በፊቴ ገበታን አዘጋጀህ
አይናችን ተከፍቶ ስላልታየን ነው
እንጂ እረኛችን በፊታችን ድል ያለ ግብዣን አዘጋጅቶልናል፡፡መዝ 23፡5 ላይ ‹‹በፊቴ ገበታን አዘጋጀልኝ በጠላቶቼ ፊት ለፊት
ራሴን በዘይት ቀባህ ጽዋዬ የተረፈ ነው፡፡››የሚል ዘወትር የሚገርመኝ እና የሚያጓጓኝ ቃል እናገኛለን፡፡ከዚህ ቃል አንድ
የምረዳው ነገር በሚገባ ይህንን ግብዣ እንዳናስተውልና የእምነት እጃችንን ዘርግተን በረከታችንን እንዳናፍስ የጠላት አዚምና
ከበባ እንዳለ ነው፡፡
ዳዊት መንፈሳዊ አይኑ የተከፈተ
ሰው ስለነበር በዚህ ቃል መሰረት አራት ነገሮችን በመንፈሳዊ አይኖቹ እንዳየ ጽፎልናል፡፡እነርሱም፡-
- በፊቱ መንፈሳዊ ገበታ መዘጋጀቱ
- ጠላት እንደ ከበበው
- የመንፈስ ቅዱስ ቅባት እላዩ እንዳለ
- ጽዋው ሞልቶ መትረፍረፉ(ለሌሎች የተረፈ በረከት እላዩ ላይ እንዳለ)
ዳዊት በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን
ሀሳብ በተሳካ ሁኔታ አገልግሎ ያንቀላፋው በፊቱ የተዘጋጀለትን ማእድ በሚገባ ማየቱና ሳያቋርጥ መውሰዱ ነው፡፡ይሄ የእንዳንዳችን
ሀላፊነት ሲሆን ጥሩ መረዳት እና ዲሲፕሊን የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡መዝ 85፡13 እና 16 ላይ ‹‹ሕዝቤ ሰምቶኝ ቢሆን
እስራኤልም በመንገዴ ሄደው ቢሆን ከስንዴ ስብ ባበላቸው ነበር ከአለቱም ማር ባጠገባቸው ነበር››የሚል ከመዝ 23፡5 ጋር
ተመሳሳይ ሀሳብ ያለው ቃል እናገኛለን፡፡እኔ “ከስንዴ ስብ ባበላቸው ነበር ከአለቱም ማር ባጠገባቸው ነበር” የሚለውን
ሀሳብ ባነበብሁት ቁጥር ጉጉቴን ይጨምረዋል፡፡ይህ ቃል የእግዚብሔርን ድምጽ መስማታችንና እና ምሪቱን መከተላችን
ያለውን መንፈሳዊ በረከት ነው የሚያሳየን፡፡በሁለቱም በተጠቀሱ ቃሎች ላይ የእግዚአብሔርን መልካም እረኝነት እና የእኛ ለምሪቱ
መሰጠት የሚያመጣውን በረከት ነው የምናየው፡፡
አዎ እርሱ ቸር ነው ገበታን
አዘጋጅቶልናል፡፡ኢሳ 25፡6 ላይም ‹‹የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ለህዝብ ሁሉ በዚህ ተራራ ላይ ታላቅ የሰባ ግብዣ ያረጀ
የወይን ጠጅ ቅልጥም የሞላባቸው የሰቡ ነገሮች የጥሩና ያረጀ የወይን ግብዣ ያደርጋል››የሚል ክርስቶስ ከመምጣቱ ከብዙ ዘመናት
በፊት የተተነበየ ትንቢት የምናገኝ ሲሆን ይህም የትንቢት ቃል በክርስቶስ መሞት እና ትንሳኤ በከፊል የተፈጸመ እንደሆነ
የመጽሀፍ ቅዱስ አዋቂዎች ይስማማሉ፡፡በዚህ ቃል ላይ ያሉ አገላለጾች እጅግ የሚያጓጉ ሲሆኑ ከእግዚአብሔር መንፈስ ጋር በሚኖረን
የጠለቀ ህብረት ስለምናገኘው ድል ያለ በረከት የሚናገር የተስፋ ቃል ነው፡፡እንዴት ታዲያ ይህን የመሰለ ድንቅ ተስፋ ሳለን ዳር
ዳር እያልን ዘመናችን እንደምንፈጅ አይገባኝም፡፡ኢሳ 55፡2 ላይም ‹‹አድምጡኝ በረከትንም ብሉ ሰውነታችሁም በጮማ ደስ
ይበለው፡፡ጆሮአችሁን አዘንብሉ ወደ እኔ ቅረቡ ስሙ ሰውነታችሁም በሕይወት ትኖራለች ››በማለት ግብዣውንና የግብዣውን ውጤት
ያሳየናል፡፡
ምንም እንኳን በተለያዩ ብዙ
የመጽሀፍ ቅዱስ ክፍሎች ይህንን ድል ያለ ግብዣ እስክንጠግብ እንድንበላ ተደጋግሞ ብንጋበዝም ምላሻችን አሳዛኝ እየሆን ነው ያለው፡፡መዝ 106፡15 እንደሚናገር የለመንነውን (ረብ እና
ዘለቄታ የሌላቸውን ነገሮች) እየሰጠን ለነፍሳችንን ግን ክሳት እየላከ ያለ ይመስለኛል፡፡በዚህ አካሄዳችን ምን ያህል ነፍሱ እንደምታዝን
በጭላንጭልም ቢሆን እገምታለሁ፡፡የማያጠግቡ፣የማይረቡ እና ወንዝ የማያሻግሩ ነገሮች ልባችንን ቀሙን፡፡ጉልበታችንን እንግዶች በሉት፡፡ግብዣው
ላይ በሚገባ መገኘት ደከምን፡፡አቃተን………..
በመፍትሄ ዙሪያ ጥቂት ልበልና ጽሁፌን ልቋጭ፡፡ማቴ 5፡6 ላይ ‹‹ጽድቅን
የሚራቡና የሚጠሙ ብጹአን ናቸው ይጠግባሉና›› የሚለው የጌታችን የተስፋ ቃል የተዘጋጀውን ግብዣ ለማፈስ ቁልፍ ቃል ነው፡፡‹‹ረሀብና
ጥማት›› ለመንፈሳዊ ለውጥና እድገት ትልቅ ሚናን ይጫወታሉ፡፡እነዚህ ሁለቱ ሞተሮች ከሌሉንና ረብ በሌላቸው ነገሮች አእምሮአችንን
እና ውስጣችንን የምንሞላ ከሆነ ለመንፈሳዊ ነገር ያለን ጉገት ስለሚደበዝዝ እና ስለሚጠፋ ከዚህ መለኮታዊ ግብዣ ተቋዳሽ እና ባለ
እድል መሆን ያቅተናል፡፡እውነተኛ መንፈሳዊ ለውጥን የምንፈልግ ከሆነና እረፍትና በረከትን የምንፈልግ ከሆነ በመሰረታዊ ደረጃ ይህ
ረሀብና ጥማት ወደ ህይወታችን እንዲመጣ ትጉህ መሆን ያስፈልገናል፤የትጉ ነፍስ ትጠግባለች ይላልና፡፡ስለዚህ ይህ ረሀብና ጥማት እንዲመጣ
የሚከተሉትን ነገሮች እናድርግ፡-
- የክብርን ጌታ ያለማሰለስ እንሻ
- ረዘም ያሉ የጾም ጊዜዎች ይኑሩን
- ቢሰማንም ባይሰማንም የጸሎት ዲሲፕሊን ይኑረን
- ከቃሉ ጋር ጠንከር ያለ ህብረት ይኑረን(እናጥናው እናሰላስለው)
- አዚምንና ድንዛዜን (የክፉን ስራና ተጽእኖ) እየተቃወምን እንጸልይ
- ከጌታ ጋር ያለንን ህብረት የሚያደበዝዙ ነገሮችን በመጨከን ከሕይወታችን እናባር
ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራዊ እርምጃዎች ሳናሰልስ ረዘም ላሉ ጊዜዎች
ስናደርጋቸው በውጤት ሂደት የሚከተለው ኡደት ውስጥ እራሳችንን ልናገኝ እንደምችል (ቀምሼ አይቼዋለሁና) በድፍረት እናገራለሁ፡-
እግዚአብሔርን በጽኑ መሻት-------›መንፈሳዊ ረሀብና ጥማት--------›የጠለቀ
ጸሎት------›መንፈሳዊ መረዳት-----›የጨመረ መንፈሳዊ ረሀብና ጥማት----------›መንፈሳዊ በረከት-------›የጨመረ መንፈሳዊ
ረሀብና ጥማት-----›የጨመረ መንፈሳዊ መረዳት-----›የጨመረ መንፈሳዊ በረከት ---------›ይቀጥላል(ማብቂያ የለውም)
ለማጠቃለል እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚደንቅ ግብዣ እንዳዘጋጀልን
እጅግ ብዙ ማስረጃዎች አሉን፡፡ይህንን ግብዣ ዝም ብለን መካፈል አንችልም፡፡ቆላ 1፡12 ‹‹በቅዱሳን ርስት በብርሀን እንድንካፈል
ያበቃንን›› እንደሚል ከዚህ በረከት የምንካፈለው በብርሀንና በብዙ መረዳት ነው፡፡ስለዚህ ከላይ ባለ ጥቅስ ላይ ‹‹ጆሮአችሁን አዘንብሉ ወደ እኔ ቅረቡ ስሙ ሰውነታችሁም በሕይወት
ትኖራለች›› እንደሚል ወደ እርሱ ያለማሰለስ እንቅረብ!!
No comments:
Post a Comment