Saturday, February 21, 2015

መለኮታዊ ጉብኝት(holy encounter with God)



መለኮታዊ ጉብኝት(holy encounter with God)

ባለፉት ዘመናት በጽሑፍ ላይ ያየናቸው መለኮታዊ የሆኑ ጉብኝቶችና ገጠመኞች ጊዜ አላለፈባቸውምአሁንም በዚህ ዘመን በሚገባ ይከሰታሉ፡፡

ከጌታ ጋር አብዛኛውን ጊዜ የምንገናኘው ቃሉን ስናነብና ስንጸልይ ቢሆንም፣አንዳንዴ እኛ ባለሰበነው መንገድ እራሱን ገልጦልን ሕይወታችን እስከወዲያኛው ሊቀየር ይችላል፡፡እንደዚህ ዓይነት ክስተት ብዙ ጊዜ ያልጠበቅነውና ራሱ ባቀደው ሰዓት ስለሚሆንበፍጹም በሕይወታችን ልንረሳው አንችልም፡፡አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ግን፣ይህን መለኮታዊ ገጠመኝ እኛ ልናቅደውና በፈቃዳችን ልንለማመደው አንችልም፡፡ከእኛ የሚጠበቀው መንፈሳዊ ጆሮአችንንና ዓይኖቻችንን ከፍተን ለመቀበል ንቁ መሆን ነው፡፡በእምነት ሆነን መጠበቅ ነው፡፡ሁሉን ቻይ የሆነውን ጌታ አለመወሰን ነው፡፡

መለኮታዊ ጉብኝቶች ወደ ሕይወታችን እንዳይመጡ ምን ከለከለን ? መልሶቹ የሚከተሉት ይመስሉኛል፡፡መሰጠትና ትጉሕ መሆን ጐድሎናል፤ልባችን በብዙ ነገር ተይዟል፤ጆሮዎቻችንና ዓይኖቻችን በሌሎች በማይረቡ ነገሮች ተደፍነዋል፤ጠበቅ አድርገን የጌታን ፊት መፈለግ አቃተን፤ዝርዝሩ ረጅም ነው!

መለኮታዊ  ጉብኝት(holy encounter) ሲመጣ ምንድነው የሚሆነው የሚለው ላይ ትንሽ ልበል፡፡ አንድ ስማቸውን የማላስታውሳቸው የእግዚአብሔር ሰው እንዲህ ብለዋል፡-
‹‹an encounter with God opens our eyes to recognize His unapproachable superiority/አርያም የሆነ ጉብኝት፣ጌታ የማይደረስበት ከፍ ያለ አምላክ መሆኑን እንድናውቅ ዓይኖቻችንን ይከፍታሉ›› እናም ጌታ በመለኮታዊ ጥበቡና ኃይሉ ሲገናኘን እንዲህ ይሆናል፡-
  • ሕልውናው ከወትሮው በሚገርም ሁኔታ ይታወቀናል
  • ያለሱ የማንረባ ሰዎች መሆናችን እንረዳለን
  • የእግዚአብሔርን መሐሪነት እንገነዘባለን
  • በተግባር ደረጃ ታዛዦች እንሆናንና ምን እንዳደርግ ትወዳለህ እንለዋለን
በኢዮብ መጽሐፍ ላይ ኢዮብ እጅግ ትሑትና ቅን ቢሆንም፣ወደ መጀመሪያ አካባቢ የነበረው መንፈሳዊ አቋም በሚቀጥለው ጥቅስ ተንጸባርቋል፡፡እንዲህ የሚል ነበር፡
ጽድቄን እይዛለሁ እርሱንም አልተውም ከቀኖቼ ሁሉ ስለ አንዱ ልቤ አይዘልፈኝም” (ኢዮብ 27፡6)

 ከጓደኞቹ ጋር በርከት ያሉ ምዕራፎች ሲከራከር ከቆየ በኋላ፣በመጨረሻ እግዚአብሔር ክብሩን ኃይሉንና ማንነቱን በሚገባው መንገድ ሲገልጽለት ከመጀመሪያው አቋሙ እጅግ የሚለይና የልብ መሰበር የታየበት ምላሽ ነበር የነበረው፡፡እንዲህ በማለት -
“መስማትን በጆሮዬ በመስማት ሰምቼ ነበር አሁን ግን ይኔ  የችህ ስለዚህ እራሴን እንቃለሁ፤በአፈርና በአመድ ላይ ተቀምጬ እጸጸታለሁ” (ኢዮብ 42፡5-6)
 
እጅግ የሚገርም እና ለጌታ የተንበረከከ ሰው ቋንቋ!ለዚህ ምላሽና መንበርከክ ያበቃው የእግዚአብሔርን ታላቅነትና ሁሉን ቻይነቱን በመንፈሱ ማየቱ ነው፡፡አዎ!እግዚአብሔርን በግርማውና በክብሩ ማየት አስደንጋጭና አስፈሪ ልምምድ ቢሆንም፣ በሕይወታችን የማንረሳውና በውስጣችን ታትሞ የሚቀር ስለሚሆን ለመንፈሳዊ ርምጃችን እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡አንድ የእግዚአብሔር ሰው በጻፉት መጽሐፋቸው ላይ የእግዚአብሔር ሰዎች ጌታን ለማገልገል ሲነሱ እንዲህ ዓይነት ገጠመኝ (traumatic experience) ቢኖራቸው መልካም ነው ይላሉ፡፡እንዲህ ዓይነት ጉብኝት(holy encounter) በሕይወታችን ሲከሰት፣በምልልሳችን ላይ ግሩም ለውጦችን ያመጣል ፡፡ለምሳሌ የልብ መሰበር፣ጥልቅ ንስሐ፣በቃላት መናገር የማይቻል ደስታና መረጋጋት እና ታዛዥነት መገለጫችን ይሆናሉና ግሩም ነው፡፡ውብ ነው፡፡

በኢሳይያስ 61-8 ላይ የተከሰተው ታሪክ በኢዮብ ላይ ከተከሰተው ሁኔታ ጋር ቢለያይም፣ሁለቱን  የእግዚአብሔር ሰዎች የሚያመሳስላቸው ነገር  ላዩትና ለገባቸው ነገር የሰጡት ምላሽ ነበር፡፡በሁለቱም ሕይወት የልብ መሰበር ታይቷል፡፡ነቢዩ ኢሳያስ እግዚአብሔርን በሚገርም ግርማና አስፈሪ ክብር ሲያይ  “ከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው በመሆኔ ከንፈሮቻቸውም በረከሱባቸው ሕዝብ መካከል በመቀመጤ አይኖቼ ጌታ ንጉሱን እግዚአብሔርን ስለ አዩ ጠፍቻለሁና ወዮልኝ”(ቁ.5) ብሎ ነበር የተናገረው፤ ልቡ የተሰበረ ሰው ቋንቋ!

በእኛም ሕይወት እንዲህ ነው የሚሆነው፡፡የጌታን ግርማ፣ኃያልነት፣ቅድስናና ክብሩን እስክናይ ድረስ ሰዎችን አብጠልጣይ፣ትዕቢተኛ፣ኩሩ፣አትንኩኝ ባይ፣ተናጋሪ፣ከሳሽና ግትር ነን፡፡እርሱን በክብሩ ስናየው ግን ነገሮች 180 ዲግሪ ይቀየራሉ፡፡ቋንቋችን ይቀየራል፣ይለወጣልም! ታዲያ ከላይ የተገለጸው ዓይነት መለኮታዊ ጉብኝት(holy encounter) ሲያገኘንበማይረሳ ሁኔታ ሕይወታችን ስለሚለወጥ እንደ ኢዮብ ‹‹እራሴን እንቃለሁ›› ወይም እንደ ነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹ጠፍቻለሁና ወዮልኝ›› እንላለን እንጂ ሌላ ቋንቋ አይኖረንም፡፡

ጌታ ሆይ ዓይኖቻችንን ክፈትና ክብርህን አሳየን!