ጄምስ ዊልፎንግ እናቱ በጣም የሚወደውን ወላጅ
አባቱን መግደሏን ገና እንቦቀቅላ ሕጻን ሆኖ ነው የሰማው፡፡ጄምስ ሲናገር “ከቤት ልወጣ ልብሴን እያዘጋጀሁ ነበር፡፡ድንገት እናቴ
ቀልቧን ስታ ነው መሰል ሽጉጧን አንሥታ አባቴ ላይ አንድ አገር ጥይት አርከፍክፋ የገደለችው” ብሎ
መስክሯል፡፡
ጄምስ ያባቱን አስደንጋጭ ዜና ሲሰማ የነበረውን ሁኔታ በሚገባ ያስታውሰዋል፡፡ያ
ሁኔታ በአእምሮው ላይ ትልቅ ቁስል ጥሎበትም አልፏል፡፡በተጨማሪም የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳለ፣በቅርብ ቤተ ዘመዱ ተደጋግሞ ተደፍሯል፡፡ምስጢሩን
ካወጣ ሰውየው ሊገድለው እንደሚችል አስጠንቅቆታልና፣ለ 42 ዓመታት ለማንም ተንፍሶት አያውቅም፡፡
ይህ ሁኔታ ጄምስ ለእግዚአብሔርና ለሰዎች ያለውን ስዕል አበላሽቶበታል፡፡የሁልጊዜም
ጥያቄው “እግዚአብሔር ካለ ለምን እንዲህ እንድሆን ፈቀደ ?” የሚል ነበር፡፡አባቱ ስለሞተና እናቱ ወደ ወኅኒ ስለ ወረደች፣ጄምስ
እና ወንድሞቹ ወደ ሕጻናት ማሳደጊያ ተላኩ፡፡ነገር ግን ብዙ ሳይቆይ፣ጄምስ በሕጻናት ማሳደጊያው የጠበቀውን ክብካቤ ስላላገኘ ኮበለለ፡፡
ከማሳደጊያው ከኮበለለ በኋላ፣ስለ ምንም ማሰብ አቆመ፡፡ራሱንም ለመግደል በርካታ
የሕክምና እንክብሎችን ወስዶ ታሞ ነበርና፣ ሆስፒታል ውስጥ ትንሽ ጊዜ ተኝቷል፡፡ከሆስፒታል ከወጣ በኋላ ጎዳና ላይ መኖሩን ተያያዘው፡፡ከዚያማ
የአደንዛዥ ዕፅና የአልኮሆል ሱሰኛ ሆነ፡፡ይህንን ያደረገው የውስጥ ሕመሙን ለመርሳት ነበር፤ባሰበት እንጂ!
ጄምስ ባሪያ ያደረገውን ሱሱን ለማስተናገድና በገንዘብ ለመደገፍ ሲል፣ቤት ውስጥ
እየገባ መዝረፍ ጀመረ፡፡ከዝርፊያው ጋር በተያያዘ ሁለት ዓመት ታሰረና ተፈታ፡፡ለሁለተኛ ጊዜ ለ 14 ዓመት ተፈረደበትና ታሰረ፡፡የእስር
ጊዜውን ጨርሶ ከወጣም በኋላ በኑሮው ዘይቤው ምንም ለውጥ አልነበረውም፡፡
ጄምስ ይባስ ብሎ የኮኬይን ጥገኛ ሆነ፡፡የአልኮሆል አጠጣጡም ከወትሮው እየጨመረ መጣ፡፡አንድ ቀን ለ 48 ሰዓታት
ኮኬይንና አልኮሆል ደባልቆ ወስዶ ሲነቃ በኃይል አሞት ነበርና እጅግ መረረው፡፡በዚያ ብሶት እግዚአብሔርን “እንዲህ ሆኜ ወደ ፊት
መቀጠል አልፈልግም፡፡አንተ በውኑ እንደሚባለው ትልቅ ከሆንክ፣ለምን በእንደዚህ ዓይነት ሕይወት እንድቀጥል ፈቀድህ?” ብሎ ይጠይቃል፡፡ከዚያም
ሽጉጡን አንሥቶና ጭንቅላቱ ላይ ደቅኖ ለመተኮስ ቢሞክር አልሠራ ይለዋል፡፡ከዚያ በኋላ “ራሴን ሌላ ሙከራ አላደርግም” ብሎ ለራሱ
ይምላል፡፡
አንድ ቀን ጄምስ የሚሠራበትን የመሥሪያ ቤት ወለል እያጸዳ ሳለ፣የሥራ ባልደረባው
“ኢየሱስ ይወደኛል” የሚል መዝሙር ሲዘምር ይሰማዋል፡፡ከዚያም ባልደረባውን “እንዴት ኢየሱስ ይወደኛል? እስቲ ተመልከት፣ሕጻን ሳለሁ
በአዋቂ ቤተ ዘመድ ተደፍሬአለሁ፤እናቴ የምወደውን ወላጅ አባቴን በጥይት ገደለችው፡፡ራሴን ለመግደል ብዙ ሞክሬአለሁ፤ጥሩ ሕይወት
ኖሬ አላውቅም፡፡ዘራፊና ወንበዴ ነበርሁ፡፡ኢየሱስ ይወድሃል ነው የምትለኝ? እንዴት ሊወደኝ ይችላል? ብሎ ይጠይቀዋል፡፡
ባልደረባውም በጥሩ ሁኔታ ጥያቄውን ስለመለሰለት፣ልቡ በግሩም ሁኔታ ይነካል፡፡ከዚያም
ቤቱ ሄዶ ጮክ ብሎ “እግዚአብሔር ሆይ ከወደድከኝ እባክህ ወደ ሕይወቴ ና፤ኃጢአቴን ሁሉ ይቅር በለኝ” ብሎ ይጸልያል፡፡ልክ ያንን
ጸሎት ከጸለየ በኋላ እላዩ ላይ የነበረው ሸክም ሁሉ እንደተራገፈ ተሰማው፡፡ክንፎች ያሉትና መብረር የሚችል ያህል ነበር ስሜቱ፡፡ከዚያም
መጽሐፍ ቅዱስን ያለማሰለስ ማጥናቱን ተያያዘው፡፡ከጥቂናት በኋላ መሥሪያ ቤት ያዩት ሰዎች ለውጡን ዐይተው ሲጠይቁት “ኢየሱስን አገኘሁት፤ድኛለሁ”
ይላቸዋል፡፡
ከዚያም ጄምስ የውስጥ ሕመሙ ሙሉ በሙሉ ይድን ዘንድ የበደሉትን መማር እንዳለበት
ተረድቶ ነበርና፣ሕጻን ሳለ ክፉኛ የበደለውን ዘመዱን ስልክ ደውሎ “ምሬሃለሁ” አለው፡፡በተጨማሪም አብራው አንድ ቤተ ክርስትያን
የምታመልከውን እናቱን በሙሉ እንደማራት ነገራት፡፡በዚህ ሰዓት ባንድ ቤተ ክርስትያን በፓስተርነት ያገለግላል፡፡ግሩም የሆነ ትዳርም
ይዟል፡፡
ጄምስ “ወደ ኋላ ሳስበውና የአሁኑን ሕይወቴን ሳስተያየው፣ይህንን ያለሁበትን ለውጥ
ከጌታ በቀር ማንም ሊያደርግ እንደማይችል እመሰክራለሁ” ብሏል፡፡በተጨማሪም “ሕይወቴን በ1997 ዓ.ም ለጌታ ሳስረክብ፣ውስጤን የቀየረ
ብርሃን ወደ ልቤ ገብቷል፤ስሙ ለዘላለም ይባረክ” ብሎ መስክሯል፡፡
አዎ፣እውነት ነው! ጌታ ኢየሱስን የመሰለ አዳኝና ምስኪንን ከፋንድያ ማንሣት የሚችል
ብቃትና ችሎታ ያለው አምላክ አላየንምና ስሙ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይባረክ!!
No comments:
Post a Comment