የቦኒ መለኮታዊ ፈውስ
ምንም እንኳ ከሕጻንነቴ ጀምሮ ጌታን ብወደውም፣እንዳለ ቤተሰቤ የአደንዛዥ ዕፅ እስረኞች እና የአእምሮ በሽተኞች ነበሩ፡፡ከዚህም የተነሣ ብዙ መከራዎችን አሳልፌአለሁ፡፡
ሬይድ የሚባል ቴክሳስ እስር ቤት ውስጥ የሚኖር እስረኛ አውቅ ነበር፡፡ይህ ሰው የክርስቶስ ብርሃን ልቤ ላይ እንዲፈነጥቅ ያደረገ ባለውለታዬ ሰው ነው፡፡ሬይድ በዘመዴ በኩል ነው ያወቀኝ እንጂ በአካል ተገናኝተን አናውቅም፡፡ነገር ግን በስልክ ብዙ ጊዜ አውርተናል፡፡
አንድ ሌሊት ብዙ አደንዛዥ ዕፅ ወስጄ ልሞት ምንም አልቀረኝም፡፡ልቤ እንደ ፈረስ ይጋልብ ነበር፣እንዳውም ከደረቴ ወጥቶ ሊሄድ ምንም የቀረው አይመስልም ነበር፡፡ራሴን ልስት ጥቂት ነበር የቀረኝ፡፡በዛ አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ሆኜ፣ድንገት የሰዎች ድምፅ እሰማለሁ፡፡ሰዎቹ እየጸለዩልኝ እንዳለ ነበር የተረዳሁት፡፡እንዳውም እጃቸውን ጭነው እንደሚጸልዩኝ ነበር ይሰማኝ የነበረው፡፡
በሚቀጥለው ቀን ትንሽ ደህና ስሆንና ልቤ ሲመለስ፣አንድ ለረጅም ጊዜ ያላገኘኋት ዘመዴ ጋ ደወልኩ፡፡እስር ቤት ስላለው ሬይድ አነሳሁላት፡፡ስለ ሬይድና ባለፈው ምሽት ስላሳለፍኩት ነገር ልነግራት አልፈለግሁም ነበር፣ነገር ግን ከአፌ አፈተለከና ነገርኳት፡፡ካዳመጠችኝ በኋላ “ትናንትና ሬይድና በእስር ቤት ያለው የጸሎት ጓድ ላንቺ እየማለዱ እንደ ነበር አላወቅሺምን?” አለችኝ፡፡እጅግ ገረመኝ፡፡
ይህች ዘመዴ ባለፉት ዘመናት ደጋግማ “ቦኒ፣ሬይድ የቴክሳስ እስር ቤት እስረኛ ቢሆንም በዓለም ላይ እንደ እሱ ነፃ ሰው የለም” ትለኝ ነበር፡፡ይሄ አባባሏ ወደ አእምሮዬ ሲመጣ በኃይል ይገርመኝ ነበር፡፡ “በእስር ቤት ውስጥ ያለ ሰው እንዴት ነፃ ሊሆን ይችላል?” እያልሁ እራሴን ስጠይቅ ነው የኖርሁት፡፡ “ታዲያ ለምንድነው እኔ በነፃው ዓለም እየኖርሁ፣የእስረኛ ኑሮ እየኖርሁ ዕድሜዬን የምጨርሰው?” ብዬም ራሴን መጠየቅ ጀመርሁ፡፡ይህ ጥያቄ ማሰብ እንድጀምር ያደረገኝ ባለውለታዬ የሆነ ጥያቄ ነው ማለት እችላለሁ፡፡
ሁኔታዬም እየባሰ ሄደ እንጂ ምንም ለውጥ አልነበረኝም፡፡አንድ ቀን ፊቴን በመስታወት እያየሁ፣እራሴን በኃይል ጠላሁት፡፡መስታወቱን መሰባበር ፈለግሁ፡፡ “እግዚአብሔር ሆይ እንደዚህ ዓይነት አስጠሊታ ሰው ነኝ እንዴ?” ብዬም ጠየቅሁት:: ድንገትም እግዚአብሔር ከዚህ በፊት በደህናው ጊዜ አዘጋጅቼው የነበረውን የትምሕርት ማስረጃዬን(resume) ወደ አእምሮዬ አመጣው፡፡ይህንን የትምሕርት ማስረጃዬን “ሄዶ የሚሳካለት/ go-getter” የሚል ስም ሰጥቸው ነበር፡፡ “አሁን ላይ ያለሁት እኔ ያችን ሴት አይደለሁም፡፡እባክህ ያንን ማስረጃዬን አስታውስ፡፡እባክህ ያቺን ሴት አድርገኝ” ብዬ ተማጸንሁት፡፡
ከዚያ ጥያቄ በኋላም በኃይል እየባሰብኝ ስለሄደ ተስፋ ቆረጥሁኝ፡፡ለእግዚአብሔርም ቀነ ገደብ ሰጥቸው “በሰባት ቀን ውስጥ ሕይወቴን ካልለወጥህና ከዚህ ችግር ካላወጣኸኝ እራሴን አጠፋለሁ” አልኩት፡፡ምንም ለውጥ ሳይኖረኝ ስድስት ቀኑ አለቀ፡፡ያ ቀነ ገደብም ሊያልቅ አንድ ቀን ቀርቶታል፡፡እናቴን “ከዚህ በኋላማ ምንም ተስፋ የለኝም” አልኳት፡፡እናቴ ግን “የነገውን ቀን ብቻ ታገሺ፣ጌታ ችግሮችሽን ያነሳቸዋል” አለችኝ፡፡ እናቴ የተናገረችኝ ቃል የእግዚአብሔር ድምጽ እንደሆነ አስቤ አመንኳት፡፡የሚቀጥለው ቀን ከመኝታዬ ስነሳ፣አፌ ላይ የነበረው “የኛ እግዚአብሔር(our God)” የሚለው የታዋቂው ክሪስ ቶምሊን መዝሙር ነበር፡፡ይህን መዝሙር ስሰማ እጠላው ነበር፤አሁን ግን እጅግ ወደድሁት፡፡እራሴን የማጥፋት መንፈስና ሐዘን ከፊቴ ሸሹ፡፡እግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ቀንበሬን ሰበረልኝ፡፡ነጻ ሰው ሆንሁኝ፡፡ከባድ የሱስ ቀንበር እላዬ ላይ ነበር፡፡አሁን ግን በሰማይ እንደሚበሩ ወፎች ተለቅቄ የነጻነት አየር እየተነፈስሁ እገኛለሁ፡፡ስሙ ከዘላለም እስከዘላለም ይባረክ !!
No comments:
Post a Comment