Friday, July 31, 2015

ከአደንዛዥ ዕፅ እሥራት የተፈታችው ጄሲ



ስሟ ጄሲ ይባላል፡፡አደንዛዥ ዕፅ ስትወስድ በትንሹ አትረካትም፡፡ዕፆቹን በተለያዩ መልኩ ትወስዳቸው ነበር፡፡የ 16 ዓመት ልጅ ሆና እናቷ ለጭንቀት የምትወስዳቸውን እንክብሎች እና አልኮሆል መውሰድ የጀመረችው፡፡

ከሕፃንነቷ ጀምራ በእንጀራ አባቷ ብዙ በደል ደርሶበታል፡፡ይህ ሰው እናቷንም በኃይል ያንገላታት ነበር፡፡ሰክሮ መጥቶ እናቷ ላይ ሽጉጡን ደግኖ ሲያስፈራራት የሚያመሽበት ጊዜ ጥቂት አልነበረም፡፡

እናቷ ከዚህ ሰው ጋር የጄሲ ዕድሜ ገና አሥራ ውስጥ ሆኖ ሳለ ነበር የተፋቱት፡፡ሰውየው ከቤታቸው ከሄደ በኋላም ቢሆን፣ጄሲ ውስጥ ገና ያልጠገገ ቁስል ነበር፡፡ታዲያ ሕመሟን ለማስታገስ ስትል አልኮሆል አብዝታ መጠጣቷን ተያያዘችው፡፡ካሳለፈችው መከራ የተነሣ ጠባይዋ የተበላሸ ነበርና ከብዙ ሰው ጋር ያጣላት ነበር፡፡

እናቷ የምትወስደውን ዛናክስ በመዋጥና አልኮሆል በመጠጣት ራሷን ማደንዘዟን ቀጠለች፡፡ከዚያም ከበድ ወዳለ ሜት ወደሚባል መድኃኒት ዞረች፡፡ስለምንም ነገር ማሰብ አቁማ ነበር፡፡ባጭሩ ግዴለሽነት የተጠናወተው ሕይወት መግፋት ዕጣ ፈንታዋ ሆነ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አረገዘችና ወንድ ልጅ ወለደች፡፡ከዚህ በኋላ ለልጄ እኖራለሁ ብላ ለራሷ ቃል ኪዳን ገባች፡፡ቢሆንም እንደዚያ መሆን አልቻለችም፡፡ከዚያም ሁለተኛ ወንድ ልጅ ደገመች፡፡ሕይወቷ የበለጠ ተወሳሰበ፡፡ስለዚህ የበለጠ ተዝረከረች፡፡

ጄሲ የምትወስደውን የሜት መጠን ስለ ጨመረችው፣ሕይወቷን ተቆጣጠረው፡፡የበለጠ ሕይወቷ እንደ ዓይን ጠፋ፡፡አብሯት ይኖር የነበረው ጓደኛዋ አካሄዷን ዓይቶ ጥሏት ሄደ፡፡መንግሥት ልጆቹን ከሷ ነጥቆ እሱ እንዲያሳድግ አደራ ጣለበት፡፡

ሕይወቷ ከመበላሸቱ የተነሣ አጠገቧ የሚሆንና የሚያጽናናት ምንም ነገር አልነበረም፡፡ጓደኞቿ ትተዋታል፤ልጆቿም ከሷ ጋር የሉም፤ልቅሶ ብቻ!ከዚህም የተነሣ ጄሲ ሕይወቷ በኃይል አስደንገጣት፡፡ያለችበት የቁልቁለት መንገድ አንድ ቦታ ላይ መቆም እንዳለበት አሰበች፡፡

በዚህ አጋጣሚ እናቷ ጌታ ኢየሱስን መከተል ጀምራ ሕይወቷ ሰመረና በኃይል ተለወጠች፡፡ስለዚህ ጄሲን ደጋግማ ቤተ ክርስትያን እንድትሄድ ትጋብዛትና ትመክራት ጀመር፡፡የእናትየው ንዝነዛ ፍሬ አፈራና ጄሲ ሰክራም ቢሆን መሄድ ጀመረች፡፡እቤት በምትቆይበት ሰዓት ደግሞ ወደ አምላኳ አብዝታ መጮኽ ጀመረች፡፡ብዙ ሳይቆይ ጸሎቷ ተሰማና፣በሕይወቷ ተለማምዳው የማታውቃው ሰላም አጥለቀለቃት፡፡የሱስ እስራቶቿ ተበጣጥሰው ነፃ አየር መተንፈስ ጀመረች፡፡

ለውጡ እጀግ ደስ ስላሰኛት ሕይወቷን ሙሉ በሙሉ ለጌታዋ ለኢየሱስ አስረከበች፡፡ከዚያማ የመጀመሪያ ያደረገችው ነገር፣አብሯት ይኖር የነበረውንና የሁለት ልጆች አባት ጓደኛዋ ጋር መደወል ነበር፡፡ባለቤቷ መለወጧን ሲሰማ እጅግ ደስ አለው፡፡ከዚያም አብረው እንዲኖሩ ያቀረበችለትን ሐሳብ በደስታ ተቀብሎ አብረው መኖር ጀመሩ፡፡ድል ባለ ድግስም ተጋቡ፡፡

ዛሬ ጌታ አንድ ሴት ልጅ ጨምሮ ባርኳቸው፣አምስት ሆነው ባንድ ጣራ ስር አብረው በደስታ ይኖራሉ፡፡ ጄሲ ስትመሰክር “ሰዎች በዚህ ዘመን እግዚአብሔር ተዓምር አይሠራም እያሉ ሲያወሩ እሰማለሁ፡፡ኧረ ለመሆኑ ከዚህ በላይ ተዓምር ምንድነው?”

http://www.cbn.com/700club/features/amazing/

Thursday, July 30, 2015

እነዚህ የደረቁ አጥንቶች በሕይወት ይኖራሉን?




 መንገድ ላይ እየሄድሁ ሳለ ድንገት “እነዚህ የደረቁ አጥንቶች በሕይወት ይኖራሉን?” የሚል መንፈሳዊ ድምፅ ወደ ውስጤ ዘልቆ እያሰብኩ የነበረውን ነገር አቋረጠኝ፡፡ጥያቄውን በውስጤ እንደሰማሁት ወዲያው ግርታና ግርምት እንደ ነበረኝ አልደብቃችሁም፡፡አሁን ግን በከፊልም ቢሆን የመጣው መልእክት ያለ ምክንያት አልመጣም ብዬ ስለማስብ ደስታን ፈጥሮብኛል፤ምንም እንኳ ጥያቄው እንዴት እንደሚመለስ ባላውቅም፡፡


እግዚአብሔርን ከኃያላኖች በላይና ልዩ የሚያደርገው የትንሣኤ አምላክ መሆኑ ነው፡፡አልቻልና አልታለፍ ያለውን ነገር ያስችላል፣ያሳልፋልም፡፡የከበደን ጉም ገፎ ደህና የሆነ ዘመንን ያመጣል፡፡ይህ ደግሞ በብዙዎች ዘንድ የተመሰከረ ነው፡፡የእስራኤል በ1948 መንግሥቷ ከፈራረሰና ከባዶ ነገር እውን ሆኖ መመለሱ አንዱ የዓለማችን ትንግርትና ይህንኑ የሚመሰክር ክስተት ነው፡፡
መቼም ስለ “የደረቁ አጥንቶች በሕይወት መኖር” ሳስብ የራሴ ሕይወት ነው ቶሎ ወደ አእምሮዬ የሚመጣው፡፡ተስፋ እንደሌለው፣ነፍስ ሊዘራ እንደማይችልና እንደ “ደረቀ አጥንት” ሕይወቴ ትርጉም አጥቶ የነበረበትን ዘመን አስታውሳለሁ፡፡በፍጹም ይሄ ዘመን ይመጣል ብዬ በሕልሜም ሆነ በውኔ አስቤ አላውቅም፡፡ያሳለፍኩት ጉስቁልና በዝርዝር ይተረክ ቢባል አንድ መጽሐፍ ብቻ የሚበቃው አይመስለኝም፡፡በዚያ የጨለማ ወቅት ብዙ ተስፋ መቁረጥ ነበር፤አንገት ማቀርቀር ነበር፤መሸማቀቅ ነበር፤ጭንቀትና ኀዘንም የማይለዩኝ የዘወትር ዕጣ ፈንታዎቼ ነበሩ፡፡እግዚአብሔር ይህንን በሁሉ መልኩ የሞተና ሙሉ በሙሉ የወደቀ ሕይወት ነው ትንሣኤ ሰጥቶ ይችን መልእክት ለምስክርነት የምጽፍላችሁ፡፡


መጽሐፍ ቅዱስን ሳነብ ከምደነቅባቸው ክፍሎች ሕዝቅኤል ምዕራፍ 37 ዋነኛው ነው፡፡ምክንያቱም ግልጽ ነው-ትንሣኤን ያውራልና ነው! ነቢዩ ሕዝቅኤል እንዲህ ብሎ ይናገራል፡-


“እግዚአብሔርም በመንፈሱ አወጣኝ፣አጥንቶችም በሞሉባት ሸለቆ መካከል አኖረኝ….በዙሪያቸው አሳለፈኝ፡፡እነሆም በሸለቆው ፊት እጅግ ብዙ ነበሩ፤እነሆም እጅግ ደርቀው ነበር” (ቁ.2)


ይህ ትንቢታዊ መልእክት የተጻፈው በምንም ተዓምር የኛ ነገር አበቃ ስላሉና በቃ አለቀልን ከዚህ በኋላ ትንሣኤ አናያም ብለው የደመደሙ እስራኤላውያንን አስመልክቶ ነው፡፡የነበሩበት የግዞትና የልቅሶ ጊዜ አንገሽግሿቸው በነበረበት ጊዜ የመጣ ትንቢት ነው፡፡ለመሆኑ ያንን ሁኔታና ጊዜ ዐይቶ ማንስ ትንሣኤን ያስባል ? በዚያን ጊዜ እነዚህ እስራኤላውያን “አጥንቶቻችን ደርቀዋል፣ተስፋችንም ጠፍቶአል፣ፈጸመንም ተቈጠርናል” (ቁ.11)ብለው ነበር፡፡ነገር ግን የመጣው ትንቢታዊ መልእክት እጅግ ተቃራኒ ነበር-ትንሣኤ(ቁ 12-14)!


አዎ፣ተስፋ መቁረጥ፣ፈጽሞ መውደቅ፣የኑሮ ትርጉም ማጣትና የሕይወት መድረቅ የሚያጋጥሙ ክስተቶች ናቸው፡፡አዎ፣የባዶነት ጊዜያትና የጭንቀት ጊዜያት ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ሕይወት እንደ “ደረቁ አጥንቶች” ትንሣኤ የሌለው እስኪመስል ድረስ፣ጣዕም የሌለው እስኪመስል ድረስ ጣዕም ሊያጣ ይችላል፡፡ቢሆንም ዋናው ቁም ነገር በዚህ ጊዜ ምን እናድርግ የሚለው ነው ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው፡፡


በዚህ ጊዜ ከምንም ጊዜ በላይ ወደ ጌታ አብዝቶ መጮኽና በፊቱ መሆን ያስፈልጋል(ለጊዜው ትርጉም ባይሰጥ እንኳን)፡፡የምሕረት አምላክ በደረቁ ነገሮቻችን ላይ ልምላሜና ትንሣኤ እስከሚያመጣ ድረስ በፊቱ መውደቅ ተፎካካሪ የሌለው ምርጫ ነው፡፡ነፍስን ሊያለመልም፣ሊያጽናና ሊያንጽ የሚችለውንና ልብን የሚያቀናውን ቃል በተጓዳኝ እያሰላሰሉ በፊቱ መሆን አስተዋይነት ነው ብዬ)አስባለሁ፡፡አዘውትሮ መጾም በግሩም ሁኔታ ሕይወትን ሲደግፍና በጌታ ላይ ያለን መጣበቅ ሲጨመር አይቼዋለሁና አዘውትሮ መለማመዱ ግሩም ነው ብዬ እመክራለሁ(ኢሳይያስ 58)፡፡


በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሆነን እየተጋን ስንጠባበቀው፣የፍቅር ጌታ በራሱ ሰዓት ሊያስደንቀንና ሊጎበኘን

  •     በድምፁ ይመጣል
  • ምሕረቱን ይገልጣል

  • በተዓምሩና በክብሩ በደረቁ ነገሮቻችን ላይ ይገለጣል

እናም  “የደረቁ አጥንቶች በሕይወት ይኖራሉ”(ቁ.6)


ስሙ ለዘላለም ይባረክ!

Wednesday, July 22, 2015

ባለ ብዙ ማስረጃ ሕይወት



ባለ ብዙ ማስረጃ ሕይወት

ሰሞኑን መጽሐፍ ቅዱስን ሳነብ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የነበሩትን፣ሐዋርያት ሆነው የተመረጡትን የጴጥሮስን፣የጳውሎስንና የሌሎችንም ምሥክርነት እያነበብኩ ልቤ በደስታ እየፈነጠዘ ሐሤት አደርግ ነበር፡፡እኒህ አባቶች በቀጥታ ከራሱ የሰሙትንና ከርሱ ጋር በነበራቸው ትስስር የዳሰሱትንና ያዩትን ነው የጻፉልን፡፡እነዚያን ማስረጃዎች በጥልቅ ብናስተውል መንፈሳዊ ሕይወታችን በኃይል ይለወጣል ብዬ አስባለሁ፡፡እኒያ ሐዋርያት ያለ ምንም መካከለኛ ተቀባይና ተላላኪ ነው ከኢየሱስ ከራሱ በቀጥታ የተቀበሉትን የነገሩን፡፡ይሄ መቼም የሚደንቅ ነገር ነው፡፡እስቲ አንዳንድ ያስደነቁኝን ጥቂት ነገሮች ላካፍላችሁ፡፡


የእግዚአብሔር ቃል ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ “አርባ ቀን እየታያቸው፣ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት እየነገራቸው በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ አሳያቸው”(ሐዋ.ሥራ 1፡3፤አጽንኦት በእኔ የተጨመረ)፡፡እስቲ አርባ ቀን የሚለውንና በብዙ ማስረጃ የሚለውን በልባችሁ አስምሩልኝ፡፡አይደንቅም? አንድ ቀን ወይም ለጥቂት ጊዜ አይደለም የታያቸው-አርባ ቀን !ደግሞም በብዙ ማስረጃ ነው የታያቸው፡፡በግሌ የዛሬ 16 ዓመት ገደማ፣ለደቂቃዎች በራዕይ ዐይቼው ተደንቄ ቀርቻለሁ፡፡ይገርማል እነዚህን ድንቅዬ ተደጋግመው ቢነበቡ የማይሰለቹ ማስረጃዎችና ልምምዳቸውን ነው በወንጌላት የጻፉልን፡፡
ከሚደንቀኝ ምንባብ ውስጥ ሌላውን እነሆ(ሐዋርያው ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ ሲመሰክር የተናገረውን ነው)፡-


“እኛም በአይሁድ አገርና በኢየሩሳሌም ባደረገው ነገር ሁሉ ምስክሮች ነን እርሱንም በእንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት።እርሱን እግዚአብሔር በሦስተኛው ቀን አስነሣው ይገለጥም ዘንድ ሰጠው፤ ይኸውም ለሕዝብ ሁሉ አይደለም ነገር ግን በእግዚአብሔር አስቀድሞ የተመረጡ ምስክሮች ለሆንን ለእኛ ነው እንጂ፤ ከሙታንም ከተነሣ በኋላ ከእርሱ ጋር የበላን የጠጣንም እኛ ነን።ለሕዝብም እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ በእግዚአብሔር የተወሰነ እርሱ እንደ ሆነ እንመሰክር ዘንድ አዘዘን”(ሐዋ.ሥራ 10፡39-42))

 
አዎ፣ከትንሣኤው በኋላ አብረውት አሳልፈዋል፡፡አብረውት በልተዋል፣ጠጥተዋልም፡፡ከአፉም ድንቅ የሆነውን ልብን በመለወጥ የሚታወቀውን ቃሉን ተቀብለዋል፡፡ያንን ደግሞ ለእኛ አስተላልፈውት በሕይወታችን ድንቅ ሥራን እየሠራ ይገኛል፡፡ኢየሱስ ሦስቱ ሐዋርያትን(ጴጥሮስን፣ያዕቆብንና ዮሐንስን)ብቻቸውን ወደ ረጅም ተራራ ካወጣቸው በኋላ በፊታቸውም ተለውጦ ክብሩን ዐይተዋል(ማቴዎስ 17፡1-2 ያነቧል)፡፡ይህንን ክስተት ሐዋርያው ጴጥሮስ በመጥቀስ፣የተሰጠን ወንጌል በእውነተኛ ምስክሮች ላይ የተደላደለ እንደ ሆነ እንዲህ ብሎ መስክሯል(እኔ መቼም ይህንን ክፍል ስለምወደው ደጋግሜ ነው የማነበው)፡-


“ከገናናው ክብር በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው የሚል ድምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ተቀብሎአልና፤እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህን ድምፅ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን።ከእርሱም ይልቅ እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን” (2 ጴጥሮስ 1፡16-19)


ይሄ አስደናቂ መልእክት ነው፡፡ከሰማይ የመጣውን ድምፅ በቀጥታ ነበር የሰሙት፡፡ጌታ ዐይኖቻችንን ከፍቶ ይህንን መልእክት ብናየውና ብንረዳው እጅግ ሕይወትን የሚለውጥ ምስክርነት ሆኖ እናገኘዋለን፤ሐዋርያው እንደ ወረደ የተቀበለውን ነውና የሰጠን! ደግሞም ያየነውና የዳሰስነው ብቻ በቂ አይደለም ይለናል፤ “ከእርሱም ይልቅ እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን’’ ነው የሚለን-የማይናወጥ፣የማይሰበር፣የማይታጠፍ፣የማይለወጥ፣ሰባት ጊዜ እንደ ተጣራ ብር የነጠረ!


ሐዋርያው ዮሐንስም በግልጽ በሚገባን አገላለጽ እንዲህ ብሎ ነግሮናል(ይኼን ክፍልማ ሳነበው እጅግ ነው የሚገርመኝ፤ደጋግሜ አንብቤው አልጠግብም)፡-


“ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን፣በዓይኖቻችን ያየነውን፣የተመለከትነውንም፣እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል፣እንመሰክርማለን፤ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን”(ዮሐንስ 1፡1-2)


በዚህ ምንባብ ያሉትን አገላለጾች እስቲ ሰከን ባለ ሁኔታ አስቧቸው፤ልብ ነው የሚንጡት-ያየነውን፣የተመለከትነውን፣የዳሰስነውን፣ለእኛም የተገለጠውን!! ቢሆንም እግዚአብሔር አምላክ በእነዚህ በምናነባቸው የጸኑ ምስክሮች ብቻ አልተወንም፡፡በተግባር ደረጃ ራሱን በተለያየ መንገድ እየገለጠ አሳይቶናል፡፡ሲደግፈን፣በመከራ ውስጥ ጸጋ ሰጥቶ ሲያሳልፈን፣ልባችንን በመንፈሱ ኃይል በደስታና በሐሤት ሲያሞቀውና አንችልም ያልነውን እንድናልፍ እያደረገ ቀጥተኛ የሆነ ምስክረነት በልባችን እየጻፈ ይገኛል፡፡ብርሃኑን በልባችን ያበራ እግዚአብሔር ስሙ ለዘላለም ይባረክ!!


Wednesday, July 8, 2015

በአንዲት ውብ ዝማሬ ከሞት ያመለጠው ጄምስ



ጄምስ ዊልፎንግ እናቱ በጣም የሚወደውን ወላጅ አባቱን መግደሏን ገና እንቦቀቅላ ሕጻን ሆኖ ነው የሰማው፡፡ጄምስ ሲናገር “ከቤት ልወጣ ልብሴን እያዘጋጀሁ ነበር፡፡ድንገት እናቴ ቀልቧን ስታ ነው መሰል ሽጉጧን አንሥታ አባቴ ላይ አንድ አገር ጥይት አርከፍክፋ የገደለችው” ብሎ መስክሯል፡፡

ጄምስ ያባቱን አስደንጋጭ ዜና ሲሰማ የነበረውን ሁኔታ በሚገባ ያስታውሰዋል፡፡ያ ሁኔታ በአእምሮው ላይ ትልቅ ቁስል ጥሎበትም አልፏል፡፡በተጨማሪም የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳለ፣በቅርብ ቤተ ዘመዱ ተደጋግሞ ተደፍሯል፡፡ምስጢሩን ካወጣ ሰውየው ሊገድለው እንደሚችል አስጠንቅቆታልና፣ለ 42 ዓመታት ለማንም ተንፍሶት አያውቅም፡፡

ይህ ሁኔታ ጄምስ ለእግዚአብሔርና ለሰዎች ያለውን ስዕል አበላሽቶበታል፡፡የሁልጊዜም ጥያቄው “እግዚአብሔር ካለ ለምን እንዲህ እንድሆን ፈቀደ ?” የሚል ነበር፡፡አባቱ ስለሞተና እናቱ ወደ ወኅኒ ስለ ወረደች፣ጄምስ እና ወንድሞቹ ወደ ሕጻናት ማሳደጊያ ተላኩ፡፡ነገር ግን ብዙ ሳይቆይ፣ጄምስ በሕጻናት ማሳደጊያው የጠበቀውን ክብካቤ ስላላገኘ ኮበለለ፡፡

ከማሳደጊያው ከኮበለለ በኋላ፣ስለ ምንም ማሰብ አቆመ፡፡ራሱንም ለመግደል በርካታ የሕክምና እንክብሎችን ወስዶ ታሞ ነበርና፣ ሆስፒታል ውስጥ ትንሽ ጊዜ ተኝቷል፡፡ከሆስፒታል ከወጣ በኋላ ጎዳና ላይ መኖሩን ተያያዘው፡፡ከዚያማ የአደንዛዥ ዕፅና የአልኮሆል ሱሰኛ ሆነ፡፡ይህንን ያደረገው የውስጥ ሕመሙን ለመርሳት ነበር፤ባሰበት እንጂ!

ጄምስ ባሪያ ያደረገውን ሱሱን ለማስተናገድና በገንዘብ ለመደገፍ ሲል፣ቤት ውስጥ እየገባ መዝረፍ ጀመረ፡፡ከዝርፊያው ጋር በተያያዘ ሁለት ዓመት ታሰረና ተፈታ፡፡ለሁለተኛ ጊዜ ለ 14 ዓመት ተፈረደበትና ታሰረ፡፡የእስር ጊዜውን ጨርሶ ከወጣም በኋላ በኑሮው ዘይቤው ምንም ለውጥ አልነበረውም፡፡

ጄምስ ይባስ ብሎ የኮኬይን ጥገኛ  ሆነ፡፡የአልኮሆል አጠጣጡም ከወትሮው እየጨመረ መጣ፡፡አንድ ቀን ለ 48 ሰዓታት ኮኬይንና አልኮሆል ደባልቆ ወስዶ ሲነቃ በኃይል አሞት ነበርና እጅግ መረረው፡፡በዚያ ብሶት እግዚአብሔርን “እንዲህ ሆኜ ወደ ፊት መቀጠል አልፈልግም፡፡አንተ በውኑ እንደሚባለው ትልቅ ከሆንክ፣ለምን በእንደዚህ ዓይነት ሕይወት እንድቀጥል ፈቀድህ?” ብሎ ይጠይቃል፡፡ከዚያም ሽጉጡን አንሥቶና ጭንቅላቱ ላይ ደቅኖ ለመተኮስ ቢሞክር አልሠራ ይለዋል፡፡ከዚያ በኋላ “ራሴን ሌላ ሙከራ አላደርግም” ብሎ ለራሱ ይምላል፡፡

አንድ ቀን ጄምስ የሚሠራበትን የመሥሪያ ቤት ወለል እያጸዳ ሳለ፣የሥራ ባልደረባው “ኢየሱስ ይወደኛል” የሚል መዝሙር ሲዘምር ይሰማዋል፡፡ከዚያም ባልደረባውን “እንዴት ኢየሱስ ይወደኛል? እስቲ ተመልከት፣ሕጻን ሳለሁ በአዋቂ ቤተ ዘመድ ተደፍሬአለሁ፤እናቴ የምወደውን ወላጅ አባቴን በጥይት ገደለችው፡፡ራሴን ለመግደል ብዙ ሞክሬአለሁ፤ጥሩ ሕይወት ኖሬ አላውቅም፡፡ዘራፊና ወንበዴ ነበርሁ፡፡ኢየሱስ ይወድሃል ነው የምትለኝ? እንዴት ሊወደኝ ይችላል? ብሎ ይጠይቀዋል፡፡

ባልደረባውም በጥሩ ሁኔታ ጥያቄውን ስለመለሰለት፣ልቡ በግሩም ሁኔታ ይነካል፡፡ከዚያም ቤቱ ሄዶ ጮክ ብሎ “እግዚአብሔር ሆይ ከወደድከኝ እባክህ ወደ ሕይወቴ ና፤ኃጢአቴን ሁሉ ይቅር በለኝ” ብሎ ይጸልያል፡፡ልክ ያንን ጸሎት ከጸለየ በኋላ እላዩ ላይ የነበረው ሸክም ሁሉ እንደተራገፈ ተሰማው፡፡ክንፎች ያሉትና መብረር የሚችል ያህል ነበር ስሜቱ፡፡ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስን ያለማሰለስ ማጥናቱን ተያያዘው፡፡ከጥቂናት በኋላ መሥሪያ ቤት ያዩት ሰዎች ለውጡን ዐይተው ሲጠይቁት “ኢየሱስን አገኘሁት፤ድኛለሁ” ይላቸዋል፡፡

ከዚያም ጄምስ የውስጥ ሕመሙ ሙሉ በሙሉ ይድን ዘንድ የበደሉትን መማር እንዳለበት ተረድቶ ነበርና፣ሕጻን ሳለ ክፉኛ የበደለውን ዘመዱን ስልክ ደውሎ “ምሬሃለሁ” አለው፡፡በተጨማሪም አብራው አንድ ቤተ ክርስትያን የምታመልከውን እናቱን በሙሉ እንደማራት ነገራት፡፡በዚህ ሰዓት ባንድ ቤተ ክርስትያን በፓስተርነት ያገለግላል፡፡ግሩም የሆነ ትዳርም ይዟል፡፡

ጄምስ “ወደ ኋላ ሳስበውና የአሁኑን ሕይወቴን ሳስተያየው፣ይህንን ያለሁበትን ለውጥ ከጌታ በቀር ማንም ሊያደርግ እንደማይችል እመሰክራለሁ” ብሏል፡፡በተጨማሪም “ሕይወቴን በ1997 ዓ.ም ለጌታ ሳስረክብ፣ውስጤን የቀየረ ብርሃን ወደ ልቤ ገብቷል፤ስሙ ለዘላለም ይባረክ” ብሎ መስክሯል፡፡

አዎ፣እውነት ነው! ጌታ ኢየሱስን የመሰለ አዳኝና ምስኪንን ከፋንድያ ማንሣት የሚችል ብቃትና ችሎታ ያለው አምላክ አላየንምና ስሙ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይባረክ!!