Friday, July 31, 2015

ከአደንዛዥ ዕፅ እሥራት የተፈታችው ጄሲ



ስሟ ጄሲ ይባላል፡፡አደንዛዥ ዕፅ ስትወስድ በትንሹ አትረካትም፡፡ዕፆቹን በተለያዩ መልኩ ትወስዳቸው ነበር፡፡የ 16 ዓመት ልጅ ሆና እናቷ ለጭንቀት የምትወስዳቸውን እንክብሎች እና አልኮሆል መውሰድ የጀመረችው፡፡

ከሕፃንነቷ ጀምራ በእንጀራ አባቷ ብዙ በደል ደርሶበታል፡፡ይህ ሰው እናቷንም በኃይል ያንገላታት ነበር፡፡ሰክሮ መጥቶ እናቷ ላይ ሽጉጡን ደግኖ ሲያስፈራራት የሚያመሽበት ጊዜ ጥቂት አልነበረም፡፡

እናቷ ከዚህ ሰው ጋር የጄሲ ዕድሜ ገና አሥራ ውስጥ ሆኖ ሳለ ነበር የተፋቱት፡፡ሰውየው ከቤታቸው ከሄደ በኋላም ቢሆን፣ጄሲ ውስጥ ገና ያልጠገገ ቁስል ነበር፡፡ታዲያ ሕመሟን ለማስታገስ ስትል አልኮሆል አብዝታ መጠጣቷን ተያያዘችው፡፡ካሳለፈችው መከራ የተነሣ ጠባይዋ የተበላሸ ነበርና ከብዙ ሰው ጋር ያጣላት ነበር፡፡

እናቷ የምትወስደውን ዛናክስ በመዋጥና አልኮሆል በመጠጣት ራሷን ማደንዘዟን ቀጠለች፡፡ከዚያም ከበድ ወዳለ ሜት ወደሚባል መድኃኒት ዞረች፡፡ስለምንም ነገር ማሰብ አቁማ ነበር፡፡ባጭሩ ግዴለሽነት የተጠናወተው ሕይወት መግፋት ዕጣ ፈንታዋ ሆነ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አረገዘችና ወንድ ልጅ ወለደች፡፡ከዚህ በኋላ ለልጄ እኖራለሁ ብላ ለራሷ ቃል ኪዳን ገባች፡፡ቢሆንም እንደዚያ መሆን አልቻለችም፡፡ከዚያም ሁለተኛ ወንድ ልጅ ደገመች፡፡ሕይወቷ የበለጠ ተወሳሰበ፡፡ስለዚህ የበለጠ ተዝረከረች፡፡

ጄሲ የምትወስደውን የሜት መጠን ስለ ጨመረችው፣ሕይወቷን ተቆጣጠረው፡፡የበለጠ ሕይወቷ እንደ ዓይን ጠፋ፡፡አብሯት ይኖር የነበረው ጓደኛዋ አካሄዷን ዓይቶ ጥሏት ሄደ፡፡መንግሥት ልጆቹን ከሷ ነጥቆ እሱ እንዲያሳድግ አደራ ጣለበት፡፡

ሕይወቷ ከመበላሸቱ የተነሣ አጠገቧ የሚሆንና የሚያጽናናት ምንም ነገር አልነበረም፡፡ጓደኞቿ ትተዋታል፤ልጆቿም ከሷ ጋር የሉም፤ልቅሶ ብቻ!ከዚህም የተነሣ ጄሲ ሕይወቷ በኃይል አስደንገጣት፡፡ያለችበት የቁልቁለት መንገድ አንድ ቦታ ላይ መቆም እንዳለበት አሰበች፡፡

በዚህ አጋጣሚ እናቷ ጌታ ኢየሱስን መከተል ጀምራ ሕይወቷ ሰመረና በኃይል ተለወጠች፡፡ስለዚህ ጄሲን ደጋግማ ቤተ ክርስትያን እንድትሄድ ትጋብዛትና ትመክራት ጀመር፡፡የእናትየው ንዝነዛ ፍሬ አፈራና ጄሲ ሰክራም ቢሆን መሄድ ጀመረች፡፡እቤት በምትቆይበት ሰዓት ደግሞ ወደ አምላኳ አብዝታ መጮኽ ጀመረች፡፡ብዙ ሳይቆይ ጸሎቷ ተሰማና፣በሕይወቷ ተለማምዳው የማታውቃው ሰላም አጥለቀለቃት፡፡የሱስ እስራቶቿ ተበጣጥሰው ነፃ አየር መተንፈስ ጀመረች፡፡

ለውጡ እጀግ ደስ ስላሰኛት ሕይወቷን ሙሉ በሙሉ ለጌታዋ ለኢየሱስ አስረከበች፡፡ከዚያማ የመጀመሪያ ያደረገችው ነገር፣አብሯት ይኖር የነበረውንና የሁለት ልጆች አባት ጓደኛዋ ጋር መደወል ነበር፡፡ባለቤቷ መለወጧን ሲሰማ እጅግ ደስ አለው፡፡ከዚያም አብረው እንዲኖሩ ያቀረበችለትን ሐሳብ በደስታ ተቀብሎ አብረው መኖር ጀመሩ፡፡ድል ባለ ድግስም ተጋቡ፡፡

ዛሬ ጌታ አንድ ሴት ልጅ ጨምሮ ባርኳቸው፣አምስት ሆነው ባንድ ጣራ ስር አብረው በደስታ ይኖራሉ፡፡ ጄሲ ስትመሰክር “ሰዎች በዚህ ዘመን እግዚአብሔር ተዓምር አይሠራም እያሉ ሲያወሩ እሰማለሁ፡፡ኧረ ለመሆኑ ከዚህ በላይ ተዓምር ምንድነው?”

http://www.cbn.com/700club/features/amazing/

No comments:

Post a Comment