የጸጋው ዙፋን
የጸጋው
ዙፋን የምሕረት ቦታ፣የሕክምና ቦታ እና የፈውስ ቦታ ነው፡፡ታዲያ ይህንን ቦታ ልዩ የሚያደርገው የጌታ ሕልውና ስላለ ነው፡፡
በዚህ
ዘመን ሰይጣንና አጋንንቱ ሌሎች ተግባሮችን ስናከናውን ምንም ግድ አይሰጣቸውም፡፡ለመጸለይ ስናስብ ግን አዚማቸውንና ጦርነታቸውን
ይለቃሉ፡፡ደፍረን ለጸሎት ስንበረከክ ደግሞ ስልቹ ሆነን እንድናቋርጥ፣እንድንታክት፣ እንቅልፍ እንዲጫጫነን እናም ቶሎ ጸሎቱን
ጨርሰን ወደ ሌላ ጉዳይ እንድንሄድ የማያደርጉት ነገር የለም፡፡የጸሎትን ጥቅም ማሣነስም ትልቁ መዋጊያ መሣሪያቸው ነው፡፡
በግል
ሕይወቴና ጥሩ የጸሎት ልምድ ካላቸው ሰዎች እንደታዘብኩት፣ጸሎት እጅግ ብዙ ጥቅም አለው፡፡ከሁሉም ሊተኮርበት የሚገባው ጥቅም
ግን ውስጣችን መለወጡ ነው፡፡ውስጣችን ዕለት ዕለት መታደሱ ነው(2 ቆሮንቶስ 4:16)፡፡ልባችን በደስታና በሰላም መረጋጋቱ
ነው፡፡ልባችን በመንፈስ ፍሬዎች መሞላቱ ነው፡፡መንፈሳችን መጠንከሩ ነው፡፡
ከላይ
እንደጠቀስሁት እንዳንጸልይ የማይመጣ የጠላት ተፅዕኖ የለም፡፡ነገር ግን እነዚህን ተግዳሮቶች ሁሉ ተቋቁመን ብንጸናና በጸሎት
በጸጋው ዙፋን ፊት በቂ ጊዜን ብናሳልፍ፣ሕይወታችን እንደ እሱ ፈቃድ ይለወጣል፡፡ ቃሉ “ታምነን በእምነት እንጂ በማየት አንመላለስም” (2 ቆሮንቶስ 5፡6) እንደሚል ሁኔታዎችን ሳንመለከት
በእምነት በፊቱ ብንሆን ሕይወታችን ይለመልማል፡፡አቅም ባጣንባቸውም ነገሮች ላይ ጉልበት እናገኛለን፡፡
የእግዚአብሔር
ቃል “ዕረፉ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ እወቁ” (መዝሙር
46፡10) ብሎ ይናገራል፡፡ቃሉ “ዕረፉ” ሲል እሱን
ታምነን፣በፊቱ እየጸለይን፣ቃሉን እየተመገብንና በእግሩ ስር ሆነን እሱን እየጠበቅን መሆኑን ልብ ይሏል፡፡የእግዚአብሔር ቃል በሱ
ፊት ሰከን ያለ ጊዜ ወስዶ “ዕርፍ” ማለት ያለውን ጥቅም
ሲናገር “በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፤በጸጥታና በመታመን ኃይል
ይሆንላችኋል” (ኢሳይያስ 30:15) ይላል፡፡በሌላ ቦታም “እግዚአብሔርን
በመተማመን የሚጠባበቁ ኃይላቸውን ያድሳሉ”(ኢሳይያስ 40፡31) የሚል የተስፋ ቃል አለልን፡፡ ስለዚህ ዓይነት ዕረፍት
ኢየሱስ ሲናገር፣“ማርያም መልካም ዕድልን መርጣለች ከእርሷም
አይወሰድባትም” (ሉቃስ 10:42) ብሏል፡፡በሚገባ ከተዘወተረ የማይወሰድ ዕድል!
በግሌ
እንዳልጸልይ ተግዳሮት ሲበዛብኝና ጊዜዬ ሲባክን እጅግ በጣም አዝናለሁ፡፡ለተወሰኑ ቀናት በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ
አሳልፌ፣ተግዳሮቶቹን ሁሉ ጥሼ በመንበርከክ፣የመለቀቅና የመፈታት መንፈስ ሳይታወቀኝና በቂ ሕክምና ሳላገኝ አልነሳም ብዬ እወስናለሁ፡፡ጸሎት መሰጠትንና ውሳኔን
ይፈልጋልና፣ሁሉን እርግፍ አድርጌ ትቼ በፊቱ እሆናለሁ፡፡እናም እንዲህ ዓይነቱ የውሳኔ ጸሎት ባይበዛም በማልረሳው መልኩ ባርኮኛል፡፡ታዲያ
ይህ ዓይነቱ ጸሎት ዘወትር ሳይቋረጥ ቢቀጥል ሕይወቴ እንዴት እንደሚለወጥና እንደሚያድግ በማሰብ አምላኬን በእንደዚህ ዓይነት ጊዜዎች
እንዲባርከኝ እየተማጸንሁት እገኛለሁ፡፡
የምር የሆነ ጸሎት(authentic
prayer) ከምር የሆነ ራብንና ጉጉትን ይፈልጋል፡፡ለዚህ ነው ቃሉ “ጽድቅን
የሚጠሙና የሚራቡ ብፁዓን ናቸው፣ይጠግባሉና”
(ማቴ 5፡6)ብሎ የተናገረው፡፡ይህ ዓይነቱ መንፈሳዊ ራብና ጥማት እያየለ ሲሄድ፣ሌላውን ረብ የሌለውን ራብና ጥማት
ይውጠዋል፡፡ወደ ጸጋው ዙፋን በቀረብን ቁጥር፣እየተሳብን የጸሎት ጸጋ በሕይወታችን እየጨመረ አስደናቂ ኡደት (positive
cycle)ውስጥ እራሳችንን እናገኘዋለን፤ነገር ግን በመቅረብ ነው የሚጀምረው!
“እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ
የሚረዳንን
ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ!” (ዕብራውያን
4፡16)
No comments:
Post a Comment