Saturday, June 6, 2015

ሕይወቱ በእግዚአብሔር ጸጋ የተለወጠው የባንክ ዘራፊ

               
በራሴ መንገድ ሕይወትን መምራቱ ጥፋትና ውድቀት እንደ ሆነ የሊቃውንቶች ዓይነት ጥናት አላስፈለገኝም፡፡በ2009 ዓ.ም በሞቃትማው የበጋ ወቅት ላይ ነበር ከአምስት የባንክ ዝርፊያዎች ጋር በተያያዘ፣ለ 11 ዓመት ከታሰርኩበት እጅግ ከባድ እስር ቤት የተፈታሁት፡፡

አንባቢዎችን ምናልባት ሊያስደነግጥ የሚችለው ነገር፣ቤተ ክርስትያን ያስተዳድሩና ይመሩ የነበሩ ክርስትያኖች ቤተሰብ ውስጥ ማደጌ ነው፡፡በትምህርት ቤት የነበረኝ የቅርጫት ኳስ ሙያዬና የኮሌጅ መማር ዕድሌ ሲበላሽ፣በአደንዛዥ ዕፅ እስራትና ድብታ(depression) ለዓላማ የለሽ ኑሮ ተጋለጥሁ፡፡እንደ እኔ ዓላማ ያልነበረው ጓደኛዬ ባንክ እንዝረፍና ገንዘብ እናግኝ ብሎ ሲያማክረኝ፣እንደ በጎ ነገር ወዲያው ነበር የተስማማሁት፡፡

አምስት ባንኮችን በውስጣቸው ተቀጥረው የሚሠሩ አገልግሎት ሰጪዎችን እያስፈራራንና እያስደነገጥን ዘረፍን፡፡ልክ እንዳልሆንኩ ግን በሚገባ ይገባኝ ነበር፡፡ኦማሃ የሚባል ሆቴል ውስጥ በፓሊስ እስክያዝ ደረስ ዝርፊያውና ውንብድናው ቀጠለ፡፡ብዙ ሳልቆይ ተይዤ በፍርድ ቤት ዳኛ ፊት እግሮቼ እየተብረከረኩ፣መንፈሴም በኃይል እየተጨነቀ የቆምኩበት ጊዜ እጅግ ከባድ ነበር፤ምን ጊዜም አይረሳኝም፡፡በዚያን ጊዜ 23 ዓመቴ መሆኑ ነው፡፡

ወኅኒ ቤት እጅግ ከባድና አስጨናቂ ቦታ ነው፡፡ታዲያ ካጠገቤ ያሉትን ታራሚዎች ለመራቅ ስል፣በወኅኒ ቤት ውስጥ ሥራ መሥራት ጀመርሁ፡፡ሥራ በማልሠራበት ጊዜ ደግሞ ከተለያዩ መጽሐፍቶች ሕግን መማርና ማጥናት ጀመርሁ፡፡በዚህ ትጋቴ ያገኘሁት አስደናቂ ነገር፣የጓደኞቼን ሕጋዊ እንቆቅልሽ መፍታት መቻሌ ነበር፡፡በእስር ቤት ያሉ ጓደኞቼ እስከ ዋናው ፍርድ ቤት ድረስ ጉዳያቸውን እንዲታገሉ መርዳቱ አንዱ ዋና ሥራዬ ሆነ፡፡ብዙዎችንም ረዳሁ፡፡ከዚህም የተነሣ እስር ቤት ውስጥ ያሉ ጓደኞቼ “የእስር ቤት ጠበቃ” ብለው ስም አወጡልኝ፡፡

አኒ ገና የትምህርት ቤት ጓደኛዬ ነበርችና ደብዳቤ እየላከች፣እየደወለችና እየጐበኘችኝ በጣም ተቀራረብን፡፡ብዙ ሰዎች እንደ እኔ ያለውን ሰው ይገፋሉ፡፡ነገር ግን የኔ ቤተሰቦች ይጸልዩልኝ ነበር፡፡እናቴ መንፈሳዊ መጽሐፍትን ትልክልኝ ነበር፤እባክሽ አትላኪልኝ እያልኩ ተስፋ ባስቆርጣትም፡፡ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በመጽሐፎቹ እየተሳብኩ ማንበብ ጀማመርኩ፤ነገር ግን ምነው እግዚአብሔር ረሳኝ እያልኩ መስጋቴ አልቀረም፡፡ወደ እሱ ለመመለስም ምንም የውስጥ ዝግጁነት አልነበረኝም፡፡ይህ ሁኔታዬ የበለጠ ፈራ ተባ አደረገኝ፡፡

ብዙ ጠዋቶችን ሮበርት የሚባል ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዘ ለ 20 ዓመት የታሰረ ባልደረባዬን እጐበኝ ነበር፡፡ሮበርት በብዙ ጉዳዮች መሪር ሕይወት ነበረው፡፡አንድ ቀን እንደ ልማዴ ልጐበኘው ስሄድ፣ክፍሉን እያፀዳ ሲያሸበሽብ አገኘሁት፡፡ “ዛሬ ምን አገኘህ አልኩት?” ብዬ ስጠይቀው ፣ “ጌታን አገኘሁ” ብሎ መለሰልኝ፡፡ውስጡ ስለተለወጠ፣በጥቂት ቀናት ውስጥ እንዲታሰር የመሰከረበትን ወኅኒ ቤት የሚገኝ ታራሚ ማረው፡፡ሌላው ገራሚ ነገር፣ከትንሽ ጊዜ በኋላ ተፈትቶ ከቤተሰቡ ጋር ተቀላቀለ፡፡ከዚያም እየተመላለሰ በወኅኒ ቤት ውስጥ የነበረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይመራ ጀመር፡፡

በ2009 ዓ.ም ሥራ በማይገኝበትና ከባድ የኢኮኖሚ ችግር (recession)በነበረበት ጊዜ ተፈታሁ፡፡ቢሆንም በእግዚአብሔር ምሕረት ፣በጥቂት ጊዜ ውስጥ የጠበቆች ረዳት ሆኜ ተቀጠርሁ፡፡ወዲያውም ከአኒ ጋር ተጋባን፡፡በጋብቻችን ክብረ በዓል ላይ ማርቲ ባርናርትን መልእክት  አቅራቢ እንዲሆን ጋበዝነው፡፡አኒ ግን ብዙም አልተስማማችም ነበር፡፡የቅድመ-ጋብቻ የምክክር አገልግሎት ከሰጠን በኋላ ግን እጅግ በደስታ መስማማቷን ገለፀችልኝ፡፡

የመጀመሪያው የምክክር ክፍለ ጊዜ በሕይወቴ እጅግ የማይረሳ ሆነና አለፈ፡፡ማርቲ ስለ ኢየሱስ የምናውቀውን ነገሮች ጠያየቀን፡፡ከዚያም ስለ ጸጋ በሚገባን መንገድ አስተማረን፡፡እንዲያው በነፃ የምንቀበለው ስጦታ እንደ ሆነ ገለፀለን፡፡ባቀረበልን መልእክት ልቤ በኃይል ተነክቶ፣ “ለመሆኑ አምስት ባንክ የዘረፈ ሰው ይማራል ነው የምትለኝ?” ብዬ ጠየቅሁት፡፡ውስጤ በግትርነትና በራስ ወዳድነት ተሸብቦ ነበርና አስቸግሬው ነበር፡፡እሱም ኤፌሶን 1፡7-8 ያለውን በማብራራት የእግዚአብሔር ጸጋ በብቃት እንደሚችል በተረጋጋ ሁኔታ አበሰረኝ፡፡ክፍሉ እንዲህ ይላል፡-

“ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፤በጸጋ ድናችኋልናበሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፣ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን።ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም” (ኤፌሶን 2፡5-8)

ክፍሉን ደጋግሜ ሳነበውና ሳሰላስለው፣ውስጤን ገለባበጠው፡፡አእምሮን የሚያልፍ ሰላም አጥለቀለቀኝ፡፡አምላኬን በብዙ የደስታ እንባ እያመሰገንሁ ውዬ ማደር ሆነ፡፡ነፍሴ በደስታና በሐሤት ዘለለች፡፡የእኔን የሕይወት ለውጥ አይታ አኒ ሕይወቷን ለኢየሱስ አስረከበች፡፡ብዙ ሳንቆይም ግሩም በሆነ ሥነ-ሥርዓት የውኃ ጥምቀት ተጠመቅን፡፡አሁን ለዚህ ለከበረ ጸጋ እጅ ወደ ላይ ካልኩ አምስት ዓመት ሆኖኛል-አምስት የነፃነትና የእፎይታ ዓመት! ከአኒ ጋር ጥቂት ዓመት አብረን ከኖርን በኋላ፣ጌታ ጸጋ የሚል ስም ያወጣንላትን ውብ ቆንጆ ልጅ ሰጥቶ ባረከን፡፡

በዚህ ሰዓት በሕግ ትምህርት ከታወቀ ትምህርት ቤት ዲግሪዬን ሠርቻለሁ፡፡እግዚአብሔር ሕይወቴን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ባርኮታል፡፡መረዳት ከምችለው በላይ ሕይወቴን አለምልሞታል፡፡ስሙ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይባረክ!

“በሰማይና በምድር የተዋረዱትን የሚያይ፤ከአለቆች ጋር ከሕዝቡም አለቆች ጋር ያኖረው ዘንድ ችግረኛን ከመሬት የሚያነሣ፣ ምስኪኑንም ከፋንድያ ከፍ ከፍ የሚያደርግ……….ሃሌ ሉያ!” (መዝሙር 113፡6-9)




No comments:

Post a Comment