ስለዚህ አንታክትም
ወደ ሕይወታችን የሚመጡ ጫናዎች--------›መታከት--------› የጸሎት ሕይወት መቀዝቀዝ------›ለዲያቢሎስ ጥቃት በቀላሉ መጋለጥ--------›መሸነፍ------------›መውደቅ
በሕይወታችን ለመታከት የሚያጋልጡን ብዙ ምክንያቶች ይኖራሉ፡፡በበቂ ሁኔታ አለመጸለይና ከጌታ ቃል ጋር በቂ ሕብረት አለማድረግ እንደ ዋነኝነት ይቆጠራሉ፡፡የእግዚአብሔር ቃል “ተግባር መፍታት እንቅልፍ ታመጣለች፤የታካችም ነፍስ ትራባለች”(ምሳሌ 19፡15) ብሎ ይናገራል፡፡በእግዚአብሔር ፊት ትጉሕ አለመሆኑ ጠንቁ ብዙ ነው፡፡የእግዚአብሔርን ቃል በበቂ ሁኔታ አለማንበብ፣አለማጥናትና አለማሰላሰል መንፈሳችን ደካማ እንዲሆን ስለሚያደርገው በቀላሉ ልንታክት እንችላለን፡፡ሐዋርያው ጳውሎስ “በውስጡ ሰውነታችሁ በኃይል እንድትጠነክሩ” (ኤፌሶን 3፡16) ብሎ ለኤፌሶን ሰዎች የጸለየላቸው ለዚህ ይመስለኛ፤መንፈሳቸው ሲጠነክር ውጫዊ ጫናን መቋቋም እንደሚችሉ አስተውሎ ነው፡፡የውስጥ ሰውነታችን በኃይል የሚጠነክርበት መንገድ ደግሞ ከቃሉ ጋር በምናደርገው ሕብረትና የጠለቀ ጸሎት የምናገኘው ነው፡፡
ከመንፈስ ቅዱስ ድምጽ ይልቅ የስጋንና የነፍስን ድምጽ ስንከተል እምነታችንና ጽናታችን ስለሚሸረሸር በቀላሉ ልንታክትና ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን፡፡ስለዚህ ስሜቶቻችን፣ነፍሳችንና ስጋችን የሚለንን ሳይሆን መንፈስ የሆነው ቃል የሚለንን ለመሆንና ለመተግበር መጨከን ምንም አማራጭ የለውም፡፡ይህ ደግሞ ትልቅ ዲሲፕሊን ይፈልጋል፡፡
በብዙዎች ዘንድ ራእይ ወይም መገለጥ ሲጠፋ መታከት ሊመጣ ይችላል፡፡ለዚህ ነው የእግዚአብሔር ቃል “ ለአሕዛብ ሁሉ የታወቀው ሚስጥር እንደ ተገለጠ መጠን ሊያበረታችሁ ለሚችለው” (ሮሜ 16፡26) በማለት የሚናገረው፡፡አዎ! የወንጌል እውነት በበራልንና በተገለጠልን መጠን ነው እየበረታን የምንመጣው፡፡ በተገላቢጦሽ መንፈሳዊ ራእይ፣መገለጥና መረዳት ከሕይወታችን ሲጠፋ ሕይወታችን በድግግሞሽ ይዋጥና ልንታክት እንችላለን፡፡
ሌላው ትልቁ ምክንያት የአጋንንት ተጽእኖ ነው፡፡የእግዚአብሔር ቃል “ባላጋራችን ዲያቢሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ በዙሪያችሁ ይዞራል” (1 ጴጥርስ 5፡8)ብሎ ያስጠነቅቃል፡፡አንዱና ዋነኛው መንገድ ሊውጠን የሚጠቀምበት መንገድ ደግሞ መታከትን ወደ ሕይወታችን በማስረጽ ነው፡፡አትችልም፣አይሳካልህም፣የት አለ ፍሬህ፣ተሰሚነት የለህም ፣አርፈህ ብትቀመጥ ይሻላል ወዘተ እያለ አእምሮአችንን በመደብደብ የጀመርነውን ስራ ሊያስጥለን ይተጋል፡፡ስለዚህ ነቅተን በኃይል መቃወም አለብን፤በቃሉ ሰይፍም መዋጋት ይኖርብናል፡፡
እንደ አዲስ ኪዳን አማኝ እንዳንታክት እግዚአብሔር በክርስቶስ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ሰጥቶናል(2ጴጥ 1፡2-3)፡፡ለምሳሌ፡-
1.በውስጣችን ከክብር ወደ ክብር እንድንለወጥ የሚያደርግ መንፈስ ስላለ አንታክትም፡፡ 2ቆሮንቶስ 3 የምእራፉ መጨረሻ ላይ “መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን”(ቁ.18፤አጽንኦት የእኔ) ይላል፡፡ “እንደሚደረግ” የሚለውን ልብ በሉልኝ፡፡ይህ ማለት በውስጣችን መታከት እንዳይመጣ ይልቁንም መንፈሳዊ ለውጥና እድገት እንዲኖረን የሚሠራና የሚያተጋን መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን አለ ማለቱ ነው፡፡ከዚህ የተነሳ የሚቀጥለው ምእራፍ መጀመሪያ ላይ “ስለዚህ አንታክትም” (2 ቆሮንቶስ 4፡1) ይላል፡፡ይህ አባባል ከምእራፍ ሦስት ጋር ተያያዥነት እንዳለው ልብ ይሏል፡፡
2.ነገር ግን የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ይህ መዝገብ በሸክላ እቃ ውስጥ ስላለን አንታክትም
ይህ መዝገብ ጎማ ተወጥሮ እንዲቆይ በከመነዳሬ ውስጥ ያለው አየር እንደሚጠቅም ሁሉ በውስጣችን ያለው መዝገብ(ባከማቸነው ልክ)ከመታከትና ተስፋ ከመቁረጥ ይጠብቀናል፡፡የዚህን የመዝገብ በውስጣችን የመኖር ጥቅም ሲገልጽ እንዲህ ይላል፡- “በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤እናመነታለን እንጂ ተሰፋ አንቆርጥም፤እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም” (2ቆሮንቶስ 4፡8) ፡፡ትልቁ ነገር በውስጣችን ያለውን እምቅ ሀብት መንገዘቡ ነው የኛ ኃላፊነት፤ቃሉ“በጻድቅ ሰው ቤት ብዙ ኃይል አለ” (ምሳሌ 15፡6) ይላልና!
3.አንዱ የእምነት መንፈስ ስላለን(2ቆሮንቶስ 4፡13) አንታክትም፤ቃሉ በግልጽ እንደሚናገር እምነት ጽናትን ያመጣልና(ኢሳይያስ7፡9)!
4.የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ስለሚታደስ (2ቆሮ 4፡16)አንታክትም
ይህ ምንባብ በተለይ በክርስትና ሕይወታችን ዋና ቁልፍ ነገር መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ሐሳቡ መታከት እና መሰላቸት ወደ ሕይወታችን እንዳይመጣ የማቋርጥ ጸሎት እንደሚያስፈልገን ነው የሚያሳየን፡፡ልክ ባትሪ ሲደክም በአሌክትሪክ ቻርጅ እንደሚደረግና እንደገና ሊሠራ እንደሚችል ሁሉ ስንጸልይ(በተለይ በመንፈስ ስንጸልይ) እንታነጻለን፤ኃይላችን ይጨምራል፤ተስፋችን ይታደሳል ብሎም እንደገና ለቀጣይ ሥራዎች እንጠናከራለን፡፡ይህ ዲሲፕሊን የሚያስፈልገውና በቀጣይነት ያለማቋረጥ መተግበር ያለበት የሕይወት ዘመን ኃላፊነታችን ነው፡፡ለዚህ ነው ‹‹ዕለት ዕለት ይታደሳል››ብሎ የሚናገረው-የዕለት ተዕለት ተግባር!
በክርስትና ሕይወታችን መታከት ሊመጣ እንደሚችል ከላይ ባሉ አንቀጾች ላይ ጠቅሻለሁ፡፡በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ስንሆን ምን እናድርግ ለሚለው ስድስት ተግባራዊ ርምጃዎችን በመጥቀስ ጽሑፌን እጨርሳለሁ፡-
1.ጠንከር ያለ የጸሎትና የጽሞና ጊዜዎችን እንያዝ(ከጾም ጋር ቢሆን የበለጠ ይመረጣል)
2.ካለንበት ሁኔታ ጋር የሚሄዱ አነቃቂ መንፈሳዊ ጽሑፎችን እናንብ፤መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ እናንብ፣እናጥና እናሰላስል
3.ከእኛ በሚሻል የክርስትና ሕይወት ላይ ካሉ ባልደረቦች ጋር በመገናኘት እንመካከር እንጸልይ
4.የጠላት ተጽእኖ ሊኖር ስለሚችል እራሳችንን ትሑት በማድረግ ይጸለይልን
5.የአጋንንትን ምሽግ ለማፍረስ በእምነትና በመንፈስ እየተቃወምን እንጸልይ
6.ባለንበት ሁኔታ ላይ ሊረዱን የሚችሉ ጤናማ ስብከቶችንና ትምሕርቶችን እንስማ
የኃይል ምንጫችን እግዚአብሔር በመሆኑ ፊቱን በመሻትና በእግሩ ስር በመሆን ስንጠባበቀውና ስንፈልገው ታማኝ ነውና ይመጣል፤ያድሰናልም፡፡ ላይ “እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ነው አይደክምም አይታክትም ማስተዋሉም አይመረመርም፡፡ለደካማ ኃይልን ይሰጣል ጉልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል፡፡ብላቴኖች ይደክማሉ ይታክቱማል ጎበዛዝቱም ፈጽሞ ይወድቃሉ እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ” (ኢሳ 40፡31) የሚል ግሩምና ድንቅ የተስፋ ቃል አለን፡፡አዎ! ደጋግሞ መታወቅ ያለበት ነገር ሁላችንም ልንታክት፣ልንሰለች፣ተስፋ ልንቆርጥ እና ልንደክም እንችላለን ነገር ግን በዚህ ጊዜ ወደ ጌታ ዘወር ብለንና ወስነን በትግእስት ጸጥታና ቆይታ በጸጋው ዙፋን ፈት ጊዜን ብንወስድ,እግዚአብሔር የምህረት አምላክ ነውና ያድሰናል፣ያበረታናል እንደገናም በክንፍ እንድንወጣ ያደርገናል፡፡
ጉልበትን የሚያድስና የሚያበረታ አምላክ ከዘላለም እስከዘላለም የተባረከ ይሁን!
No comments:
Post a Comment