Thursday, March 12, 2015

የሚያስቀና ሕይወት



የሚያስቀና ሕይወት

በእነዚህ ባለፉት ጥቂት ቀናት የፍራንሲስ አሽበሪ፣የደንካን ካምፕቤል፣የኦስዋልድ ቻምበር፣የጆን ሃይድ ወዘተ መንፈሳዊ ሕይወትን የሚቃኝ መጽሐፍ እያነበብኩ ነፍስ አልቀረልኝም፡፡እጅግ በመደነቅና በመገረም ተሞልቼ ነበር የእነዚህ የእምነት ጀግኖች ግለ-ታሪክ እያነበብኩ የነበረውና፣ከፍ ያለ እንደ እነሱ የመሆን ራብ አድሮብኛል፡፡


የእነዚህ ጀግኖችን የሚያስቀና ሕይወት በመንፈስ ዐይቼ፣የኔንና በዙሪያዬ ያሉ ሰዎችን መንፈሳዊ ሕይወት ማሰቤ አልቀረም፡፡ታዲያ በነሱና በእኛ መካከል ያለው ልዩነት እጅግ ገዝፎብኛል፡፡እንደ እነሱ የመሆን ኃይለኛ ጉጉትም ስላደረብኝ፣ንባቤን እያቋረጥሁ ጌታዬን “እባክህ አስበን” በማለት ተማፅኛለሁ፣ቃትቻለሁም፡፡


በጥቅሉ የነበርኩበት ስሜት ከባድ ነበር፡፡ሊጐበኘን ዝግጁ የሆነ፣እጁን ዘርግቶ የሚጠብቅ ትሑት አምላክ ሆኖ ሳለ፣በድርቅ መመታታችን ሳስብ እጅግ አዘንኩ፤የውስጥ እንባም አነባሁ፡፡


በግለ-ታሪኮቹ ውስጥ ልቤን የነካው ነገር ይኼ ነው፡፡እነዚያን መንፈሳዊ ጀግኖች ያንን የመሰለ ግሩም ሕይወት እንዲኖሩ ያደረጋቸው አንድ ተመሳሳይ ነገር፣በአምላካቸው ላይ ሙሉ በሙሉ መደገፋቸው ነበር፡፡ለክርስትና ሕይወት እጅግ የተሰጡ ነበሩ፡፡የጸሎት ሕይወታቸው ነካ ነካ አልነበረም፤በመቃተትና በመጮኽ ውሎ የሚታደርበት ነበር እንጂ፡፡ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የነበራቸው ቁርኝትና ትስስር እጅግ ልዩ ነበር፡፡በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በጌታቸው ፊት ለመደፋት የማያቅማሙና የማይሰስቱ የምልጃ ሰዎች ነበሩ፡፡አያስቀናም?

እናም እንዲህ ብዬ ጸለይሁ፡- 

“ጌታ ሆይ ያለ ስስት ሁለንተናችንን እንደ እነዚህ የእምነት ጀግኖች እንድንሠጥህ እርዳን”
ከዚህ ሌላ ምን ይጸለያል ?

No comments:

Post a Comment