Saturday, February 7, 2015

እንታጠቅ፣እንንቃ



እንታጠቅ፣እንንቃ


ሰሞኑን በቪኦኤ በሰማሁት ቃለ ምልልስ ማዘኔን አልዋሻችሁም፡፡ እጅግ አዝኛለሁ፡፡ቢሆንም ወደ ጉዳዩ ዝርዝሩ አልገባም፣ምንም አይጠቅመንምና፡፡እንደ ጦማሪ ግን የራሴን ምልከታ ጽፌአለሁ፤እነሆ፡-


ቃለ ምልልሱን ከሰማሁ በኋላ ወደ ራሴ ማየት ነው የጀመርሁት፡፡በግሌ የክርስትያን ሕይወት የሚጠይቀው ጥንካሬ፣መሰጠት፣ትጋትና ፅናት እንደሚፈለግብኝ መጠን የለኝም፡፡ታዲያ አንድ የፈተና ጐርፍ ቢመጣ ይዞኝ እንደሚሄድ እያሰብሁ፣ውስጤ በሙግት ነው የከረመው፤“ወገንህ ሲታማ፣ለእኔ ብለህ ስማ” እንዲሉ! 


የምር የምሩን እንነጋገር ከተባለ፣ቢያመንም በውስጤ የማምንበትን ልበላችሁ፡፡በአሁኑ ወቅት ጠላት ሸርሽሮን፣ጉልበታችን በእንግዶች ተበልቶ እየተንገዳገድን ነው ያለነው፡፡አፋችን ያወራል፡፡ዝማሬ ሞልቷል፡፡ጥቅስ መጥቀስ እንደ ልብ ነው፡፡የሚዳሰስ ክርስትና ግን በብዙዎች ዘንድ አይታይም፡፡በጥቅሉ በቃሉ ብርሃን ሲታይ እጅግ ብዙ የቤት ሥራ ይጠበቅብናል፡፡ይህንን ፀሐይ የሞቀ ሃቅ መቀበልና፣ምን እናድርግ የሚለው ላይ ትኩረት ማድረጉ አስተዋይነት ነው እላለሁ፡፡አለበለዚያ ግን አስመሳይነቱ ይቀጥላል፤ጉዳታችንም ሌሎች ጉዳቶችን እየወለደ ይሄዳል፡፡


የእግዚአብሔር ቃል ባለጋራ እንዳለን ደጋግሞ ያስጠነቅቀናል፡፡እንዳውም “ሊውጠን” እንደሚፈልግ ተፅፏል፤እንዲህ በማለት፡-


“ባላጋራችሁ ዲያቢሎስ የሚውጠውን ፈልጐ እንደሚያገሣ አንበሳ በዙሪያችሁ ይዞራል::በመጠን ኑሩ ንቁም ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት”(1ጴጥሮስ 5፡8-9)


ይህንን ቃል ሰሞኑን ሳስብ ትኩረቴን የሳበው “ይዞራል” የሚለው ቃል ነው፡፡አዎ! ባላጋራችን እረፍት የለውም ይዞራል፡፡ትጉህ ነው፤የሚጥለውን ሰው እስኪያገኝ ድረስ አይተኛም፡፡ከጣለን በኋላ ብዙ ነው ጉዱ፡፡እግዚአብሔር በምሕረቱ እስኪያነሣን ድረስ፣ያለው ስብራት ቀላል አይሆንም፡፡እንዲህ የሚያደባና የማይተኛ ጠላት ካለን፣የሌላው ወገናችን ጉድ ላይ ጊዜ መግደሉ ምን ይጠቅመናል? ተረኛ ላለመሆን መጋደሉ ነው ሊታሰብበት የሚገባው፡፡


ሕይወቱ ኃይለኛ መሆንን ይፈልጋል(ማቴዎስ 11፡12)፡፡ቆራጥነትን ይጠይቃል፡፡እምቢተኝነትን ግድ ይለናል፡፡ብዙውን ጊዜ በጌታ እግር ስር በፅሞና መሆን፣ቃሉን ማሰላሰል እናም ደግሞ በተግባር ቃሉን በድርጊት በሕይወታችን መተርጐም ይጠይቀናል፡፡እናም “ተው፣ተመለስ” እያለ በለሆሳስ የሚናገረንን የጌታን ድምፅ ስንሰማ  መታዘዝ ይገባናል፡፡አዎ! እጅግ ንቁ መሆን ይገባናል ብዬ አምናለሁ፡፡በብዙ ተማፅኖና ጩኸት በፊቱ መሆን ይገባናል፤እንዲህም እየተተጋ እንኳ ድጡ ከባድና አስፈሪ እየሆነ ነውና!


ብዙ ሰዎች በዝማሬና በስብከት ብቻ ነው የሚኖሩት፡፡የሰዎችን የንባብ ሕይወት በግሌ እሰልላለሁ፡፡በዙሪያዬ ያሉ በርከት ያሉ ሰዎች፣የማንበብና የጸሎት ልምዱ የላቸውም፡፡በቅንጥብጣቢ ስብከትና የትንቢት መልእክት ተንጠልጥለው፣በጠኔ ያሉም አይጠፉም፡፡አንድ ሰው በቤተ ክርስትያኑ ውስጥ ሊሸጡ የተዘጋጁትን የመጽሐፍት ብዛት ሲነግረኝ፣ማመን አቅቶኛል፡፡የረጅም ጊዜ መንፈሳዊ ልምምድና ብስለት ያላቸው ደራሲያን መጽሐፍት በመደርደሪያ ላይ ተሰድረው እንደሚገኙ ነገሮኛል፡፡ገንዘብ የሚያደርጋቸውና ይዟቸው የሚሄድ ሰው አጥተው ለረጅም ጊዜ አሸልበዋል፡፡“ሰው የመዝሙር ካሴት ብቻ ነው የሚገዛው” ብሎ እጅግ እያዘነም ነው ያጫወተኝ፡፡ከዚህ በላይ ምን የሚያሳዝን ጉዳይ ኖሮስ ነው፣የአንድ ሰው ጉዳይ ስናብጠለጥል የምንከርመው!!


ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን አማኞች “በመንፈሱ በውስጥ ሰውነታችሁ በኃይል እንድትጠነክሩ”(ኤፌሶን 3፡16) ብሎ ማልዷል፡፡እጅግ አስፈላጊ በቀጣይነት በሕይወታችን ሊጸለይ የሚገባ ጸሎት!ጳውሎስ በመንፈሳዊ ሕይወታችን መጠንከራችን መንፈስ ከሆነው ቃል ጋር ያለን ቁርኝት መሆኑ ሲገልጽ “ለአሕዛብ ሁሉ የታወቀው ምሥጢር እንደ ተገለጠ መጠን ሊያበረታችሁ ለሚችለው ብቻውን ጥበብ ላለው  (ሮሜ 16፡26) ብሏል፡፡እንደ ተገለጠልን መጠን ነው መንፈሳችን የሚጠነክረው፡፡ቆመን በጽኑነት መራመድ የምንችለው፡፡እስቲ አስቡት መንፈሳችን ካልጠነከረ፣እንደ ጐርፍ እየመጣ ያለውን የጠላት ከበባ እንዴት እንቋቋማለን? መንፈሳችን የሚጠነክረው ደግሞ ቃሉን ሳናሰልስ በመብላት ነው፡፡በማሰላሰል ነው፡፡ከጾምና ከጸሎት ጋር በማጣመር በልባችን ላይ ሲጻፍ ነው፡፡አለበለዚያ ግብዞችና አስመሳዮች ሆነን እንቀጥላለን፡፡ፈተና ሲመጣም ተልፈስፍሰን መውደቅ ብቻ ይሆናል እጣ ፈንታችን፡፡


የእግዚአብሔር ቃል “ስለዚህ ቅዱስ ሁሉ በምቹ ጊዜ  ወደ አንተ ይለምናል፣ብዙ የጥፋት ውኃም ወደ እርሱ አይቀርብም/Therefore every godly person should pray to you at such a time. Surely a flood of great waters will not reach him(ISV)” (መዝሙር  32:6) ይላልና አስቀድመን በበቂ ሁኔታ እንታጠቅ! እንንቃ ! 

ቸር እንሰንብት!

No comments:

Post a Comment