Friday, October 24, 2014

ከምድር ሲኦል ያመለጠው ዳኒ ቬላስኮ

ከምድር ሲኦል ያመለጠው ዳኒ ቬላስኮ

የ17 ዓመት ወጣት ሳለሁ በውበት ሳሎን ውስጥ ጸጉር መሥራትና የሜክ-አፕ አርት ባለሙያ ሆኜና ተቀጥሬ እሠራ ነበር፡፡በዛን ጊዜ በጣም ታዋቂነትን ስላተረፍኩ መጽሔቶች ላይ መውጣት ጀመርሁ፡፡ባጭር ጊዜ ውስጥ በሙያው ስሜ በኃይል ናኘ፡፡ቢሆንም ውስጤ ሁለት የተለያዩ ሰዎች እንዳሉ ይሰማኝ ነበር፡፡አብሮኝ የኖረ ጥልቅ የበታችነትም ስሜት ያሸኝ ነበር፡፡ሃኪም ጋ ሄጄ አእምሮዬ እንዲረጋጋና ጸጥታ እንዲሰማኝ ቫሊየም (valium) አዘዘልኝ፡፡እኔ ግን መድሐኒቱን ከቮድካ ጋር ቀላቅዬ እየወሰድሁ መደንዘዝና ራሴን መሳት ጀመርሁ፡፡ማታ ማታ እንዲህ እያሳለፍሁም ቢሆን፣ቀን ሥራዬን ያለ ብዙ ችግር እሠራ ነበር፡፡

ነገሮች እያሽቆለቆሉ የሙያዬ ዕድገት በ20 ዎቹ ላይ ተገታ፡፡ውስጣዊ እረፍት በማጣቴ ወደ ፓሪስ አመራሁና እንደ ገና ሙያዬን ከዚሮ ጀመርሁ፡፡እዚያም እንደ ደረስሁ ፣ብዙ የሚያቁኝ ቀጣሪዎችም ባይኖሩ የሥራ በሮች በኃይል ተከፈቱ፡፡ሥራዬም መጽሔቶች ላይ መውጣት ጀመሩና ብር ማፈስ ጀመርሁ፡፡ሞያዬም ከፍተኛ ዝናን አላበሰኝ፡፡
ከአራት ዓመት በኋላ ወደ ኒውዬርክ ተመለስኩና ሥራዬን ቀጠልሁ፡፡ያኔ በቀን እስከ 3000 ዶላር በቀን አገኝ ጀመር፡፤በዓለም ምርጥ የውበት ሳሎኖች እየተጠራሁ እሠራ ነበር፡፡ቢሆንም ከፓሪስ ስመለስ የሄሮይን ጥገኛ ሆኜ ነበር የተመለስኩት፡፡ቀን ሥራዬን እሠራለሁ፣ማታ ማታ ግን የሱስ እስረኛ ሆንሁ፡፡የመጠጥ ዓይነት አይቀረኝም ነበር፡፡ስለዚህም መታሰርና ከሥራ መቅረት አበዛሁ፡፡ባንዴ ሁለት ሰው ነበርሁ-ጥሩ ሙያዊ ሥራ የሚሠራና፣ድራሻባቱ ጠፍቶ የሚያድር፤በስሜት ጦዞ ከፍታን የሚረግጥ፣ከዚያም በሚያስደነግጥ ድብርት ዘብጥያ የሚገኝ!

ወደ ቤቴ ስመለስ ከዛ ሁሉ መወራጨት በኋላ ውስጤ ባዶ ይሆን ነበር፡፡ከዚህም የተነሣ እጅግ አሳዛኝ ሕይወት እመራ ነበር፡፡አንድ ቀን አንድ ቆንጆ ሞዴል ሴት ስለ እግዚአብሔር አወራችኝ፡፡አንዳንድ የጸጉር ሥራዎችን እንድሠራ ሥራዎችን እያገኘች ትጋብዘኝ ጀመር፡፡እንዲሁም ወደ እርሷ ቤተ ክርስትያን እንድሄድ ግድ ትለኝም ነበር፡፡ይህች ሴት የምትኖርበት አፓርትመንት ጸጉር ለመሥራት ሄጄ “Danny, the day you call the name of Jesus, you will be set free” (የኢየሱስን ሥም በጠራህ ቀን ነፃ ትሆናለህ) ብላ በሚገርም መታመን ልቤ ላይ የማልረሳው ቃል ጣል አረገችብኝ፡፡ይህች ሴት ለብዙ ጊዜ ስለ ጌታ ብትነግረኝም ሁኔታዬ ባሰና ራቅኋት፡፡

የምወስደው አንደንዛዥ ዕፅ መጠን ከቀን ወደ ቀን እየበዛ ከጎዳና እየወጣሁ፣ራሴን እየጣልሁና ገቢዬ እየቀነሰ መጣ፡፡የቤት ኪራይ መክፈል አቃተኝ፡፡ዕዳ ተደማመረብኝ፡፡ስለዚህም ኪሴ የነበሩትን ለክፍያ የምጠቀምባቸውን ካርዶች ማለትም መታወቂያዬን፣ፓስፓርቴን፣የምገበይባቸውን የባንክ ካርዶቼን ወዘተ ቀዳድጄና የምኖርበትን ለቅቄ ጎዳና ላይ ወጣሁ፡፡የጎዳና ተዳዳሪም ሆንሁ፡፡ሁልጊዜ ከእንቅልፌ ስነሳ፣ራሴን እጠላ ነበር፡፡መኖርም አስጠላኝ፡፡ሁልጊዜ ከተኛሁበት ስነሳ ሁለት ጥያቄዎች ነበሩኝ፡-
• የት ነው ለቀኑ አደንዛዥ ዕፅ የማገኘው ?
• ዕፁን ለመግዛትስ ገንዘቡን ከየት ነው የማገኘው?
አንድ ጊዜ የጥንት ወዳጄ ጋ ደውየላት ያቺ ሞዴል እንደምትፈልገኝ አበሰረችኝ፡፡እርሷም የጸጉር ሥራ እንድሠራላት ፈልጋ ነበር የጠራችኝ፡፡የምትኖርበት አፓርትመንት እንደደረስሁ የሥራውን ቀብድ እና መጽሐፍ ቅዱስ ሰጠችኝ፡፡የሚገርመው ከአፓርትመንቷ ወዲያው እንደ ወጣሁ ነበር መጽሐፍ ቅዱሱን የሸጥሁት፡፡

ከዚያማ ችግሬ እየባሰ፣ውስጤ ስለ እኔ የሚያወሩና የሚከራከሩ ሁለት ሰዎችን እሰማ ጀመር፡፡በዚህም ምክንያት ጭንቀቴ ባሰ፡፡መንገድ ላይ የሚራመድ እንስሳ ሆንሁ፡፡አካላቴ ቆሳሰለ፣ልብሴ በላዬ ላይ በሰበሰ እናም በቁሜ በከትሁ፡፡ የጉበት በሽታ ያዘኝ፡፡መቆም ሲያቅተኝና ልወድቅ ትንሽ ሲቀረኝ ወደ አቅራቢያው ሆስፒታል ሄድሁ፡፡ሆስፒታል እንደ ደረስሁ፣ነርሶቹ አስተኙኝ፡፡ወዲያው እንዳስተኙኝ መድሐኒቶች ሰጡኝ፡፡የተሰጡኝ መድሐኒቶች አስተኝተውኝ ስለ ነበር ከእንቅልፌ ስነቃ፣እነዛ ድምፆች አእምሮዬ ላይ ይንጫጩ ጀመር፡፡ያኔ ሞቴን ነበር የመረጥሁት፡፡በመስኮት ዘልዬ ራሴን ለማጥፋት ሞከርሁ፡፡ነገር ግን የተኛሁበት አጠገብ የነበረው የመስኮት መስታወት በብረት የታጠረ ነበር፡፡

በሚቀጥለው ቀን ሆስፒታል ውስጥ ሳለሁ ሰው የተናገረኝን ያህል የሚሰማ አንድ ሹክሹክታ ድምፅ ሰማሁ፡፡ድምፁም ያ ሞዴሏ ከአመታት በፊት የተናገረችኝ ቃል ነበረ፡፡እንዲህ ነበር የሚለው፡-

“The day you call on the Lord, He will set you free”(ጌታን የጠራህ ቀን ትድናለህ)

ይህንን ድምፅ ሌሎች የምሰማቸው ድምፆች ሊውጡት ሞከሩ፡፡ሊውጡት ግን አልቻሉም፡፡ያ ሹክሹክታ ከመላዕክት ይሁን ከመንፈስ ቅዱስ ኩልል ያለና ልዩ ድምፅ ነበረ፡፡ቀጥዬ
“እባክህ ጌታ ሆይ እርዳኝ”
“አንተ ብቻ ነህ ተስፋዬ ኢየሱስ” እያልኩ አለቀስሁ፡፡ከዚያማ እነዚያ የሚረብሹኝ ድምፆች ሁሉ ጠፉ፡፡ፍርሃቴና ሐዘኔ ሁሉ ሸሹ፡፡በውጪ ምንም የተለወጠ ነገር ባይኖርም፣ኃይለኛ መለኮታዊ ለውጥ ውስጤ እንደ ገባ ታወቀኝ፡፡

ከሆስፒታ ከወጣሁ በኋላ ክብደቴ እየጨመረ፣ሰውነቴ እየተመለሰ መጣ፡፡የቆዳ ቁስሎቼ ሙሉ በሙሉ ዳኑ፡፡መጽሐፍ ቅዱስን በኃይል ማንበቤን ተያያዝሁት፡፡ከዚያም በመንፈሳዊ ሕይወቴ እየበረታሁ ሄጄ ባንድ ባካባቢዬ የታወቀ ትልቅ ቤተ ክርስትያን በዚህ ሰዓት የአምልኮ መሪ ነኝ፡፡ደጋሜ ደጋግሜ የምዘምረው ዝማሪዬም፡ ፡-
“God is Still Doing Great Things!”(እግዚአብሔር ዛሬም ትልቅ ሥራን ይሠራል!)

No comments:

Post a Comment