Saturday, March 21, 2015

የእግዚአብሔር ቃል ይሠራል

የእግዚአብሔር ቃል ይሠራል


የእግዚአብሔር ቃል እጅግ ብዙ ሥራን ይሠራል፡፡የጌታ መንፈስ በነቢዩ ኢሳይያስ ከእኔ የሚወጣው ቃል፣መንፈስ የሆነው ቃል፣ወይም የጊዜው ቃል፣የምሻውን ያደርጋል፣የላክሁትን ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም (ኢሳይያስ 5510-11) ብሎ ተናግሯል፡፡እውነት ነው መንፈስ የሆነው ቃል ከእግዚአብሔር አፍ ይውጣ እንጂ በከንቱ አይወድቅም፡፡

የዕብራውያን ጸሐፊ የእግዚአብሔርን ቃል ሲገልጸው የሚሠራ እና ሁለት አፍ ካለው ሰይፍ ይልቅ የተሳለ እና ወደ ጠለቀው ማንነታችን ዘልቆ ልባችንን እንደሚመረምር እና በእርሱ ፊት ሁሉ ነገር የተገለጠ እና የተራቆተ (ዕብራውያን 412-16) እንደ ሆነ ይናገራል፡፡አዎ ትክክል! የእግዚአብሔር ቃል የሚሠራ ነው፣ነፍስን ይመልሳል፣ሰላምንና ደስታን ይሰጣል፣ከብዙ ጥፋት ያወጣል ያድናልም፣መንገድንም ያቀናል፡፡

በምሳሌ መጽሐፍ ላይ ቃልም በጊዜው ምንኛ መልካም ነው፤በታች ካለው ከሲኦል ያመልጥ ዘንድ የሕይወት መንገድ አስተዋዩን ሰው ወደ ላይ ይወስደዋል (ምሳሌ 1523-24) የሚል ቃል እናገኛለን፡፡ ቃልም በጊዜው ምንኛ መልካም ነው የሚለው አሳብ በጊዜው ወይም በሚፈለግበት ሰዓት በእግዚአብሔር መንፈስ ስለተነገረ የእግዚአብሔር ቃል ነው የሚጠቁመው፡፡የእንደዚህን ዓይነት ቃል ውድነትና ተፈላጊነት ሲገልጽ ምንኛ መልካም ነውይለዋል፡፡ማለትም ሥራን የሚሠራ፣ለውጥን የሚያመጣ፣ካለንበት ማጥ የሚያወጣ ባለ ውለታ የሆነ ቃል እንደ ሆነ ነው የሚያሳየን፡፡ይህ ቃል በታችን ካለው ከሲኦል ያመልጥ ዘንድ የሕይወት መንገድ አስተዋዩን ሰው ወደ ላይ ይወስደዋልከሚለው አሳብ ጋር ተያያዥነት ያለው ይመስላል፡፡አዎ! ይህ የጊዜው ቃል ነው ከሲኦል የሚያስመልጠው፡፡ ሲኦልየሚለው ቃል ማንኛውንም እኩይ የሆነ ነገርን ሁሉ ይወክላል፡፡ ወደ ላይ ይወስደዋል  የሚለው አሳብ ደግሞ መንፈስ የሆነው ቃል እጅግ ብርቱ እንደ ሆነና ከብዙ ጉድ ማውጣት እንደሚችል ነው የሚያሳየን፡፡

በግሌ የቃሉን ኃይል በሕይወቴ አይቼዋለሁ፡፡መንፈስ የሆነው ቃል ከብዙ ጉድ ሊያወጣን እንደሚችል በድፍረት መናገር እችላለሁ፡፡በተግባር ደረጃ ይህ የሕይወት ቃል ወደ ውስጤ በመግባቱ ከመጠጥ፣ከጫት፣ከሲጋራ ሱስ እና ብልሹ ከሆነ ማኅበራዊ ሕይወት መንጭቆ አውጥቶኛል፡፡እጅግ በጣም ይገርማል፡፡እላዬ የነበረው የሱስ ቀንበር ቀላል አልነበረም፡፡እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤ይህ ኃይል ያለው ቃል ነፃ አድርጐኝ፣ተለቅቄ ያለ ምንም ባርነት እየኖርኩ እገኛለሁ፡፡ወደ እሱ ከመጣሁ በኋላም ተነግሮ የማያልቅ ሥራን በሕይወቴ እየሠራ ይገኛል፡፡

ይህ የሚሠራ ቃል የጠላትን ተግዳሮት እንድናሸንፍ ያደርገናል፤መጽሐፉ እንዲህ ይላልና፡-“ኃያል ሆይ፣ፍላጻዎችህ የተሳሉ ናቸው፤እነርሱም በንጉሥ ጠላቶች ልብ ውስጥ ይገባሉ፤አሕዛብም በበታችህ ይወድቃሉ(መዝሙር 455):: ይህ ምንባብ የሚናገረው እንደ ተሳለ ፍላጻ፣በመንፈስ የሚነገር ቃል የሚያመጣውን ውጤት ነው፡፡አዎ! በሕይወታችን መንፈስ የሆነው ቃል ማንኛውንም ተግዳሮት ጥሶ የመግባትና ነገሮችን የመለወጥ ችሎታ አለው፡፡ነገር ግን እዚህ ሊታሰብ የሚገባው ጉዳይ፣ወደ ውስጣችን በተለያየ መንገድ የሚገባው ቃል እንዴት ይሳላል የሚለው ነው፡፡በጆሮአችን የምንሰማቸውና በዓይናችን የምናነባቸው የእግዚአብሔር መዛግብቶች፣ወደ ልባችን የሚያልፉት በአእምሮአችን በኩል ነው፡፡ለቃሉ ያልተከፋፈለ ልብን በመስጠት ስናጠናውና ስናሰላስለው፣ብሎም በተግባር ደረጃ ስንለማመደው፣በልባችን ጽላት ላይ በማይረሳ መልኩ ይጻፋል፤ከሕይወታችን ጋር ይዋሃዳልም፡፡ቃሉ በውስጣችን በእምነት ሲዋሃድ ተሳለ ማለት ይቻላል፡፡

ቃሉ የሚሳልበትን ሂደት ሐዋርያው ዮሐንስ ሲናገር፣ከመልአኩ እጅ ታናሺቱን መጽሐፍ ወስጄ በላኋት፣በአፌም እንደ ማር ጣፋጭ ሆነች፣ከበላኋት በኋላም ሆዴ መራራ ሆነ (ራእይ 1010) ብሎ ገልጾታል፡፡ትክክል! ቃሉ የተሳለና ውጤታማ ይሆን ዘንድ ሂደት አለው፡፡ጊዜን ይፈልጋል፣ማጥናት ይፈልጋል፣ማሰላሰልንም ይጠይቀናል፡፡ያኔ ነው ከውስጣችን ሲወጣ ሥራን ሊሠራ የሚችለው፡፡ወረድ ብሎ ሐዋርያው ዮሐንስ ትንቢት ትናገር ዘንድ ይገባሃል(.11) እንደ ተባለ መስክሯል፡፡ትንቢት ይናገር ዘንድ የተገባው፣ቃሉ በሐዋርያው ዮሐንስ ውስጥ ተገቢውን ሂደት አልፏልና ነው፡፡ታዲያ የትንቢት ቃሉ ከአፉ ሲወጣም ታላቅ ሥራን እንደሚሠራ ምንም ጥያቄ አለው?

ጌታ ሆይ በሕይወታችን ዘርፈ ብዙ ሥራን ለሚሠራው ቃልህ ያልተከፋፈለ ልብንና ተገቢውን ጊዜ እንድንሰጥ እርዳን!

No comments:

Post a Comment