Friday, October 31, 2014

የእግዚአብሔር ጉብኝት




  Nov 1, 2014          

                             የእግዚአብሔር ጉብኝት

መነቃቃት‹‹Revival›› ማለት በውጤት ደረጃ የሞተ ነገር ወደ ሕይወት መመለሱን ያመለክታል፡፡በሌላ በኩል ደግሞ መነቃቃት ማለት ባጭሩ ‹‹እግዚአብሔር ወደ ግለሰብ ወይም ወደ ጉባዔ መጣ››ማለት ሊሆን ይችላል፡፡በትንቢተ ዕንባቆ መጽሐፍ ‹‹እግዚአብሔር ከቴማን ቅዱሱም ከፋራን ይመጣል ›› (ዕንባቆ 3፡3) የሚለው ምንባብ በወደፊት ጊዜ ነው የተገለጸው፡፡በእንግሊዝኛ መጽሀፍ ቅዱሶች ውስጥ ግን “God came…” ብሎ በኀላፊ ጊዜ ነው ዐረፍተ ነገሩ የሚጀምረው፡፡ስለዚህም ዕንባቆ ምዕራፍ ሦስት ላይ ያለውን ቃል በመነቃቃት ዙሪያ የሚጽፉ የእግዚአብሔር ሰዎች ያዘወትሩታል፡፡ምዕራፉ ከቁጥር 4 ጀምሮ ‹‹እግዚአብሔር ሲመጣ›› የሚሆኑ ድንቅ ክስተቶችን እስከ ቁጥር 16 ድረስ በሰፊው ይዘረዝራልና በግላችሁ በሚገባ አንቡት፡፡እኔ ግን አለፍ አለፍ እያልኩ በግልጽ በሚገባ ሁኔታ ስዕላዊ በሆነ መንገድ የተገለጹትን መንፈሳዊ ለውጦች ለማስፈር እሞክራለሁ-  
  • ቆመ ምድርንም አወካት፤ተመለከተ አሕዛብን አናወጠ፤የዘላለም ተራሮች ተቀጠቀጡ፤የዘላለም ኮረብቶች ቀለጡ
  • በቃልህ እንደማልህ መቅሰፍትን አወጣህ ቀስትንም ገተርህ ምድርንም ሰንጥቀህ ፈሳሾችን አወጣህ
  • ተራሮች አንተን አይተው ተጨነቁ
  • ፍላጾችህ ከወጡበት ብርሃን የተነሣ ከሚንቦገቦገውም ከጦርህ ፀዳል የተነሳ ፀሀይና ጨረቃ በመኖሪያቸው ቆሙ
  • በምድር  ላይ በመትህ ተራመድህ አሕዛብን በቁጣ አሄድሃቸው
  • የኃጢአተኛውን ቤት ራስ ቀጠቀጥህ መሠረቱን እስከ አንገቱ ገለጥህ
  •  የአለቆችን ራስ በገዛ በትራቸው ወጋህ
  • ፈረሶችህን በባሕር ፣በብዙ ውኆችም ላይ አስረገጥግህ”
ከዚያም ዕንባቆ እግዚአብሔር እየመጣ እንደሆነ በመንፈሱ ስላወቀ እንዲህ ይላል፡-
‹‹እኔ ሰምቻለሁ ልቤም ደነገጠብኝ ከድምጹ የተነሳ ከንፈሮቼ ተንቀጠቀጡ መንቀጥቀጥ ወደ አጥንቶቼ ውስጥ ገባ በስፍራዬ ሆኜ ተናወጥሁ›› (ዕንባቆ 3፡16)
እግዚአብሔር በክብሩ በሰዎች መሃል ሲገኝ ብዙ መንፈሳዊ ነውጥ እንደሚሆን ከላይ ጀምሮ ያሉት ስዕላዊ አገላለጾች ፍንትው አድርገው ያሳዩናል፡፡የእግዚአብሔር መንፈስ ወርዶብኝ ከንፈሬ ተንቀጥቅጦና መናገር አቅቶኝ ያውቃል አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በርከት ያሉ ጊዜያት፡፡ለአገልግሎት መድረክ ላይ ወጥቼ ለተወሰነ ደቂቃ መስበክ እና ቃል ማውጣት አቅቶኝ ያውቃል፡፡ስለዚህ ይህ አገላለጽ በትንሹም ቢሆን ይገባኛል፡፡
መዝ 681-35 እግዚአብሔር ሲነሣ ወይም ክብሩን በሰዎች መሃል ሲገልጥ የሚሆኑ ድንቅ ነገሮች በስፋት ይዟል፡፡ይህ ክፍል ሲጀምር ‹‹እግዚአብሔር ይነሣ›› ብሎ ነው የሚጀምረው፡፡እናም እግዚአብሔር በክብሩ ሲገኝ የሚታዩ ነገሮችን ከዚህ ምንባብ አለፍ አለፍ ብዬ እዘረዝራለሁ (የራሴን አገላለጾች አልፎ አልፎ እንድጠቀም ይፈቀድልኝ)፡- 
  • ጠላቶቹ መግቢያ ነው የሚያጡት፤ሰም በእሳት እንደሚቀልጥ ይቀልጣሉ፤ጢስ እንደሚበንን ይበናሉ
  • ጻድቃን በእርሱ ፊት ሐሴት ያደርጋሉ በኃይልም ደስ ይላቸዋል
  •  እስረኞች ከወኅኒዎቻቸው ይፈታሉ
  • ምድር ትናወጣለች ሰማያት ያንጠባጥባሉ(የቃሉንና የመንፈሱ በህዝብ መሀል መዝነብን ነው የሚያሳየን)
  • የደከሙ ይበረታሉይጸናሉ
  • እግዚአብሔር ቃሉን ይሰጣል (የጠፋው ቃል ይገኛል) ብሎም ብዙ እንቆቅልሾ ይፈታል
  • በቤት የምትኖር ምንም ተሳትፎ ያልነበራት ሴት እንኳን ምርኮ ተካፈለች ይላል(የሚመጣውን የበረከት ሰፊነት ነው የሚያመለክተን)
  • ብዙ ሰዎች መንፈሳዊ ስጦታዎችን ይቀበላሉ(የጸጋ ስጦታዎችን)
  • ብዙ ሰዎች ከብዙ ጉድ ይድናሉይወጣሉም(ከሞት መውጣትም በእግዚአብሔር ነው የሚለው ይህንን ያመለክታል)
  • ኃይል ያለው ቃል ይለቀቃል
  • ብዙ ሰዎች ኃይልንና ብርታትን ይቀበላሉ
  • ጸሎት ይበዛል ወይም ጸሎት የጉባዔዎች መገለጫ ይሆናል(ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች የሚለው ይህንን ይጠቁማል)
ወገኖቼ የእግዚአብሔር መገኘት ብዙ አዳዲስ ነገሮችን ይዞ ይመጣልና፣እጅግ የሚጓጓ ጉዳይ ነው፡፡እዚህ ላይ ትልቅ ሊስተዋል የሚገባው ነገር የእግዚአብሔርን በጉባዔና በሕዝብ መካከል መገለጥ ሰው ሊያቅደውና ሊያደራጀው አይቻልም፡፡ቢሆንም ክርስትያን ወገኖች የሚከተሉትን ሁለት ግሩም መርሆዎች በልባቸው በመጠበቅ በበኩላቸው የሚገባቸውን ነገሮች ማድረግ አለባቸው የሚል አስተሳሰብ አለኝ፡፡እነዚህ ሁለት መርሆዎች የሚከተሉት ናቸው፡-
1.የእግዚአብሔር ሉአላዊነት (God’s sovereignity):-ጌታችን ይህንን ዓይነት ክስተት በወደደ ሰዓት ያደርጋል
2.የሰው ኃላፊነት (man’s responsibility):-ሰው ይህ ክስተት መቼ እንደሚመጣ ባያውቅም በብዙ ናፍቆትና በጋለ ጸሎት እየተጋ መጠበቅ አለበት
የእግዚአብሔር ጉብኝት ወደ እኛ እንዲመጣ ልንኮተኩታቸው የሚገቡ ሁለት ነገሮች የሚከተሉት ናቸው፡-
1.ከልብ የሆነና እውነተኛ መመለስ ያስፈልገናል (2 ዜና 713-15 ያንቡ)- ይህንን ቃል አንድ ቢል ብራይት የሚባሉ የእግዚአብሔር ሰው እንዲህ ብለውታል፡-‹‹the final and finished formula for revival››
2.መንፈሳዊ ጥማትና ራብ (ሉቃ 20-21)-አንድ ሰው በመነቃቃት ዙሪያ የጻፉት ጽሑፍ ላይ የማልረሳው ድንቅ ሁለት ነገሮች በልቤ ተጽፈው ቀርተዋል፡፡እነርሱም በእንግሊዝኛ ‹‹fasting and feasting›› ሲባሉ ትርጉማቸውም መጾምና የእግዚአብሔርን ቃል በብዛት መመገብ ነው፡፡ሰውየውም እነዚህ ሁለት ርምጃዎች መንፈሳዊ ጥማትንና ራብን ያቀጣጥላሉ ብለው ነው ጽሑፉ ላይ የሚያስገነዝቡት፡፡በግሌ የመንፈስ ራቤ ሲቀንስ እነዚህን ሁለት ነገሮች አብዝቼ አደርጋለሁ፡፡
ዊሊያም ቡዝ የሚባሉ ትልቅ የእግዚአብሔር ሰው አንድ የቤተ ክርስትያን አገልጋይ በቤተ ክርስትያኑ ለውጥ አጥቶ ሲያማክራቸው‹‹try tears/እስቲ እንባን ሞክር››አሉት ይባላል፡፡ይህ አባባል ባሰብኩት ቁጥር እንዴት እንደሚነካኝ አትጠይቁኝ፡፡እንባ ደረቀብን እንጂ መፍትሔው በጌታ ፊት አብዘተን በቅን ልብ መጮህ እንደ ሆነ ምንም አያጠያይቅም፡፡ቃሉ ‹‹የሚያስተውል እግዚአብሔርን የሚፈልግ እንዳለ ያይ ዘንድ እግዚአብሔር ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ›› (መዝሙር 14፡2) እንደሚል  የክብር ጌታ መሰጠታችንን አይቶ እንዲራራ እሱው ነው መደረግ ያለበት፡፡በመገኘቱ እንዲባርከንና እንዲያስደንቀን ለዚህ ለከበረ ነገር ዋጋ የሚከፍሉ ትጉ የሆኑና የጸሎት ሚስጥር የገባቸው ሰዎች በዚህ ዘመን በጣም ያስፈልጋሉ፡፡
3›የተሰበረ ልብ (ኢሳ 5714-15)-እግዚአብሔር የልብ መሰበርንና ትህትናን ይወዳልና በፊቱ ባዶነታችንና ያለሱ ምንም ማድረግ የማንችል መሆናችንን እውቅና እንድንሰጥ ይፈልጋል፡፡ከልብ በመሰጠትስጣችንን እንድናሳየው ይፈልጋል፡፡‹‹እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል›› (መዝ 34፡18) ስለሚል የልብ መሰበር በህይወታችን እንዲመጣ በፊቱ በትሕትና መቅረብ አለብን፡፡በልብ መሰበር የሚጠብቁትን ሰዎችን እግዚአብሔር እንደሚባርክ የሚያሳየው ‹‹ያድናቸዋል›› የሚለው ቃል ነው፡፡‹‹ያድናቸዋል›› ሰፊ የሆነ መንፈሳዊ በረከትን እንደያዘ ያስተውሏል፡፡
የእግዚአብሄር ጉብኝት ሲመጣ የሚታዩ ለውጦች - 
  •  በቤተ ክርስትያን ኃይል ይጨምራል
  • ተ ክርስትያን ትጠራለች
  • ቅድስና የሕይወት መሠረት ይሆናል
  • ንጹህ መለኮታዊ ፍቅር በአማኞች መካከል መታየት ይጀምራል
  • / በውጭው አለም ማህበራዊ ተጽዕኖን ማምጣት ትጀምራለች
ስለዚህ የእግዚአብሔር ጉብኝትና መልካሚቱ እጁ በትውልዳችን መካከል መጥታ ክብሩን እንድናይ ያለማሰለስና ያለመታከት እንጸልይ!