁለት ትልልቅ ክፉ ነገሮችን አደረግን፡-“የሕያውን ውሃ ምንጭ ትተናል፤ውሃውን ይይዙ ዘንድ የማይችሉትን ጉድጓዶች ለራሳችን ቆፍረናል”(ኤርምያስ 2፡13)፡፡የራሳችንን እሳት አንድደን ባነደድነው ወላፈን  እየሄድን ነው(ኢሳይያስ 50፡11)፡፡ስለዚህ ሐዘናችን፣እንቆቅልሾቻችንና ስብራቶቻቸን በዝተዋል፡፡ስለዚህ በብዙ ጥልቅ ንስሐና ልቅሶ አምርረን እንፈልገው፡፡በድለንሃል እንበለው፡፡ “ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደምትናፍቅ ነፍሴ አንተን ትናፍሃለች”(መዝሙር 42፡1) እንበለው፡፡

በጥልቅ ንስሐ ከተመለስን፣በብዙ ዕንባ በፊቱ ከቀረብን፣ከምር በረከቱን እንደ ያዕቆብ ከፈለግን ወገኖቼ ምንም ጥርጥር የለውም ተገኝቶ ያስደንቀናል፡፡እውነተኞች ከሆንንና አሁን ያለንበትን መንፈሳዊ ሕይወት ከጠላነውና፣ወደ ፊት እንዲስበን እጃችን ከሰጠነው፣ለሱ መሸነፋችንን በግልጽነትና በቅንነት ካሳየነው እንዲሁም ከመሪው ላይ እጆቻችን ካነሳን፣ባስደናቂ መገኘቱ ይባርከናልና እጅ ወደ ላይ እንበል!!

በቀለ ብርሃኑ(ዶ/ር)
240-330-5004

No comments:

Post a Comment