ጫናን የመቋቋሚያው ምስጢር
ከእግዚአብሔር መንፈስ ዳግመኛ ከተወለድን በኋላ፣ክርስትና አልጋ በአልጋ እንደማይሆን የታወቀ ነው፤በተለይ የአገልግሎት ሩጫ ከታሰበ! በተለያዩ አጣብቂኞች፣ግራ አጋቢ ነገሮች፣ተስፋ አስቆራጭ መንገዶችና የሚያንገደግዱ ጉዳዮች እናልፋለን፡፡ስለዚህ መውደቅና መነሣት ይኖራል፡፡
በእነዚህ የሕይወት ጉዞዎች፣የማይመጣ የተግዳሮት ዓይነት የለም፡፡የኢየሱስ ነንና፣እሱ ራሱ ባለፈባቸው ብዙዎቹ ጐዳናዎች ማለፋችን አይቀሬ ይሆናል፤እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፡-“የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን።” (2 ቆሮንቶስ 4፡10)
እነዚህን ወደ ሕይወታችን የሚመጡ ፈተናዎች ጥሶ ለማለፍና የፍሬዎች ሰዎች ለመሆን፣እግዚአብሔር የሚያስፈልገንን ሁሉ ሰጥቶናል(2 ጴጥሮስ 1፡2-3)፡፡እግዚአብሔር በውስጣችን ከብዙ ጉድ የሚጠብቀንና በጽናት እንድንቆም የሚያደርገን መዝገብ በውስጣችን አስቀምጧል፤የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ይላልና፡- “ነገር ግን የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ይህ መዝገብ በሸክላ እቃ ውስጥ አለን” (2 ቆሮንቶስ 4፡7)
የዚህ መዝገብ በውስጣችን የመኖሩ ጥቅም ምን መሰላችሁ? ልክ የመኪና ጐማ ተወጥሮ ሳይሟሽሽ ለረጅም ጊዜ እንዲቆይ በአየር የተሞላ ከመነዳሬ እንደሚያስፈልገው ሁሉ፣እኛም ይህንን ከባድ የክርስትና ጉዞ ለመቀጠል በውስጣችን የተቀመጠው መዝገብ በወሳኝነት ያገለግለናል፡፡ታዲያ የዚህ በውስጣችን ያለው የመዝገብ ስፋትና ይዘት፣የጉዞአችንን ሁኔታ በእጅጉ ይወስነዋል፡፡ለዚህም ነው የእግዚአብሔር ቃል “እንጀራህን በውኃ ላይ ጣለው፣ከብዙ ቀንም በኋላ ታገኘዋለህ”(መክብብ 11፡1) ብሎ የሚናገረው፡፡በፈተና ጊዜ ሲያቆምህ ታገኘዋለህ ማለቱ ነው፡፡በመከራ ጊዜ ሲደግፍህ ታየዋለህ ማለቱ ነው፡፡
በውስጣችን ያለው መዝገብ ነው በፈተና ውስጥ ጌታን አምነንና ተደግፈን እንድንቆም የሚያደርገን፤አምነንም ከከበባው ተቃራኒ የእምነት ቋንቋ ከአፋችን የሚወጣው(2ቆሮንቶስ 4፡13)፡፡የእግዚአብሔር ቃል “የጠቢብ ልብ አፉን ያስተምራል” (ምሳሌ 16፡23) እንደሚል መዝገቡ አፋችንንም ይገራዋልና፡፡
ስለዚህ ለልባችን መዝገብ ሰፊ ቦታን እንስጥ!
No comments:
Post a Comment