Wednesday, June 24, 2015

የዌንዲ ያልተጠበቀ ስብራትና የጌታ ትድግና



የዌንዲ ያልተጠበቀ ስብራትና የጌታ ትድግና

በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን? ስብራትን እንደ እሱ የሚጠግን፣ፈዋሽ አምላክ ከየት ይገኛል?

ስሜ ዌንዲ ብላይት እባላለሁ፡፡ትዝ ይለኛል ሰኔ 7 1986 ላይ ነበር ከኮሌጅ የተመረቅሁት፡፡ያንን ምሽት ቤታችን ካለው ገንዳ ከጓደኞቼ ጋር ስዝናና ቆይቼ፣ልብሴን ልለውጥ ወደ ቤት አመራሁ፡፡የቤቱን ደረጃዎች ጨርሼ ወደ መኝታ ቤቴ ልገባ ትንሽ ሲቀረኝ፣ፊቱ ላይ ጥቁር ጭንብል ያጠለቀ ሰው ትልቅ ቢላ ይዞ መኝታ ቤቴ አስገብቶ እንድቆልፈው አስገደደኝ፡፡ከዛም ወደ አልጋዬ ጐትቶና አስተኝቶ፣ለብዙ ሰዓታት እንደ ፈለገው ሲጫወትብኝ ቆየ፡፡ስለምነው የበለጠ ስለሚበሳጭ የሚለውን ከማድረግ በስተቀር ምንም ዕድል አልነበረኝም፡፡

መጨረሻ ላይ ጥሎኝ ከመሄዱ በፊት ይህንን ምስጢር ላንድ ሰው ብናገር፣ሊገለኝ እንደሚችል ዝቶብኝ ውልቅ ብሎ ሄደ፡፡ልክ እንደ ወጣ ለቤተ ዘመድና ለእጮኛዬ አሳውቄ፣ለፓሊስ ወዲያው አመለከትን፡፡በቂ ማስረጃም ለፓሊስ ሰጠሁ፡፡ከዛ አካባቢዬ በነበሩ ሰዎች የማጽናናትና የማበርታት ኃይል ቀለል ቢለኝም፣ከቀናት በኋላ ሌላ በሕልሜም በውኔም ያልጠበቅሁት ነገር ሆነ-በጭንቀት፣ፍርሃት፣ባዶነትና ደስታ ማጣት ተዋጥሁ፡፡

ሌሊት መተኛት አቃተኝ፡፡ደክሞኝ ከተኛሁ፣ድንገት ደንግጬ በቅዠት እነሣለሁ፤አዘውትሬ በሕልሜ ይኼ ሰው ጩቤ ይዞ ሲያስፈራራኝ አየው ነበረና፡፡በጭራሽ ብቻዬን ባዶ ክፍል ውስጥ መግባት አቃተኝ፡፡ፍርሃትና ጭንቀት ሙሉ በሙሉ ሕይወቴን ተቆጣጠረው፡፡ሕይወቴን እንደ ገና ለማቅናትና በሁለት እግሬ ለመቆም በማለም ቶሎ አገባሁ፡፡ኮሌጅ ገብቼም ሕግ ማጥናት ጀመርሁ፡፡ከውጪ ሁኔታዬ መልካም ቢመስልም፣በእግዚአብሔር ላይ እናደድ ነበር-መልስ ፈላጊ ነበርሁና፡፡እግዚአብሔር ላይ በቀጥታ “እጠላሃለሁ፤እንዴት እንደዚያ ዘግናኝ ነገር በአካሌ ላይ ሲደረግ ዝም አልክ?” ብዬ ደጋግሜ እጮኽ ነበር፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ጉዳዬን የያዙት ፓሊሶች “ለወንጀል ምርመራ የሰጠሽው ናሙና(DNA sample) ስለ ጠፋ፣ተጠርጣሪውን ለፍርድ ማቅረብ አንችልም”ብለው አረዱኝ፡፡በዚህ ሁኔታ እጅግ አበድሁ፣በገንሁም፡፡ቢሆንም በጥቂት ቀናት ውስጥ፣ይኼን ሰው መማር እንደሚገባኝ በውስጤ ተረዳሁ፡፡ስለዚህ መኝታ ቤቴ ተንበርክኬ እየጸለይኩ፣ “የደፈርከኝና ለዚህ ሁሉ መከራ ያበቃኸኝ ወንድም ሆይ፣ባለህበት ሙሉ በሙሉ ይቅር ብዬሃለሁ” ብዬ ስተነፍስ፣የተሰማኝ እረፍት ቀላል አልነበረም፡፡ኩንታል ሸክም ከላዬ ላይ እንደ ተራገፈ ነበር የተሰማኝ፡፡በተጨማሪም “የውስጥ ሰላሜን፣ማንነቴን፣ሕይወቴን፣ኑሮዬንና ግቤን አበላሽተሃል፤ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ምሬሃለሁ” ብዬ የውስጤን ብሽቀትና ምሬት አወጣሁት፡፡

ከዚያ ውሳኔ በኋላ፣ተዓምር ነው የሆነው፡፡በኃይል ቆሽሾ እንደ ታጠበ ሰው ነበር የቀለለኝ፡፡ፍጹም ነፃ ሆንኩ፡፡መንፈሴን ከፍታን ረገጠ፡፡ሰላምና ደስታ አጥለቀለቀኝ፡፡

የነበረኝ ምሬት ቢተንና ሰላምና ደስታ በልቤ ቢሰፍንም፣አንድ ገና ያልተወገደ ችግር ነበረኝ-ድንገት የሚከሰት ፍርሃት፡፡ፍርሃቴ ደግሞ በዙሪያዬ ያሉትን ሰዎችና ባለቤቴን ጭምር የሚረብሽ ስለ ነበር፣ገና ድሌ ሙሉ አልነበረም፡፡ከዚያም ጉዳዬን በግልጽ ለፓስተሬ ዘክዝኬ ነገርኩት፡፡ፓስተሩም ሰዎችን የመምከር ጸጋ ነበረውና፣ሕይወቴን የሚለውጡ ግሩም ምክሮችና ትምህርቶችን በሚደንቅ ሁኔታ ለገሰኝ፡፡ከጎኔ ሆኖ ይደግፈኝም ጀመር፡፡የእግዚአብሔርን ቃል እንዳጠና መክሮኝም ስለ ነበር፣መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ጉድ አጠናው ጀመር፡፡ውዬ አድርበት ነበር ማለት ይቀላል፡፡ከዚያም ያ የፍርሃት ባርነት፣እንደ ጥንቸል ከፊቴ ላይመለስ ሸሸ፡፡ነፃ ወጣሁና በድፍረት ተሞላሁ-ለሌሎችም እስከሚተርፍ ድረስ፡፡

በአሁኑ ሰዓት ልበ ሙሉ ሚስት፣እናትና የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ ነኝ፡፡ማቄን ቀድዶ ደስታንና ድፍረትን ያስታጠቀኝ የፍቅር አምላክ ይመስገን፡፡ስሙ ለዘላለም ይባረክ!

No comments:

Post a Comment