Wednesday, June 24, 2015

የዌንዲ ያልተጠበቀ ስብራትና የጌታ ትድግና



የዌንዲ ያልተጠበቀ ስብራትና የጌታ ትድግና

በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን? ስብራትን እንደ እሱ የሚጠግን፣ፈዋሽ አምላክ ከየት ይገኛል?

ስሜ ዌንዲ ብላይት እባላለሁ፡፡ትዝ ይለኛል ሰኔ 7 1986 ላይ ነበር ከኮሌጅ የተመረቅሁት፡፡ያንን ምሽት ቤታችን ካለው ገንዳ ከጓደኞቼ ጋር ስዝናና ቆይቼ፣ልብሴን ልለውጥ ወደ ቤት አመራሁ፡፡የቤቱን ደረጃዎች ጨርሼ ወደ መኝታ ቤቴ ልገባ ትንሽ ሲቀረኝ፣ፊቱ ላይ ጥቁር ጭንብል ያጠለቀ ሰው ትልቅ ቢላ ይዞ መኝታ ቤቴ አስገብቶ እንድቆልፈው አስገደደኝ፡፡ከዛም ወደ አልጋዬ ጐትቶና አስተኝቶ፣ለብዙ ሰዓታት እንደ ፈለገው ሲጫወትብኝ ቆየ፡፡ስለምነው የበለጠ ስለሚበሳጭ የሚለውን ከማድረግ በስተቀር ምንም ዕድል አልነበረኝም፡፡

መጨረሻ ላይ ጥሎኝ ከመሄዱ በፊት ይህንን ምስጢር ላንድ ሰው ብናገር፣ሊገለኝ እንደሚችል ዝቶብኝ ውልቅ ብሎ ሄደ፡፡ልክ እንደ ወጣ ለቤተ ዘመድና ለእጮኛዬ አሳውቄ፣ለፓሊስ ወዲያው አመለከትን፡፡በቂ ማስረጃም ለፓሊስ ሰጠሁ፡፡ከዛ አካባቢዬ በነበሩ ሰዎች የማጽናናትና የማበርታት ኃይል ቀለል ቢለኝም፣ከቀናት በኋላ ሌላ በሕልሜም በውኔም ያልጠበቅሁት ነገር ሆነ-በጭንቀት፣ፍርሃት፣ባዶነትና ደስታ ማጣት ተዋጥሁ፡፡

ሌሊት መተኛት አቃተኝ፡፡ደክሞኝ ከተኛሁ፣ድንገት ደንግጬ በቅዠት እነሣለሁ፤አዘውትሬ በሕልሜ ይኼ ሰው ጩቤ ይዞ ሲያስፈራራኝ አየው ነበረና፡፡በጭራሽ ብቻዬን ባዶ ክፍል ውስጥ መግባት አቃተኝ፡፡ፍርሃትና ጭንቀት ሙሉ በሙሉ ሕይወቴን ተቆጣጠረው፡፡ሕይወቴን እንደ ገና ለማቅናትና በሁለት እግሬ ለመቆም በማለም ቶሎ አገባሁ፡፡ኮሌጅ ገብቼም ሕግ ማጥናት ጀመርሁ፡፡ከውጪ ሁኔታዬ መልካም ቢመስልም፣በእግዚአብሔር ላይ እናደድ ነበር-መልስ ፈላጊ ነበርሁና፡፡እግዚአብሔር ላይ በቀጥታ “እጠላሃለሁ፤እንዴት እንደዚያ ዘግናኝ ነገር በአካሌ ላይ ሲደረግ ዝም አልክ?” ብዬ ደጋግሜ እጮኽ ነበር፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ጉዳዬን የያዙት ፓሊሶች “ለወንጀል ምርመራ የሰጠሽው ናሙና(DNA sample) ስለ ጠፋ፣ተጠርጣሪውን ለፍርድ ማቅረብ አንችልም”ብለው አረዱኝ፡፡በዚህ ሁኔታ እጅግ አበድሁ፣በገንሁም፡፡ቢሆንም በጥቂት ቀናት ውስጥ፣ይኼን ሰው መማር እንደሚገባኝ በውስጤ ተረዳሁ፡፡ስለዚህ መኝታ ቤቴ ተንበርክኬ እየጸለይኩ፣ “የደፈርከኝና ለዚህ ሁሉ መከራ ያበቃኸኝ ወንድም ሆይ፣ባለህበት ሙሉ በሙሉ ይቅር ብዬሃለሁ” ብዬ ስተነፍስ፣የተሰማኝ እረፍት ቀላል አልነበረም፡፡ኩንታል ሸክም ከላዬ ላይ እንደ ተራገፈ ነበር የተሰማኝ፡፡በተጨማሪም “የውስጥ ሰላሜን፣ማንነቴን፣ሕይወቴን፣ኑሮዬንና ግቤን አበላሽተሃል፤ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ምሬሃለሁ” ብዬ የውስጤን ብሽቀትና ምሬት አወጣሁት፡፡

ከዚያ ውሳኔ በኋላ፣ተዓምር ነው የሆነው፡፡በኃይል ቆሽሾ እንደ ታጠበ ሰው ነበር የቀለለኝ፡፡ፍጹም ነፃ ሆንኩ፡፡መንፈሴን ከፍታን ረገጠ፡፡ሰላምና ደስታ አጥለቀለቀኝ፡፡

የነበረኝ ምሬት ቢተንና ሰላምና ደስታ በልቤ ቢሰፍንም፣አንድ ገና ያልተወገደ ችግር ነበረኝ-ድንገት የሚከሰት ፍርሃት፡፡ፍርሃቴ ደግሞ በዙሪያዬ ያሉትን ሰዎችና ባለቤቴን ጭምር የሚረብሽ ስለ ነበር፣ገና ድሌ ሙሉ አልነበረም፡፡ከዚያም ጉዳዬን በግልጽ ለፓስተሬ ዘክዝኬ ነገርኩት፡፡ፓስተሩም ሰዎችን የመምከር ጸጋ ነበረውና፣ሕይወቴን የሚለውጡ ግሩም ምክሮችና ትምህርቶችን በሚደንቅ ሁኔታ ለገሰኝ፡፡ከጎኔ ሆኖ ይደግፈኝም ጀመር፡፡የእግዚአብሔርን ቃል እንዳጠና መክሮኝም ስለ ነበር፣መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ጉድ አጠናው ጀመር፡፡ውዬ አድርበት ነበር ማለት ይቀላል፡፡ከዚያም ያ የፍርሃት ባርነት፣እንደ ጥንቸል ከፊቴ ላይመለስ ሸሸ፡፡ነፃ ወጣሁና በድፍረት ተሞላሁ-ለሌሎችም እስከሚተርፍ ድረስ፡፡

በአሁኑ ሰዓት ልበ ሙሉ ሚስት፣እናትና የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ ነኝ፡፡ማቄን ቀድዶ ደስታንና ድፍረትን ያስታጠቀኝ የፍቅር አምላክ ይመስገን፡፡ስሙ ለዘላለም ይባረክ!

Thursday, June 18, 2015

በአደንዛዥ ዕፅ የተበላሸ፣በፍቅር የዳነ



የውስጥ አካላቴ በምወስዳቸው ኬሚካሎች የተበከለና የደነዘዘ ስለ ነበር፣ስሜት ማለት ምን እንደ ሆነ አላውቅም ነበር፡፡ዶፓሚን መቼ እንደምተኛ ይነግረኛል፡፡አልኮሆል ወደ መኝታ መሄድ እንደሚገባኝ ያሳውቀኛል፡፡አደንዛዥ መድኃኒቶች መቼ እንደምሰርቅ፣መቼ እንደምዋሽ፣መቼ እንደማታልልና መቼ እንደምደባደብ ይነግሩኛል፡፡እኔም በታማኝነት ለነዚህ የሱስ ቀንበሮች ታዛዥ ነበርሁ፡፡

ስሜ ሐውስተን ያሬድ ሲሆን፣በክርስትያን ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደግሁት፡፡ከአደንዛዥ ዕፅ፣አልኮሆልና ቁማር ባገኘሁት ማንነት የተነሣ፣የቤተሰቦቼን እምነት እርግፍ አድርጌ ተውሁኝ፡፡ሜት የሚባል አደንዛዥ መድኃኒት እየሸጥሁ ብዙ ገንዘብ በቀላሉ አገኝ ነበር፡፡ለጊዜውም ቢሆን ኑሮዬን ወደድሁት፡፡ለ 12 ሰዓት ያህል ብቻ ሳይሆን ከፈለግሁኝ ለ 3 ቀናት ሳላቋርጥ ቁማር መጫወትን ተክኜበት ነበር፡፡ማድረግ የነበረብኝ ነገር የምወስደውን የአደንዛዥ መጠን ከፍ ማድረግ ብቻ ነበር፡፡ነገር ግን እየዋለ እያደር የምወስደው መድኃኒት ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረኝ፡፡

ሜት በሚባለው አደንዛዥ ስሜ ገነነ፡፡ዙሪያዬን በጓደኞችና በአደገኛ ቡድኖች ተከበብሁ፡፡ቢሆንም ፍርሃትና ጥርጣሬ በሕይወቴ ነገሡ፡፡ስለዚህም ሽጉጥ አይለየኝም ነበር፡፡ፓሊስም ቅንጣት የማያስፈራኝ ሰው ነበርሁ፡፡ለኔ እስር ቤት መታሰር ቀልድ ነበር፡፡ቢሆንም የእስር ጊዜ እየጨመረ መሄዱ አሳሰበኝ፡፡አንድ ጊዜ 3 ዓመት ተኩል ታስሬ ስፈታ፣ከወንድሜ ጋር መኖር ጀመርሁ፡፡ወንድሜም እንደኔው ሜት ይነግዳል፡፡አንድ ቀን በወጣበት ሳይመለስ ቀረ፤ደብዛው ጠፋ፡፡ከዚያም ከሜት ጋር በተያያዘ አደገኛ ወንጀል መኪና ሰርቄ ስሸሽ፣ፓሊሶች በመኪና አሳድደው ያዙኝና 7 ዓመት አሰሩኝ፡፡በዚህ ሰዓት ፍርድ ቤቱን ፍርዱን እንዲቀንስልኝ ተማጸንሁ፡፡ ነገር ግን ልመናዬ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ይህ ሁኔታ ልቤን በኃይል ሰበረው፣አዘንኩም፡፡ስለዚህም ሕይወቴን መለወጥ አለብኝ ብዬም ወሰንሁ፡፡

በመጨረሻም እዚያች ጠባብ እስር ቤት ውስጥ እግዚአብሔር በሚደንቅ ሁኔታ አገኘኝ፡፡ልክ ሰው እንደተናገረኝ ያህል “ወደ እኔ ተመለስ” የሚል የማያሻማና የማያጠራጥር ድምጽ ሰማሁ፡፡ከሰማሁት ድምጽ የተነሣ፣ሕይወቴ በፍጥነት ተለወጠ፡፡ሰላምና ደስታ አጥለቀለቀኝ፡፡ጌታ እንደ ማረኝ ታወቀኝ፡፡ተሸክሜው የነበረው የሱስ ቀንበር ተነነ፡፡ሁለት ሺህ ፓውንድ የሚመዝን ዝሆን ከላዬ እንደ ተነሣ ያህል ነበር የተሰማኝ፡፡

ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትና መጸለዬን ተያያዝኩት፡፡የእግዚአብሔር ፍቅር በሕይወቴ ውስጥ የነበረውን ባዶነት ሞላው፡፡በአደንዛዣ ዕፅ የማገኘው ሰላምና መረጋጋት ጊዜያዊና ቶሎ የሚበን ነበር፤አሁን ግን ዘለቄታ ያለው ሰላምና ደስታ አለኝ፡፡ከዚያም ጌታ ትልቅ ተዓምር አደረገልኝ፡፡እንዲህ ነበር የሆነው፡፡ዘጠኝ ወር ከታሰርሁ በኋላ ከማረሚያ ቤቱ ውጪ የጸባይ ማረሚያ ፕሮግራም ወይም ኮርስ እንድወስድ ተደረግሁ፡፡ያ ፕሮግራም ለወደፊቱ አኗኗሬ ዓይኔን ከፍቶልኝ ተጠናቀቀ፡፡በዚህ ሰዓት የወጣቶች ፓስተር በመሆን አገለግላለሁ፡፡ጌታ ላና የምትባል ጌታን የምትወድና የተባረከች ሚስት ሰጥቶኛል፡፡ሕይወቴ ወደ ኋላ ላይመለስ ተለውጧል፡፡

በዚህ ሰዓት ከማንኛውም ሱስ ነፃ ነኝ፡፡የአልኮሆል ባሪያ አይደለሁም፡፡ወንጀለኛ አይደለሁም፡፡አሁን የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ፡፡አሁን በጌታ ጸጋ አዲስ ሕይወት አግኝቼና ታድሼ ግሩም ሕይወት እየመራሁ እገኛለሁ፡፡ስሙ ለዘላለም ይባረክ !

Thursday, June 11, 2015

ሕይወቱ ከጥፋት የተረፈው ሪኪ ክሪስማስ




ስሜ ሪኪ ክሪስማስ ይባላል፡፡ከጓደኞቼ ጋር ክፍት የሆነ ጋራጅ ወይንም መኪና ካገኘን ዘርፈን መሄዱን ተክነንበታል፡፡በውስጤ “ማንም ሰው ሊያቆመኝ አይችልም” የሚል የራስ ትምክህት ነበረኝ፡፡እንዳውም “እግዚአብሔር ራሱ ሊያቆመኝ አይችልም” ብዬም አስቤ አውቃለሁ፡፡


በማኅበረሰቡ ውስጥ አደገኛ ጠንቅና አሸባሪ መሆን የጀመርሁት ጉርምስና  እንደ ጀማመረኝ ነው፡፡በሕይወቴ አንድ ግብ ብቻ ነበረኝ፡፡እሱም “እዚህ ምድር እስካለሁ ድረስ፣እደሰታለሁ፤ከዚያም ሲያበቃ ያበቃል” የሚል ነበር፡፡


በእናት ብቻ ነው ያደግሁት፡፡እናቴ ገና ከሕጻንነቴ ጀምሮ “የባሕርይ ችግር” እንደ ነበረኝ ትናገር ነበር፤ “እያደገ የሄደ የንዴት ችግር አለው” ትል ነበር፡፡ለሚቀርቧት “ዓመፀኛ ነው” ብላ ደጋግማ ስትናገር ሰምቻለሁ፡፡ቢሆንም እግዚአብሔር እንደሚወደኝና ከኔ ጋር እንደ ሆነ እየነገረችኝ፣ቤተ ክርስትያን እንድሄድ ከመጣር ችላ ብላ አታውቅም፡፡


አንዱ ክፍል እኔ እግዚአብሔርን ይወድ ነበር፡፡ሌላኛው እኔ ደግሞ ከቤተ ክርስትያን ውጪ ያለውን ሕይወት ማየት ፈለገ፡፡በቤተ ክርስትያን አያቸው የነበሩ ብዙዎቹ ድሆች ስለ ነበሩ፣ያንን ከባቢ ጠላሁት፡፡ስለዚህም ለጊዜውም ቢሆን ከአካባቢው መራቅን መረጥሁ፡፡እውነተኛ ሕይወት ይገኝበታል ብዬ ያሰብኩትን ሁሉ እስከ ጥግ ድረስ አደረግሁ፡፡


በእንደዚህ ዓይነት ፍለጋ እያለሁ ነበር የታወቀ የወንበዴ(gang) ቡድን የተቀላቀልኩት፡፡እጅግ አደገኛ ጊዜ ላይ ነበርና የነበርሁት፣”ፓሊስን መግደል ምንም ችግር የለውም፣ምንም አይደል ሰው ከ10 ሴቶች ጋር ቢተኛ፤አደንዛዥ ዕፅ መሸጥ ምንም አይደል፤ምክንያቱም መኖር አለብህ፣መብላት አለብህ” ከሚሉ ለጋ ወጣቶች ጋር ነበር የተዋሃድኩት፡፡


ከእነዚህ ባልደረቦች ጋር ወደ አደገኛ ስርቆት ውስጥ ገባን፡፡የመኪና ውስጥ ቴፓችን መስረቅ ነበር የኔ ኀላፊነትና ድርሻ፡፡ሌብነቱ አድጐ፣ቤት ሰብረን እየገባን መዝረፉ ተጧጧፈ፡፡ብዙ ገንዘብ ስለምናገኝ፣ልባችን እስኪጠፋ እንዝናና ነበር፡፡ነፍሴ ከልጆቹ ነፍስ ጋር በፍቅር ተሳሰረች፡፡ከዚያም የተነሣ ወጣ ገባ እያልኩ የምማረው ትምህርት እስከ መጨረሻው ተቋረጠ፡፡ለአካባቢው እጅግ አደገኛ በመሆኔ አካባቢው ተሸበረ፡፡በዚህ ሁሉ ግን እናቴ ተስፋ አልቆረጠችም ነበርና፣አብዝታ ትጸልይልኝ ነበር፡፡ “እግዚአብሔር ምንም ሳይሆን ወደ ራሱ ይመልሰዋል” ብላ ታምንና በቅርቧ ላሉ ሰዎች ትናገር እንደ ነበረ ያካባቢው ሰዎች መስክረውኛል፡፡


ጊዜው እየገፋ ሲሄድ፣የእናቴ ጸሎት ያልሠራ እስኪመስል ድረስ፣ነገሮች እየባሱ መጡ፡፡አንድ ቀን የቅርብ ጓደኛዬ ተይዞ ወኅኒ ወረደ፡፡እዚያው እስር ቤት እያለ ወዲያው ይሞታል፡፡ከዚህ ወንድም ጋር እድሜያችን ተቀራራቢ ነበር፡፡የሚገርመው ሕፃን ልጅ ነበረችው፡፡የሚቀበርበት ሳጥን ወስጥ በድኑ ተዘጋጅቶ ሳለ፣ሕፃኗ  ወደ ሳጥኑ እያየች እሪታዋን አቀለጠችው፡፡ያንን ትዕይንት እያየሁ “እንዲህ ነው የሚያልቀው/that is how it ends” ብዬ ከልቤ ጋር አወራሁ፡፡ያ ልቤ ከልቤ ጋር የነበረው ንግግር የመንፈስ ቅዱስ ድምፅም እንደ ነበረ ምንም አልጠራጠርም፡፡ታዲያ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? ቀጥሎም በዛ ሳጥን ውስጥ ራሴን አየሁት፡፡እጅግ ደነግጬ ነበርና፣ ከዚያ ቀን በኋላ ከጓደኞቼ ራሴን አርቄ የጌታን ፊት መፈለግ ጀመርሁ፡፡እውነተኛ ንስሐ ገባሁ፡፡ጌታን ማረኝ ብዬ አምርሬ ተማጸንሁት፡፡ከዚየ በኋላ ያንን የወንበዴ ቡድን በኪሎ ሜትር ተለየሁኝ፡፡


ወዲያው በጌታ ምሕረት ሥራ አግኝቼ መሥራት ጀመርሁ፡፡ቤተ ክርስትያን መሄድ አዘወተርሁና፣ውስጤ በሚገርም ሁኔታ ታደሰ፡፡ያለ ጌታ ሕይወቴ ድምጥማጡ እንደሚጠፋ በሚገባ ገባኝ፡፡ከጊዜያዊ ደስታ ይልቅ፣ከሱ ጋር መሆን እንደሚሻል አስተዋልሁ፡፡ከቤቱ ላልወጣም ወሰንሁ፡፡በዚህም ምክንያት ልቤ በጥሩ ሁኔታ ተረጋጋ፡፡


እናቴ መቼም ቢሆን ገፍታኝና ትታኝ አታውቅም፡፡ይህን ባሰብኩት ቁጥር ይገርመኛል፡፡አሁንማ ግንኙነታችን እጅግ ታድሷል፡፡ይሄ ለኔ ብቻውን ትልቅ በረከቴ ነው፡፡አዘውትረን አብረን እንጸልያለን፣እናሳልፋለንም፡፡በዚህ ሰዓት ባል፣አባትና ፓስተር ሆኛለሁ፡፡ሌሎችን እንደ እኔ ከመሰለ ክፉ መንገድ እንዲመለሱ እረዳለሁ፡፡በጥቅሉ ጌታ ሕይወቴን ልናገረው ከምችለው በላይ በሁሉም መስክ ባርኮታልና ስሙ የተባረከ ይሁን!

Saturday, June 6, 2015

ሕይወቱ በእግዚአብሔር ጸጋ የተለወጠው የባንክ ዘራፊ

               
በራሴ መንገድ ሕይወትን መምራቱ ጥፋትና ውድቀት እንደ ሆነ የሊቃውንቶች ዓይነት ጥናት አላስፈለገኝም፡፡በ2009 ዓ.ም በሞቃትማው የበጋ ወቅት ላይ ነበር ከአምስት የባንክ ዝርፊያዎች ጋር በተያያዘ፣ለ 11 ዓመት ከታሰርኩበት እጅግ ከባድ እስር ቤት የተፈታሁት፡፡

አንባቢዎችን ምናልባት ሊያስደነግጥ የሚችለው ነገር፣ቤተ ክርስትያን ያስተዳድሩና ይመሩ የነበሩ ክርስትያኖች ቤተሰብ ውስጥ ማደጌ ነው፡፡በትምህርት ቤት የነበረኝ የቅርጫት ኳስ ሙያዬና የኮሌጅ መማር ዕድሌ ሲበላሽ፣በአደንዛዥ ዕፅ እስራትና ድብታ(depression) ለዓላማ የለሽ ኑሮ ተጋለጥሁ፡፡እንደ እኔ ዓላማ ያልነበረው ጓደኛዬ ባንክ እንዝረፍና ገንዘብ እናግኝ ብሎ ሲያማክረኝ፣እንደ በጎ ነገር ወዲያው ነበር የተስማማሁት፡፡

አምስት ባንኮችን በውስጣቸው ተቀጥረው የሚሠሩ አገልግሎት ሰጪዎችን እያስፈራራንና እያስደነገጥን ዘረፍን፡፡ልክ እንዳልሆንኩ ግን በሚገባ ይገባኝ ነበር፡፡ኦማሃ የሚባል ሆቴል ውስጥ በፓሊስ እስክያዝ ደረስ ዝርፊያውና ውንብድናው ቀጠለ፡፡ብዙ ሳልቆይ ተይዤ በፍርድ ቤት ዳኛ ፊት እግሮቼ እየተብረከረኩ፣መንፈሴም በኃይል እየተጨነቀ የቆምኩበት ጊዜ እጅግ ከባድ ነበር፤ምን ጊዜም አይረሳኝም፡፡በዚያን ጊዜ 23 ዓመቴ መሆኑ ነው፡፡

ወኅኒ ቤት እጅግ ከባድና አስጨናቂ ቦታ ነው፡፡ታዲያ ካጠገቤ ያሉትን ታራሚዎች ለመራቅ ስል፣በወኅኒ ቤት ውስጥ ሥራ መሥራት ጀመርሁ፡፡ሥራ በማልሠራበት ጊዜ ደግሞ ከተለያዩ መጽሐፍቶች ሕግን መማርና ማጥናት ጀመርሁ፡፡በዚህ ትጋቴ ያገኘሁት አስደናቂ ነገር፣የጓደኞቼን ሕጋዊ እንቆቅልሽ መፍታት መቻሌ ነበር፡፡በእስር ቤት ያሉ ጓደኞቼ እስከ ዋናው ፍርድ ቤት ድረስ ጉዳያቸውን እንዲታገሉ መርዳቱ አንዱ ዋና ሥራዬ ሆነ፡፡ብዙዎችንም ረዳሁ፡፡ከዚህም የተነሣ እስር ቤት ውስጥ ያሉ ጓደኞቼ “የእስር ቤት ጠበቃ” ብለው ስም አወጡልኝ፡፡

አኒ ገና የትምህርት ቤት ጓደኛዬ ነበርችና ደብዳቤ እየላከች፣እየደወለችና እየጐበኘችኝ በጣም ተቀራረብን፡፡ብዙ ሰዎች እንደ እኔ ያለውን ሰው ይገፋሉ፡፡ነገር ግን የኔ ቤተሰቦች ይጸልዩልኝ ነበር፡፡እናቴ መንፈሳዊ መጽሐፍትን ትልክልኝ ነበር፤እባክሽ አትላኪልኝ እያልኩ ተስፋ ባስቆርጣትም፡፡ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በመጽሐፎቹ እየተሳብኩ ማንበብ ጀማመርኩ፤ነገር ግን ምነው እግዚአብሔር ረሳኝ እያልኩ መስጋቴ አልቀረም፡፡ወደ እሱ ለመመለስም ምንም የውስጥ ዝግጁነት አልነበረኝም፡፡ይህ ሁኔታዬ የበለጠ ፈራ ተባ አደረገኝ፡፡

ብዙ ጠዋቶችን ሮበርት የሚባል ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዘ ለ 20 ዓመት የታሰረ ባልደረባዬን እጐበኝ ነበር፡፡ሮበርት በብዙ ጉዳዮች መሪር ሕይወት ነበረው፡፡አንድ ቀን እንደ ልማዴ ልጐበኘው ስሄድ፣ክፍሉን እያፀዳ ሲያሸበሽብ አገኘሁት፡፡ “ዛሬ ምን አገኘህ አልኩት?” ብዬ ስጠይቀው ፣ “ጌታን አገኘሁ” ብሎ መለሰልኝ፡፡ውስጡ ስለተለወጠ፣በጥቂት ቀናት ውስጥ እንዲታሰር የመሰከረበትን ወኅኒ ቤት የሚገኝ ታራሚ ማረው፡፡ሌላው ገራሚ ነገር፣ከትንሽ ጊዜ በኋላ ተፈትቶ ከቤተሰቡ ጋር ተቀላቀለ፡፡ከዚያም እየተመላለሰ በወኅኒ ቤት ውስጥ የነበረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይመራ ጀመር፡፡

በ2009 ዓ.ም ሥራ በማይገኝበትና ከባድ የኢኮኖሚ ችግር (recession)በነበረበት ጊዜ ተፈታሁ፡፡ቢሆንም በእግዚአብሔር ምሕረት ፣በጥቂት ጊዜ ውስጥ የጠበቆች ረዳት ሆኜ ተቀጠርሁ፡፡ወዲያውም ከአኒ ጋር ተጋባን፡፡በጋብቻችን ክብረ በዓል ላይ ማርቲ ባርናርትን መልእክት  አቅራቢ እንዲሆን ጋበዝነው፡፡አኒ ግን ብዙም አልተስማማችም ነበር፡፡የቅድመ-ጋብቻ የምክክር አገልግሎት ከሰጠን በኋላ ግን እጅግ በደስታ መስማማቷን ገለፀችልኝ፡፡

የመጀመሪያው የምክክር ክፍለ ጊዜ በሕይወቴ እጅግ የማይረሳ ሆነና አለፈ፡፡ማርቲ ስለ ኢየሱስ የምናውቀውን ነገሮች ጠያየቀን፡፡ከዚያም ስለ ጸጋ በሚገባን መንገድ አስተማረን፡፡እንዲያው በነፃ የምንቀበለው ስጦታ እንደ ሆነ ገለፀለን፡፡ባቀረበልን መልእክት ልቤ በኃይል ተነክቶ፣ “ለመሆኑ አምስት ባንክ የዘረፈ ሰው ይማራል ነው የምትለኝ?” ብዬ ጠየቅሁት፡፡ውስጤ በግትርነትና በራስ ወዳድነት ተሸብቦ ነበርና አስቸግሬው ነበር፡፡እሱም ኤፌሶን 1፡7-8 ያለውን በማብራራት የእግዚአብሔር ጸጋ በብቃት እንደሚችል በተረጋጋ ሁኔታ አበሰረኝ፡፡ክፍሉ እንዲህ ይላል፡-

“ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፤በጸጋ ድናችኋልናበሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፣ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን።ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም” (ኤፌሶን 2፡5-8)

ክፍሉን ደጋግሜ ሳነበውና ሳሰላስለው፣ውስጤን ገለባበጠው፡፡አእምሮን የሚያልፍ ሰላም አጥለቀለቀኝ፡፡አምላኬን በብዙ የደስታ እንባ እያመሰገንሁ ውዬ ማደር ሆነ፡፡ነፍሴ በደስታና በሐሤት ዘለለች፡፡የእኔን የሕይወት ለውጥ አይታ አኒ ሕይወቷን ለኢየሱስ አስረከበች፡፡ብዙ ሳንቆይም ግሩም በሆነ ሥነ-ሥርዓት የውኃ ጥምቀት ተጠመቅን፡፡አሁን ለዚህ ለከበረ ጸጋ እጅ ወደ ላይ ካልኩ አምስት ዓመት ሆኖኛል-አምስት የነፃነትና የእፎይታ ዓመት! ከአኒ ጋር ጥቂት ዓመት አብረን ከኖርን በኋላ፣ጌታ ጸጋ የሚል ስም ያወጣንላትን ውብ ቆንጆ ልጅ ሰጥቶ ባረከን፡፡

በዚህ ሰዓት በሕግ ትምህርት ከታወቀ ትምህርት ቤት ዲግሪዬን ሠርቻለሁ፡፡እግዚአብሔር ሕይወቴን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ባርኮታል፡፡መረዳት ከምችለው በላይ ሕይወቴን አለምልሞታል፡፡ስሙ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይባረክ!

“በሰማይና በምድር የተዋረዱትን የሚያይ፤ከአለቆች ጋር ከሕዝቡም አለቆች ጋር ያኖረው ዘንድ ችግረኛን ከመሬት የሚያነሣ፣ ምስኪኑንም ከፋንድያ ከፍ ከፍ የሚያደርግ……….ሃሌ ሉያ!” (መዝሙር 113፡6-9)