Thursday, July 30, 2015

እነዚህ የደረቁ አጥንቶች በሕይወት ይኖራሉን?




 መንገድ ላይ እየሄድሁ ሳለ ድንገት “እነዚህ የደረቁ አጥንቶች በሕይወት ይኖራሉን?” የሚል መንፈሳዊ ድምፅ ወደ ውስጤ ዘልቆ እያሰብኩ የነበረውን ነገር አቋረጠኝ፡፡ጥያቄውን በውስጤ እንደሰማሁት ወዲያው ግርታና ግርምት እንደ ነበረኝ አልደብቃችሁም፡፡አሁን ግን በከፊልም ቢሆን የመጣው መልእክት ያለ ምክንያት አልመጣም ብዬ ስለማስብ ደስታን ፈጥሮብኛል፤ምንም እንኳ ጥያቄው እንዴት እንደሚመለስ ባላውቅም፡፡


እግዚአብሔርን ከኃያላኖች በላይና ልዩ የሚያደርገው የትንሣኤ አምላክ መሆኑ ነው፡፡አልቻልና አልታለፍ ያለውን ነገር ያስችላል፣ያሳልፋልም፡፡የከበደን ጉም ገፎ ደህና የሆነ ዘመንን ያመጣል፡፡ይህ ደግሞ በብዙዎች ዘንድ የተመሰከረ ነው፡፡የእስራኤል በ1948 መንግሥቷ ከፈራረሰና ከባዶ ነገር እውን ሆኖ መመለሱ አንዱ የዓለማችን ትንግርትና ይህንኑ የሚመሰክር ክስተት ነው፡፡
መቼም ስለ “የደረቁ አጥንቶች በሕይወት መኖር” ሳስብ የራሴ ሕይወት ነው ቶሎ ወደ አእምሮዬ የሚመጣው፡፡ተስፋ እንደሌለው፣ነፍስ ሊዘራ እንደማይችልና እንደ “ደረቀ አጥንት” ሕይወቴ ትርጉም አጥቶ የነበረበትን ዘመን አስታውሳለሁ፡፡በፍጹም ይሄ ዘመን ይመጣል ብዬ በሕልሜም ሆነ በውኔ አስቤ አላውቅም፡፡ያሳለፍኩት ጉስቁልና በዝርዝር ይተረክ ቢባል አንድ መጽሐፍ ብቻ የሚበቃው አይመስለኝም፡፡በዚያ የጨለማ ወቅት ብዙ ተስፋ መቁረጥ ነበር፤አንገት ማቀርቀር ነበር፤መሸማቀቅ ነበር፤ጭንቀትና ኀዘንም የማይለዩኝ የዘወትር ዕጣ ፈንታዎቼ ነበሩ፡፡እግዚአብሔር ይህንን በሁሉ መልኩ የሞተና ሙሉ በሙሉ የወደቀ ሕይወት ነው ትንሣኤ ሰጥቶ ይችን መልእክት ለምስክርነት የምጽፍላችሁ፡፡


መጽሐፍ ቅዱስን ሳነብ ከምደነቅባቸው ክፍሎች ሕዝቅኤል ምዕራፍ 37 ዋነኛው ነው፡፡ምክንያቱም ግልጽ ነው-ትንሣኤን ያውራልና ነው! ነቢዩ ሕዝቅኤል እንዲህ ብሎ ይናገራል፡-


“እግዚአብሔርም በመንፈሱ አወጣኝ፣አጥንቶችም በሞሉባት ሸለቆ መካከል አኖረኝ….በዙሪያቸው አሳለፈኝ፡፡እነሆም በሸለቆው ፊት እጅግ ብዙ ነበሩ፤እነሆም እጅግ ደርቀው ነበር” (ቁ.2)


ይህ ትንቢታዊ መልእክት የተጻፈው በምንም ተዓምር የኛ ነገር አበቃ ስላሉና በቃ አለቀልን ከዚህ በኋላ ትንሣኤ አናያም ብለው የደመደሙ እስራኤላውያንን አስመልክቶ ነው፡፡የነበሩበት የግዞትና የልቅሶ ጊዜ አንገሽግሿቸው በነበረበት ጊዜ የመጣ ትንቢት ነው፡፡ለመሆኑ ያንን ሁኔታና ጊዜ ዐይቶ ማንስ ትንሣኤን ያስባል ? በዚያን ጊዜ እነዚህ እስራኤላውያን “አጥንቶቻችን ደርቀዋል፣ተስፋችንም ጠፍቶአል፣ፈጸመንም ተቈጠርናል” (ቁ.11)ብለው ነበር፡፡ነገር ግን የመጣው ትንቢታዊ መልእክት እጅግ ተቃራኒ ነበር-ትንሣኤ(ቁ 12-14)!


አዎ፣ተስፋ መቁረጥ፣ፈጽሞ መውደቅ፣የኑሮ ትርጉም ማጣትና የሕይወት መድረቅ የሚያጋጥሙ ክስተቶች ናቸው፡፡አዎ፣የባዶነት ጊዜያትና የጭንቀት ጊዜያት ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ሕይወት እንደ “ደረቁ አጥንቶች” ትንሣኤ የሌለው እስኪመስል ድረስ፣ጣዕም የሌለው እስኪመስል ድረስ ጣዕም ሊያጣ ይችላል፡፡ቢሆንም ዋናው ቁም ነገር በዚህ ጊዜ ምን እናድርግ የሚለው ነው ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው፡፡


በዚህ ጊዜ ከምንም ጊዜ በላይ ወደ ጌታ አብዝቶ መጮኽና በፊቱ መሆን ያስፈልጋል(ለጊዜው ትርጉም ባይሰጥ እንኳን)፡፡የምሕረት አምላክ በደረቁ ነገሮቻችን ላይ ልምላሜና ትንሣኤ እስከሚያመጣ ድረስ በፊቱ መውደቅ ተፎካካሪ የሌለው ምርጫ ነው፡፡ነፍስን ሊያለመልም፣ሊያጽናና ሊያንጽ የሚችለውንና ልብን የሚያቀናውን ቃል በተጓዳኝ እያሰላሰሉ በፊቱ መሆን አስተዋይነት ነው ብዬ)አስባለሁ፡፡አዘውትሮ መጾም በግሩም ሁኔታ ሕይወትን ሲደግፍና በጌታ ላይ ያለን መጣበቅ ሲጨመር አይቼዋለሁና አዘውትሮ መለማመዱ ግሩም ነው ብዬ እመክራለሁ(ኢሳይያስ 58)፡፡


በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሆነን እየተጋን ስንጠባበቀው፣የፍቅር ጌታ በራሱ ሰዓት ሊያስደንቀንና ሊጎበኘን

  •     በድምፁ ይመጣል
  • ምሕረቱን ይገልጣል

  • በተዓምሩና በክብሩ በደረቁ ነገሮቻችን ላይ ይገለጣል

እናም  “የደረቁ አጥንቶች በሕይወት ይኖራሉ”(ቁ.6)


ስሙ ለዘላለም ይባረክ!

No comments:

Post a Comment