Friday, February 20, 2015

ሰማያዊ ሸክም




ሰማያዊ ሸክም

በውስጣችን እውነተኛ የሆነ ከአርያም የሆነ ሸክም ሲኖር አያስተኛንም፣ያስቃትተናል እንጂ፡፡እረፍት አይሰጠንም፣ መለቀቅ እስኪሰማን ድረስ በጉልበታችን ያስኬደናል እንጂ፡፡በእንደዚህ ዓይነት መሰጠት፣ጽኑነትና፣ትጋት የሚጸለይ ጸሎት ደግሞ ብዙ ፍሬን ማፍራቱ አይቀሬ ነው፤ባለፉት ዘመናት በነበሩ ብዙ የእንባ ሰዎች ታይቷልና፡፡


ወደ ጌታ ከልብ የሆነ ጩኸትና መቃተት ፡-
·       እውነተኛ ትሕትናን
·       ያለ ምንም ሁኔታ ራስን መስጠትን
·       “ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም” (ዮሐንስ 15፡5) የሚለውን የጌታን ቃል አጥብቆ መረዳትን
·       ጨክኖ ከጌታ በረከትን ሽቶ ራስን በፊቱ መጣልን(desperation) ይወክላል ወይም ያመለክታል፡፡

ንጉሥ ዳዊት በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ነው “በጨነቀኝ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፣ወደ አምላኬ ጮኽሁ፤ከመቅደሱ ቃሌን ሰማኝ፣ጩኸቴም በፊቱ ወደ ጆሮው ገባ” (መዝሙር 18፡6)ብሎ የተናገረው፤በእውነትና በመንፈስ የተጸለይ ጸሎት ከጣሪያ እንደሚያልፍና ውጤትና ፍሬ እንዳለው ሲያበስር፡፡


አዎ! ልክ እንደ ዳዊት ሸክም ያላቸው፣ራእይ ያረገዙ፣ለትውልዱ የሚያስቡና ለቤተ ክርስትያን የሚጨነቁ ሰዎች ይማልዳሉ፣ይቃትታሉ፣ይጮኻሉ፣በመንፈስ ኃይል ወደ እግዚአብሔር ማደሪያ ይገሠግሣሉ፡፡ታዲያ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ሲበዙ ቤተ ክርስትያን በፍሬ እንደምትሸፈን ምን ጥርጥር አለው? ቃሉ እንዲህ ይላልና፡-


“…ጕልበቴን ይያዝ፣ከእኔ ጋር ሰላም ያድርግ፤ ከእኔ ጋር ሰላም ያድርግ።በሚመጣው ዘመን ያዕቆብ ሥር ይሰድዳል፣እስራኤልም ያብባል ይጨበጭብማል፤በፍሬያቸውም የዓለሙን ፊት ይሞላሉ።”(ኢሳይያስ 27፡5-6)

 
ከመቸውም ዘመን ይልቅ የጌታ ጉልበት በጸሎት ሊያዝበት የሚገባው ዘመን መቼ ነው ካላችሁኝ አሁን ይመስለኛል፡፡ምክንያቱም ሁኔታው ሁሉ እየጨለመ ነውና ነው፡፡ሰይጣንም በታላቅ ቁጣ ምድሪቷን ሊያተራምስ ወጥቷልና ነው፡፡እናም ያለ ጌታ አስተማማኝ ምንም መጠጊያ የለምና ነው፡፡ባለቀ ሰዓት ሳምሶን ምሰሶውን እንዲያስይዙት እንደሻና ወስኖ እንደለመነ፣የጌታን ጉልበት ለመያዝ እጅግ በኃይል መሻት ያስፈልጋል ብዬ አስባለሁ፡፡በተጨማሪም በዚሁ አንቀጽ ከጠቀስኩት ምክንያቶች ጋር በተያያዘ በዙሪያችን የፈረሱ ነገሮችን በመንፈስ እያዩ፣መቃተት፣ማልቀስና መጮኽ ይገባል የሚል እሳቤ አለኝ፡፡አዎ!ዙሪያችንን ብንቃኝ ብዙ የፈረሱ ነገሮች አሉ፤በብዙዎች ዘንድ ትዳር፣ሕብረት፣በወንድማማችነት አብሮ መሥራት ፈርሷል፤መከፋፈል ገኖ አንድነት ጠፍቷል፤አንዱ አንዱን የመሸከሚያ ትከሻ ሳስቷል፡፡ግለኝነት አይሏል፤ሌላም ሌላም፡፡


ይህ ትውልድ የፈረሰውን ቅጥር በመንፈስ ዐይተው፣አያሌ ቀን የሚያዝኑ፣በሰማይ አምላክ ፊት የሚጾሙና የሚጸልዩ (ነህምያ 1፡4) ሰዎችን ይፈልጋል፡፡በልቅሶና በምጥ በጌታ ፊት ወድቀውና በመቃተት ጨርሰው፣በተግባር ለሥራ የሚነሱ ሰዎችን ይፈልጋል፡፡እርግጠኛ ነኝ፣መንፈሴም ይመሰክርልኛል፤ጌታ በዚህ ሰዓት በብዙ መቃተትና ምልጃ ወደ እሱ የሚያነቡ ሰዎችን ይፈልጋል፤ለሕዝቡ የሚገደው ጌታ በኢሳይያስ መጽሐፍ ላይ እንዲህ ብሏልና፡-


“ኢየሩሳሌም ሆይ ጉበኞችን በቅጥርሽ ላይ አቁሜአለሁ፤ቀንና ሌሊት ከቶ ዝም አይሉም፤ እናንተ እግዚአብሔርን የምታሳስቡ፣ኢየሩሳሌምን እስኪያጸና በምድርም ላይ ምስጋና እስኪያደርጋት ድረስ አትረፉ ለእርሱም ዕረፍት አትስጡ።”(ኢሳይያስ 62፡6-7)


ለቤተ ክርስትያን ትክክለኛ ጉዞና ተጽእኖ ቀንና ሌሊት ዝም የማይሉ ጉበኞች ያስፈልጋሉ፡፡ለዚህ ነው እግዚአብሔር እንድንጠራው፣እንድንጮኽ፣እንድንቃትትና ያለ መታከት ፊቱን እንድንፈልግ ደጋግሞ በቃሉ የተናገረው፡፡ከተናገራቸው ውስጥ እጅግ የምወደውን ከበድ ያለ የተስፋ ቃል የያዘውን አንድ ቃል እዚህ ላይ ጣል ላድርግ፡-
“በመከራ ቀን ጥራኝ፣አድንህማለሁ፤አንተም ታከብረኛለህ” (መዝሙር 50፡15)
በዚህ ምንባብ ሦስት በውጤት ሂደት የተሰናሰሉ ነገሮችን ነው የምናስተውለው፡፡ እንደሚከተለው እንዳስቀምጣቸው ይፈቀድልኝ፡-

እሱን በጸሎት እንጠራዋለን--------›ያድነናል(እንደ ሕይወታችን ዓይነት ከተለያየ ጉድ እንድናለን/ቤተ ክርስትያን ትታደሳለች፣ትጠራለች )------------›እሱን እናከብረዋለን

“ጥራኝ” የሚለውን ቃል በተለያዩ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱሶች ላይ ሳየው “cry out” የሚል ትርጉምን ይዟል፡፡ ይህ ቃል “ጩኽ” የሚለውን በኤርምያስ 33፡3 ላይ ያለውን ቃልም ያመለክታል፡፡ታዲያ የጌታ መንፈስን ታዝዘን አብዝተን ስንጮኽና ስንቃትት፣ለውጡ እኛ ላይ ነው የሚጀምረው፡፡ከብዙ ከጌታ ካፈነገጡ ነገሮች እንድናለን፡፡ማለትም የጌታ መንፈስ ውስጣችንን እስክንደነቅ ድረስ በፈውሱ ይገበኘዋል፡፡ቀጥሎም የእግዚአብሔር ቃል “ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ በዚህ  አባቴ ይከበራል” (ዮሐንስ 15፡8) እንደሚል የመንፈስ ፍሬዎች በሕይወታችን ስለሚያብቡ ከሩቅ የምናበራና ለብዙዎች ክርስቶስን የምናሳይ መልእክት እንሆናለንና በዚህ ጌታ ይከበራል፡፡አዎ! ውጤቱ እጅግ አስደናቂ ነው፤ጌታ በሕይወታችን ይከብራልና ይከበራል፡፡እናም ክብሩንና የማዳኑን ኃይል ዐይተን፣እሱን በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ እናከብረዋለን፡፡የሚጓጓለት ለውጥ!


ጌታ ሆይ አብዝተን እንድንጮኽ እርዳን!






No comments:

Post a Comment