Sunday, October 20, 2013

የድብርት መድሀኒት(Medicine to depression)



                                                        የድብርት መድሀኒት

በአለማችን በተለይ በምእራቡ ምድር እንደምናየው ብዙ ሰዎች በተለያዩ የአእምሮ በሽታዎች ሲጠቁ እናያለን፡፡ዋነኛው የአእምሮ ችግርም ድብርት (depression) እንደሆነ በዚህ ዙሪያ ጥናት ያደረጉ ጠበብቶች ይስማማሉ፡፡የድብርት (depression) መንስኤው እንደቦታው እና እንደሰው አይነትና አኗኗር ይለያያል፡፡ሁሉንም የሚያመሳስላቸው ግን የችግሩ ስሜቶች እና ምልክቶች ናቸው፡፡ማለትም ሁሉም ሰዎች ላይ ደስታ ማጣት እና ሀዘን ይኖራል መጠኑ ቢለያይም፡፡ይህ ችግር ጌታ ኢየሱስን የማያውቁ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን እሱን በሚገባ የሚያውቁ ሰዎችን ላይ ሳይቀር ይስተዋላል፡፡አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ጊዜያዊ ጭንቀት እና ድብርት ማናችንም ላይ በተለያየ ምክንያት ሊመጣ ይችላል ነገር ግን እላያችን ላይ ቤቱን ሰርቶ እንዲረጋጋ እና መጫወቻ እንዲያደርገን መፍቀድ የለብንም፡፡


መጽሀፍ ቅዱስ ይህ ችግር ወደ ህይወታችን እንዳይመጣ ጥሩ መከላከላያ መድሀኒት ያለው ሲሆን ይህ ችግር ካገኘንም በኋላ ባስተማማኝ ሁኔታ የምንወጣበት መፍትሄም በውስጡ የያዘ ነው፡፡መጽሀፍ ቅዱስ ትክክለኛ እና የጠለቀ ህብረት ያለው ክርስትያን ዝቆ እና ቀድቶ የማይጨርሰው የደስታ ምንጭ እንዳለው እኔም በህይወቴ ስላየሁ በድፍረት እመሰክራለሁ፡፡


ዳዊት በእንደዚህ ነፍስን ግራ በሚያጋባ አጣብቂኝ እና ሀዘን ውስጥ ከማናችንም በላይ ያለፈ ሲሆን ችግሩንም መፍትሄውንና የመፍትሄውን ውጤት በመዝ 422-4 ላይ በሚደንቅ ሁኔታ ጽፎልናል፡፡ይህ ቃል አስገራሚ ሚስጥር ያለው ቃል ሲሆን በሚገባ በህይወታችን ከተገበርነው ድንቅ ህይወት ውስጥ እንደሚከተን አምናለሁ፡፡ይህንን ክፍል ወደ ጌታ ከመጣሁ በኋላ ከመቶ ጊዜ በላይ አንብቤዋለሁ፡፡አሁንም ደጋግሜ አነበዋለሁ፡፡እንዳውም በጸሎት ጊዜ ወደ እራሴ ህይወት ቀይሬ(by personalizing it) ሁሉ እጸልየዋለሁ፡፡ቃሉ እንዲህ ይነበባል፡-

 ‹‹አንተ አምላኬ ሀይሌም ለምን ትተወኛለህ?ጠላቶቼ ሲያስጨንቁኝ ለምን አዝኜ እመላለሳለሁ?ብርሀንና እውነትህን ላክ እነርሱም ይምሩኝ ወደ ቅድስህናህ ተራራ እና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ፡፡ወደ እግዚአብሔር መሰዊያ ጎልማስነቴንም ደስ ወዳሰኛት ወደ አምላኬ እገባለሁ››

·       የዳዊት ችግር-----የመተው/የመገፋት ስሜት ከዚህም የተነሳ የደረሰበት ጭንቀት እና ሀዘን
·       መፍትሄው--------የእግዚአብሔር ብርሀንና እውነት(ከአፉ የሚወጣው ቃል /ሬማ የሆነው የጊዜው ቃል)
·       የመፍትሄው ውጤት------ደስ መሰኘቱ፤‹‹ጎልማስነቴን ደስ ወዳሰኛት›› የሚለው ሀረግ ይህንን ያመለክታል

ዳዊት በእንደዚህ አይነት ሁኔታ የቆየበት ጊዜ ባይታወቅም ትንሽ እንደቆየ መገመት ይቻላል፡፡ይህንን የሚጠቁመን ቃል ደግሞ ‹‹ለምን አዝኜ እመላለሳለሁ››የሚለው ሀሳብ ነው፡፡እንደዚህ አይነት በደል ሀዘንና ጭንቀት የሚያደርሱበት ደግሞ ጠላቶቹ(አጋንንቶች-የሰው ጠላት የለንምና)እንደሆኑ ይናገራል፡፡ከዚያም መፍትሄውን እራሱ ያቀርባል ‹‹የእግዚአብሔር ብርሀንና እውነት››ናቸው በማለት፡፡በዚህ ዙሪያ የገጠምኩት ግጥም አለ፡-

                የቃሉ ሬማ
ሽንፈት ሲያልብኝ  መነሳት ሲከብደኝ
ሁኔታው ሲያቅራራ አለቀልህ ሲለኝ
ውስጤ እንዲህ ሲስማማ እያየ ጨለማ
ግራ ተጋብቼ ስወናበድ ድንገት
በክስ ሰነድ ብዛት
እንዲህ ባረግህ ኖሮ እንዲህ ይሆን ነበር
የሚል ምክንያታዊ ስሰማ ንግግር
እራሴ ለራሴ ቃላት ሲወራወር
ከጸጸት ስሜት ውስጥ ገፍትሮ የሚያወጣኝ
የቃሉ ሬማነው የሚገላግለኝ !

ዳዊት መፍትሄው የእግዚአብሔር መንፈስ(ሀይል ያለው ከአፉ የሚወጣው ቃል) እንደሆነ በሚገባ ያሳየናል፡፡ማለቴም በጸሎት መንፈስ ሆነን ፊቱን እየፈለግንእየቃተትንቃሉን እያሰላሰልን በሀይል(aggressively)ስንጸልይና በጽናት ስንጠብቀው ከተፍ ብሎ ያስደንቀናል፤ቀንበራችንን ይሰብረዋል፤ሀዘናችንንና ድብርታችንን ያስወግደዋል፡፡እናም ክፋት ወደሌለበት ‹‹ወደ ቅድስና ተራራው ወይም ወደ ማደሪያው(His presence)›› ይወስደናል፡፡በህልውናው ውስጥ ደግሞ ሰላም አለ፤ደስታ አለ፤እረፍት አለ፤መረጋጋት አለ ወዘተ፡፡ይህንን በረከት በህይወቴ ደጋግሜ ስላየሁኝ ህያው ምስክር ነኝ፡፡ክርስትናን ውብ የሚያደርገውም እርሱ ነው፡፡ስለዚህ በራሳችን መታገል አቁመን ሙሉ በሙሉ እራሳችንን ለእርሱ እንስጥ፤በጸጋው ዙፋን ፊት እንውደቅ!በመመለስና በማረፍ እንድናለንና በጸጥታና በመታመን(በፊቱ በመሆን)ሀይል ይሆንልናልና መጥተን በፊቱ ምንም ሳናቅማማ እንረፍ!


ወደ ጌታ ያልመጣችሁ ሰዎች የዲያቢሎስን ሽንገላ ንቃችሁና ንዝነዛውን ወደ ኋላ ጥላችሁ ሸክማችሁን በኢየሱስ እግር ለመጣል ብትወስኑ የሚገርም ህይወት ውስጥ እራሳችሁን እንደምታገኙት በሙሉ እምነት እናገራለሁ፡፡የዛሬ አስራ አምስት አመት ገደማ እኔም የዲያቢሎስን ሽንገላ አሽቀንጥሬ ነው ከብዙ ሀዘንና መከራ ወጥቼ በነጻነት መኖር ምን እንደሆነ የቀመስኩትና መጥታችሁ የእግዚአብሔርን እረፍትና ቸርነት ምን እንደሚመስል ቅመሱ!!


No comments:

Post a Comment