Friday, February 20, 2015

እጆችህ ሠሩኝ አበጃጁኝ



እጆችህ ሠሩኝ አበጃጁኝ


የእግዚአብሔር ቃል እጅግ ብዙ ሥራን ይሠራል፡፡ የጌታ መንፈስ በነቢዩ ኢሳይያስ ከእኔ አፍ የሚወጣው ቃል፣መንፈስ የሆነው ቃል ወይም የጊዜው ቃል የምሻውን ያደርጋል የላክሁትን ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም (ኢሳይያስ 5510-11 አጽንኦት የእኔ) ብሎ ተናግሯል፡፡እውነት ነው መንፈስ የሆነው ቃል ከእግዚአብሔር አፍ ሲወጣ በከንቱ አይወድቅም፡፡አብዛኞቻችን ወደ ጌታ የመጣነው በአንድ ወቅት ይህ የተሳለ ቃል ውስጣችን መተከያና መብቀያ ቦታ ስላገኘ ነው፡፡የዕብራውያን ጸሐፊ የእግዚአብሔርን ቃል ሲገልጸው የሚሠራ እና ሁለት አፍ ካለው ሰይፍ የተሳለ እና ወደ ጠለቀው ማንነታችን ዘልቆ ልባችንን እንደሚመረምር እና በእርሱ ፊት ሁሉ ነገር የተገለጠ እና የተራቆተ (ዕብራውያን 412-16) እንደሆነ ይናገራል፡፡አዎ የሚሠራ ነው፤ነፍስን ይመልሳል፣ደስታን ይሰጣል፣ከብዙ ጥፋት ያወጣል፣መንገድን ያቀናል ወዘተ፡፡


በምሳሌ መጽሐፍ ላይ “ቃልም በጊዜው ምንኛ መልካም ነው፡፡በታች ካለው ከሲዖል ያመልጥ ዘንድ የሕይወት መንገድ አስተዋዩን ሰው ወደ ላይ ይወስደዋል (ምሳሌ 1523-24)  የሚል ቃል እናገኛለን፡፡ ቃልም በጊዜው ምንኛ መልካም ነው የሚለው አሳብ በጊዜው ወይንም በሚፈለግበት ሰዓት በእግዚአብሔር መንፈስ ስለተነገረ የእግዚአብሔር ቃል ነው የሚጠቁመው፡፡የእንደዚህን አይነት ቃል ውድነት ሲናገር ምንኛ መልካም ነው ይለዋል፡፡ማለትም ሥራን የሚሠራ፣ለውጥን የሚያመጣ፣ካለንበት ማጥ የሚያወጣ ባለውለታ የሆነ ቃል እንደሆነ ነው የሚያሳየን፡፡ይህ ቃል በታች ካለው ከሲዖል ያመልጥ ዘንድ የሕይወት መንገድ አስተዋዩን ሰው ወደ ላይ ይወስደዋል ከሚለው አሳብ ጋር ተያያዥነት ያለው ይመስላል፡፡አዎ!ይህ የጊዜው ቃል ነው ከሲዖል የሚያስመልጠው፡፡“ሲዖል” የሚለው ቃል ማንኛውንም እኩይ የሆነ ነገር ሁሉ ይወክላል፡፡ወደ ላይ ይወስደዋል የሚለው አሳብ ደግሞ መንፈስ የሆነው ቃል ብርቱ እንደሆነና ከብዙ ጉድ ማውጣት እንደሚችል ያሳየናል፡፡ይህ ቃል ሰው ከሞት ወጥመድ ያመልጥ ዘንድ የጠቢብ ሰው ትምሕርት የሕይወት ምንጭ ነው(ምሳሌ1314)  ከሚለው ቃል ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡እርግጥ ነው፣ቃሉ እያስጠነቀቀን፣ማስተዋልን እየቸረን፣የመለየትን ጸጋ እየሰጠንና አቅጣጫንና ጎዳናን እያስለወጠን፣ከብዙ የሞት ወጥመዶች ያስመልጠናል፡፡


ኢየሱስ ቃሉ ውስጣችን ገብቶ ስለሚሠራው ግሩም ሥራ ሲናገር እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል(ዮሐንስ 831-32) ብሏል::ከጽኑ ባርነት ይገላግላል ነው ያለን፡፡በግሌ የቃሉን ኃይል በሕይወቴ አይቼዋለሁ፡፡መንፈስ የሆነው ቃል ከብዙ ጉድ እንደሚያወጣን ሕያው ምስክር ነኝ እላለሁ፡፡በተግባር ደረጃ ይህ የሕይወት ቃል ወደ ውስጤ በመግባቱ ከመጠጥ፣ከጫትከሲጋራ ሱስ እና ከብልሹ ማኅበራዊ ሕይወት መንጭቆ አውጥቶኛል፡፡ሳስበው ይገርመኛል፣እላዬ ላይ የነበረው የሱስ ቀንበር ቀላል አልነበረም::ቢሆንም ይህ ኃይል ያለው ቃል ነፃ አድርጎኝ በነፃነት ተለቅቄ ያለ ምንም ባርነት እየኖርኩ እገኛለሁ፡፡
የጠላትን ተግዳሮት የምናሸንፍበት ዋና መሣሪያችን ይህ ኃይል ያለው የእግዚአብሔር ቃል ነው፤መጽሐፍ እንዲህ ይላልና፡-

ኃያል ሆይ ፍላጻዎችህ የተሳሉ ናቸው፤እነርሱም በንጉሥ ጠላቶች ልብ ውስጥ ይገባሉ አሕዛብም በበታችህ ይወድቃሉ(መዝሙር 455)


ይህ ቃል የሚናገረው ሬማ ተስሎና ተዘጋጅቶ በአፋችን ላይ የተዘጋጀ ቃል ሊያመጣ ስለሚችለው ውጤት ነው፡፡በሕይወታችን መንፈስ የሆነው ቃል ማንኛውንም ተግዳሮት ጥሶ የመግባትና ነገሮችን የመለወጥ ችሎታ አለው፡፡የአጋንንትን መረብና እቅድንም መቆራረጥ ይችላል፡፡አንድ ወቅት የምሠራበት ቦታ የማይመች ነበረና ወደ ጌታ በዛ ጉዳይ እጸልይ ነበር፡፡አንድ ፓስተር ወደ ምሠራበት ቢሮ መጥቶ ልጸልይልህ አለኝና ‹‹የጌታ መንፈስ ጠላቶችን ጣልሁልህ ይልሃል››ብሎ አጭር ትንቢታዊ መልእክት ነግሮኝ ሄደ፡፡ያ መልእክት የጊዜው መልእክት ስለነበር ልረሳው በማልችለው ሁኔታ አሁንም ልቤ ውስጥ ተቀርቅሮ አለ፡፡ከዚያ በኋላ በትንሽ ጊዜ ውስጥ ያን አስቸጋሪ ቦታ ለቅቄ በብዙ መስፈርት የሚሻል ቦታ መሥራት ጀመርሁ፤የጊዜው ቃል ሲመጣ ነገሮችን በፍጥነት ሊለውጥ ይችላልና፡፡


ቃሉ ለሕይወታችን ውበትን የመስጠት ችሎታ አለው፡፡ንጉሥ ዳዊት ‹‹እጆችህ ሠሩኝ አበጃጁኝም›› (መዝ 11973)  እንዳለውቃሉ እያቀና እና እያስተካከለ ሕይወታችንና ፍጻሜያችንን ይለውጣል፡፡በጥበብ፣በሞገስ፣በእምነት እና በፍቅር እንድናድግ እያደረገ ደምቆ የሚታይ መልእክት ያደርገናል፡፡እንዲሁም መንፈስ የሆነው ቃል ውስጣችንን በመሥራትና በመቀየር እንደ ጌታ ፈቃድ የሆነ መስዋዕትን እና አምልኮ እንድንሰዋ ያደርገናል፤ቃሉ እንደዚህ እንደሚል፡-

አቤቱ በውዴታህ ጽዮንን አሰማምራት የኢየሩሳሌምን ቅጽሮች ሥራ፡፡የጽድቁን መስዋዕት መባውንም የሚቃጠለውንም መስዋዕት በወደድህ ጊዜ ያን ጊዜ በመሰዊያህ ላይ ፍሪዳዎችን ይሰዋሉ(መዝሙር 51፡18-19)


እውነት ነው፡፡ውስጣችን በሚገባ ሳይሠራ የምንሰዋው መስዋዕት ምሥጋናም ሆነ አምልኮ ከጣራ አያልፍም፡፡ነገር ግን ለቃሉ ያልተከፋፈለ ልብን ሰጥተን በበቂ ሁኔታ ከከተመገብነውካጠናነው እና ካሰላሰልነው ውስጣችንን ከምናስበው በላይ ይሠራዋል፣ያሠማምረዋል፡፡ስለዚህም አምልኮአችን እና ስግደታችን እውነተኛ(authentic) እና በጌታ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ይሆናል፡፡


ጌታ ሆይ ፍጻሜያችንን የሚያሳምረውን የቃልህን ደጆች ክፈትልን፤በቃልህ ውስጥ ያለውን እንቁ እንድናይ አይኖቻችንን አብራልን!




No comments:

Post a Comment