ባለ ብዙ ማስረጃ ሕይወት
ሰሞኑን
መጽሐፍ ቅዱስን ሳነብ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የነበሩትን፣ሐዋርያት ሆነው የተመረጡትን የጴጥሮስን፣የጳውሎስንና የሌሎችንም ምሥክርነት
እያነበብኩ ልቤ በደስታ እየፈነጠዘ ሐሤት አደርግ ነበር፡፡እኒህ አባቶች በቀጥታ ከራሱ የሰሙትንና ከርሱ ጋር በነበራቸው ትስስር
የዳሰሱትንና ያዩትን ነው የጻፉልን፡፡እነዚያን ማስረጃዎች በጥልቅ ብናስተውል መንፈሳዊ ሕይወታችን በኃይል ይለወጣል ብዬ አስባለሁ፡፡እኒያ ሐዋርያት ያለ ምንም መካከለኛ
ተቀባይና ተላላኪ ነው ከኢየሱስ ከራሱ በቀጥታ የተቀበሉትን የነገሩን፡፡ይሄ መቼም የሚደንቅ ነገር ነው፡፡እስቲ አንዳንድ ያስደነቁኝን
ጥቂት ነገሮች ላካፍላችሁ፡፡
የእግዚአብሔር ቃል ኢየሱስ ከትንሣኤው
በኋላ “አርባ ቀን እየታያቸው፣ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት እየነገራቸው በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ አሳያቸው”(ሐዋ.ሥራ 1፡3፤አጽንኦት በእኔ የተጨመረ)፡፡እስቲ
አርባ ቀን የሚለውንና በብዙ ማስረጃ የሚለውን በልባችሁ አስምሩልኝ፡፡አይደንቅም? አንድ ቀን ወይም ለጥቂት ጊዜ አይደለም የታያቸው-አርባ ቀን !ደግሞም በብዙ ማስረጃ ነው የታያቸው፡፡በግሌ የዛሬ 16 ዓመት ገደማ፣ለደቂቃዎች በራዕይ ዐይቼው ተደንቄ ቀርቻለሁ፡፡ይገርማል
እነዚህን ድንቅዬ ተደጋግመው ቢነበቡ የማይሰለቹ ማስረጃዎችና ልምምዳቸውን ነው በወንጌላት የጻፉልን፡፡
ከሚደንቀኝ ምንባብ ውስጥ ሌላውን
እነሆ(ሐዋርያው ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ ሲመሰክር የተናገረውን ነው)፡-
“እኛም በአይሁድ አገርና
በኢየሩሳሌም ባደረገው
ነገር ሁሉ
ምስክሮች ነን፤ እርሱንም
በእንጨት ላይ
ሰቅለው ገደሉት።እርሱን እግዚአብሔር በሦስተኛው ቀን አስነሣው ይገለጥም ዘንድ ሰጠው፤ ይኸውም ለሕዝብ ሁሉ አይደለም ነገር ግን በእግዚአብሔር አስቀድሞ የተመረጡ ምስክሮች ለሆንን ለእኛ ነው እንጂ፤ ከሙታንም ከተነሣ በኋላ ከእርሱ ጋር የበላን የጠጣንም እኛ ነን።ለሕዝብም እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ በእግዚአብሔር የተወሰነ እርሱ እንደ ሆነ እንመሰክር ዘንድ አዘዘን”(ሐዋ.ሥራ 10፡39-42))
አዎ፣ከትንሣኤው በኋላ
አብረውት አሳልፈዋል፡፡አብረውት በልተዋል፣ጠጥተዋልም፡፡ከአፉም ድንቅ የሆነውን ልብን በመለወጥ የሚታወቀውን ቃሉን
ተቀብለዋል፡፡ያንን ደግሞ ለእኛ አስተላልፈውት በሕይወታችን ድንቅ ሥራን እየሠራ ይገኛል፡፡ኢየሱስ ሦስቱ ሐዋርያትን(ጴጥሮስን፣ያዕቆብንና
ዮሐንስን)ብቻቸውን ወደ ረጅም ተራራ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸውም ተለውጦ ክብሩን ዐይተዋል(ማቴዎስ 17፡1-2 ያነቧል)፡፡ይህንን
ክስተት ሐዋርያው ጴጥሮስ በመጥቀስ፣የተሰጠን ወንጌል በእውነተኛ ምስክሮች ላይ የተደላደለ እንደ ሆነ እንዲህ ብሎ መስክሯል(እኔ
መቼም ይህንን ክፍል ስለምወደው ደጋግሜ ነው የማነበው)፡-
“ከገናናው ክብር በእርሱ ደስ
የሚለኝ የምወደው
ልጄ ይህ
ነው የሚል
ያ ድምፅ
በመጣለት ጊዜ
ከእግዚአብሔር አብ
ክብርንና ምስጋናን
ተቀብሎአልና፤እኛም
በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን።ከእርሱም ይልቅ
እጅግ የጸና
የትንቢት ቃል
አለን” (2 ጴጥሮስ
1፡16-19)
ይሄ አስደናቂ መልእክት ነው፡፡ከሰማይ የመጣውን ድምፅ በቀጥታ ነበር የሰሙት፡፡ጌታ ዐይኖቻችንን ከፍቶ ይህንን
መልእክት ብናየውና ብንረዳው እጅግ ሕይወትን የሚለውጥ ምስክርነት ሆኖ እናገኘዋለን፤ሐዋርያው እንደ ወረደ የተቀበለውን ነውና
የሰጠን! ደግሞም ያየነውና የዳሰስነው ብቻ በቂ አይደለም ይለናል፤ “ከእርሱም ይልቅ እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን’’ ነው
የሚለን-የማይናወጥ፣የማይሰበር፣የማይታጠፍ፣የማይለወጥ፣ሰባት ጊዜ እንደ ተጣራ ብር የነጠረ!
ሐዋርያው ዮሐንስም በግልጽ በሚገባን አገላለጽ እንዲህ ብሎ ነግሮናል(ይኼን ክፍልማ ሳነበው እጅግ ነው የሚገርመኝ፤ደጋግሜ
አንብቤው አልጠግብም)፡-
“ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን፣በዓይኖቻችን ያየነውን፣የተመለከትነውንም፣እጆቻችንም
የዳሰሱትን እናወራለን፤ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል፣እንመሰክርማለን፤ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን
ሕይወት እናወራላችኋለን”(ዮሐንስ 1፡1-2)
በዚህ ምንባብ ያሉትን አገላለጾች እስቲ ሰከን ባለ ሁኔታ አስቧቸው፤ልብ ነው የሚንጡት-ያየነውን፣የተመለከትነውን፣የዳሰስነውን፣ለእኛም
የተገለጠውን!! ቢሆንም እግዚአብሔር አምላክ በእነዚህ በምናነባቸው የጸኑ ምስክሮች ብቻ አልተወንም፡፡በተግባር ደረጃ ራሱን
በተለያየ መንገድ እየገለጠ አሳይቶናል፡፡ሲደግፈን፣በመከራ ውስጥ ጸጋ ሰጥቶ ሲያሳልፈን፣ልባችንን በመንፈሱ ኃይል በደስታና
በሐሤት ሲያሞቀውና አንችልም ያልነውን እንድናልፍ እያደረገ ቀጥተኛ የሆነ ምስክረነት በልባችን እየጻፈ ይገኛል፡፡ብርሃኑን በልባችን ያበራ እግዚአብሔር ስሙ ለዘላለም ይባረክ!!
No comments:
Post a Comment