Tuesday, October 8, 2013

የልብ ለውጥ(change of heart)



የልብ ለውጥ

በዚህ ዘመን ሳይንሳዊና ማህበራዊ ተቋማት፣ጠበብቶች፣ሳይንቲስቶች እና አዋቂዎች ለሰው ልጅ የሞራል ማሽቆልቆል እና ጥፋት “የሰው ባህርይ” ስለሆነ የባህርይ ለውጥ ላይ መስራት ነው መፍትሄው ይላሉ፡፡ነገር ግን መጽሀፍ ቅዱስ የሰው ልጅ ችግር ከዛ እንደሚጠልቅ እና “የልብ ለውጥ” እንደሚያስፈልግ በተለያየ መንገድ ያስተምረናል፡፡“ልብ” የሰው ሁለንተናዊ ማንነቱን ይወክላል መንፈሱን ጨምሮ፡፡ሀጢያተኛው ተፈጥሮአችን (the sin nature) በዳግም መወለድ ካልተሸነፈ በስተቀር ልባችን ላይ አሉታዊ ተጽእኖን ስለሚያሳርፍ አካባቢያችን ላሉ ድምጾች እና ግብዣዎች የምንሰጠው ምላሽ እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ መሆን ያቅተዋል፡፡ ምላሾቻችንም ከራስ ወዳድነት እና ከስጋዊ ማንነታችን የመነጨ ስለሚሆኑ አሳዛኝ ውጤቶችን ማየታችን አይቀሬ ነው፡፡ስለዚህ ባህርይን መለወጥ ሽንፍላን የማጠብ አይነት ስራ ይሆናል ማለት ነው፡፡

የባህርይ ለውጥ ያመጡ ሰዎች በቀላሉ ወደ አሮጌው ማንነታቸው የመመለስ እድላቸው የሰፋ ነው የልብ ለውጥ እስካላገኙ ድረስ፡፡ለምሳሌ ተከታታይ ሙያዊ ምክሮችን አግኝቼ ሲጋራ ማጨስ ለተወሰነ ጊዜ አቁሜና ባህርዬ ተስተካክሎ ደስ ብሎኝ ያውቃል፡፡ግን ውጫዊ ለውጥ ስለነበር ባንድ በገጠመኝ ቀውስ ምክንያት ስመለስ እንዳውም ሶሰት እጥፍ ብሶብኝ እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡

ባለማችን የምናያቸው ድርጊቶች እና አሳዛኝ ክስተቶች የተጸኑት በልብ ውስጥ ነው፡፡የምናደርጋቸው ኢንቨስትሜንቶች ልብ ላይ መሆን ይገባቸዋል አለበለዚያ ለውጣችን ታይታዊ ነው የሚሆነው፡፡ማቴ 15፡18-19 ላይ ‹‹ከአፍ የሚወጣ ግን ከልብ ይወጣል ሰውንም የሚያረክሰው ያ ነው፡፡ከልብ ክፉ አሳብ መግደል፣ምንዝርነት፣ዝሙት፣መስረቅ፣በውሸት መመስከር፣ስድብ ይወጣልና››የሚል ሀሳብ እናገኛለን፡፡ልባችን የክፋት ሁሉ ፋብሪካ እንደሆነም በግልጽ እናያለን፡፡ስለዚህ እርሱ ላይ ነው ትኩረት አድርገን ስራን መስራት ያለብን ዘለቄታዊ ለውጥ እንዲኖረን ካስፈለገን፡፡አለበለዚያ ልፋታችን “አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” አይነት ይሆናል፡፡ለውጡም ታይታዊ ብቻ ነው የሚሆነው፡፡

በዳግም መወለድ ስለሚመጣ ስር ነቀል  ለውጥ ህዝ 36፡26-27 ላይ ‹‹አዲስም ልብ እሰጣችኋለሁ አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ የድንጋዩንም ልብ ከስጋችሁ አወጣለሁ የስጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ፡፡መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ በትእዛዜም አስሄዳችኋለሁ ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ ታደርጉትማላችሁ››ይላል፡፡ከድርጊት እና ከተግባር በፊት የልብ ለውጥ እንደሚያስፈልግ ነው በግልጽ የሚያሳየን፡፡በውጤት ሂደት ሳስቀምጠው፡-

የድንጋይ ልብ------›የስጋ ልብ-------›የእግዚአብሄር መንፈስ ውስጣችን ማደር-------›በትእዛዙ መሄድና እውነተኛ ድርጊት(ውጤቱ)

የአለም ጠበብቶች፣ፈላስፋዎችና አዋቂዎች ይህንን መርህ ባለመገንዘብ በድንጋይ ልብ የባህርይ ለውጥ አምጡ ነው እያሉን ያለው ነገር ግን ለሰው ልጅ እጅግ በጣም የሰለጠነ ትምህርት ብንሰጠው፣አለ የተባለ ሙያዊ ምክር ብንሰጠው ልቡ ካልተለወጠ ታጥቦ ጭቃ ነው የሚሆነው፡፡ለምሳሌ እኔ የህክምና ባለሙያ ነኝ፡፡በጤና ዙሪያ አሉ የተባሉ ብዙ መጽሀፍትን አንብቤአለሁ ነገር ግን ተግባሬ ግን ፈጽሞ ከባለሙያ የሚጠበቅ አልነበረም፡፡በሀይል እቅም እጠጣና አጨስ ነበር፡፡ያነበብኳቸው ነገሮች በፍጹም አልረዱምኝ የልብ ለውጥ እንጂ!ወደ ጌታ በዳግመኛ መወለድ ስመለስ ያ ሁሉ ሱስ ባንዴ ነው ቀጥ ያለው፡፡በነጻነት መኖር ምን አይነት እንደሆነ ቀምሼዋለሁና ክርስትና ተረት ተረት ሳይሆን እውነተኛ የልብ ለውጥ የምናገኝበት ህይወት እንደሆነ እመሰክራለሁ፡፡

አንደበታችን ብዙ ክፉ ነገሮችን ያወጣል፡፡ብዙዎችን ያሳዝናል ብሎም የብዙ ሰዎችን ሩጫ ያሰናክላል፡፡የባህርይ ለውጥ በማምጣት በጥቂቱ አንደበታችን ሊሻሻል ይችል ይሆናል ነገር ግን ለውጡ ምንጩን በማድረቅ ሳይሆን ውጫዊ ስለሆነ ዞሮ ዞሮ ባንድ የህይወት ቀውስ ሰአት ሊያገረሽብን እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ምሳ 16፡23 ላይ ‹‹የጠቢብ ልብ አፉን ያስተምራል ››ይላል፡፡ይህ ቃል ግሩም መርህ ያለው ቃል ነው፡፡የተለወጠ ልብ የአፍን ቋንቋ ይለውጣል ነው የሚለው፡፡ሉቃ 12፡34 ላይም ‹‹በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራልና፤ መልካም ሰው ከልቡ መልካም መዝገብ መልካም ነገርን ያወጣል ክፉ ሰውም ከክፉ መዝገብ ክፉ ነገርን ያወጣል›› ይላል ፡፡ስለዚህ ለዘለቄታዊ ለውጥ ትኩረታችን የልብ ለውጥ ላይ እንጂ የባህርይ ለውጥ ላይ መሆን እንደሌለበት በሚገባ ያስገነዝበናል፡፡

ቆላ 2፡11 ላይ ‹‹የስጋንም ሰውነት (sin nature)በመገፈፍ በክርስቶስ መገረዝ በእጅ ባልተደረገ መገረዝ በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ››ይላል፡፡ይህ ቃል ከእግዚአብሄር መንፈስ ዳግመኛ ስንወለድ ስለሚከናወን መንፈሳዊ ሂደት የሚያስረዳ አስደናቂ ክፍል ነው፡፡የእግዚአብሄርን መንፈስ በእውነተኛ ንስሀ ስናስተናግድና ወደ ውስጣችን ከልብ ፈቅደንለት ሲገባ የሚያደርገው ነገር ሃጢያተኛው ተፈጥሮአችንን ወይም ሀጢያት በመስራት የሚደሰተው ማንነታችንን በእንግሊዝኛው “the sin nature” ይገርዘዋል ወይም ይገፈዋል፡፡ስለዚህ ከእንግዲህ በኋላ ተሳስተን እና ሳናስተውል ሀጢያትን ልንሰራ እንችል እንደሁ እንጂ ሀጢያትን ደስ ብሎን ያለ ወቀሳ በደንዳንነት በመስራት አንቀጥልም፡፡ይህ ለውጥ ነው ለእያንዳንዳችን የሚያስፈልገን! ይህ ነው ትክክለኛ የልብ ለውጥ!አስቸጋሪው ተፈጥሮአችን ስለሚገፈፍ እና የድንጋይ ልባችን ወደ ስጋ ልብ ስለሚለወጥና ለውጣችን ከውስጥ ወደ ውጭ ስለሚሆን የአሸናፊነትን ህይወት መኖር የሚያስችል ህይወት ውስጥ እራሳችንን እናገኘዋለን፡፡ስለዚህ ታይታዊ ነገሮችን መፍትሄ የሚመስሉ ነገሮችን አቁመን ወደ ልብን ወደሚለውጥ አምላክ እንመለስ!!


ዋቢ መጻህፍት፡-
The heart of a man from a biblical perspective,by Danny Smith:-
http://epages.wordpress.com/2010/01/25/the-heart-of-man-from-a-biblical-perspective/

No comments:

Post a Comment