Monday, August 17, 2015

አዲስ ራእይ ያስፈልገናል (Fresh vision)



ነቢዩ ኢሳይያስ በሱ ዘመን ከነበሩ የእግዚአብሔርን ሕግ በማወቅ በጽድቅና በቅድስና ከሄዱ ሰዎች መካከል አንዱ እንደ ነበር በጻፋቸው እጅግ በርከት ባሉት ትንቢታዊ መልእክቶቹ ላይ ይስተዋላል ፡፡

 
ነቢዩ ኢሳይያስ እግዚአብሔርን የሚፈራና የሚያውቅ ሰው በመሆኑ ከሱ ፈቃድ ባፈነገጠ ኑሮ የሚሄዱ እስራኤላውያንን ወደ መስመር እንዲገቡ ከበድ ያለ ተግሣጽ ያለው መልእክት ሲያስተላልፍ እንደ ነበረ የትንቢት ኢሳይያስ መጽሐፍ ከምዕራፍ አንድ እስከ አምስተኛ ምዕራፍ ያሉት ክፍሎችን ስናነብ እንገነዘባለን፡፡

 
ስካርን የሚከተሉትን፣አምላካቸውን የማያውቁትን፣ትዕቢተኞችን፣በደልን በምናምንቴ ገመድና ኃጢአትን በሠረገላ ማሠሪያ ወደ ራሳቸው የሚስቡትን፣ክፉውን መልካም እና መልካሙን ክፉ የሚሉትን፣በዓይናቸው ጥበበኞችና በነፍሳቸው አስተዋዮች የሆኑ የመሰላቸውን(ኢሳይያስ 5) ወዘተ ወዮላችሁ እያለ ሲያስጠነቅቅ ከርሞ፣በስድስተኛው ምዕራፍ ላይ ከዚህ በፊት አይቶት የማያውቀውን ከፍ ያለ አስደንጋጭ ራእይ አየ፡፡ጌታ እግዚአብሔር ራሱን በሚገርምና በሚያስፈራ መልኩ ገለጠለት፡፡ያ አስደናቂና አስደንጋጭ ራእይ፣ኢሳይያስን ወደ ራሱና ወደ ውስጥ እንዲመለከት አድርጐታል፡፡ክስተቱ እጅግ አስደንግጦት ነበርና፣እንዲህ ነበር ያለው፡-

 
“ከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው በመሆኔ ከንፈሮቻቸውም በረከሱባቸው ሕዝብ መካከል በመቀመጤ ዓይኖቼ የሠራዊትን ጌታ ንጉሡን እግዚአብሔርን ስለ አዩ ጠፍቻለሁ ወዮልኝ” (ቁ.5)

 
ባጭሩ ወዮላችሁ ወደ ወዮልኝ ተቀየረ፡፡የሚገርም ነው፡፡በነገራችን ላይ “ጠፍቻለሁ” የሚለውን ቃል በእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱሶች ላይ ስመለከት “I am ruined” ወይም “I am undone” የሚሉ ትርጉሞችን እንደያዘ አይቻለሁ፡፡አር ሲ ስፕሮውል የሚባሉ የእግዚአብሔር ሰው ለዚህ ቃል ትክክለኛውና በጣም ተቀራራቢ የሆነው ትርጉም “I am undone” የሚለው እንደ ሆነ ባስተማሩት ትምህርታቸው ላይ ሰምቻለሁ፡፡ “ጠፍቻለሁ” የሚለው ቃል “አበቃልኝ አልተርፍም” እንደ ማለት ነውና፡፡
አዎ፣ነቢዩ ኢሳይያስ የነበረበት ሁኔታ የመጨረሻ የሚያርበተብት፣ግራ የሚያጋባና የሚያስጨንቅ ነበረ፡፡ከዚህም የተነሣ ይህ ነቢይ በብዙ ጥልቅ ንስሐ በጌታው ፊት ያሳለፈ ይመስለኛል፡፡እውነተኛ ጥልቅ ንስሐ ከባድ ነውና፣በብዙ ሕመም እንዳሳለፈ የሚጠቁመን ክፍል ቁ.6 ነው፡፡እንዲህ ይላል፡-

 
“ከሱራፌልም አንዱ እየበረረ ወደ እኔ መጣ፤በእጁም ከመሠዊያው በጉጠት የወሰደው ፍም ነበረ፡፡አፌንም ዳሰሰበት”(ቁ.6)

 
ከንፈራችን በጣም ስስና በቀላሉ የሚጐዳ የአካል ክፍላችን እንደ ሆነ ይታወቃል፡፡እዚሁ ክፍል ላይ ነው በጉጠት የነበረው ፍም ያረፈው፡፡እጅግ በጣም እንደሚያም መገመቱ ከባድ አይሆንም፡፡አዎ፣ይህ ሕመም ትክክለኛና እውነተኛ ንስሐ ዋዛ እንዳልሆነ ይጠቁማል፡፡በዚያ የጋለ ጉጠት ላይ በነበረው ፍም ከንፈሩ ከተዳሰሰ በኋላ ነበረ በደሉ የተሻረለት፤ኃጢአቱም የተሰረየለት(ቁ.7).ከዚያም “ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል?” (ቁ.8) ሲባል “እነሆኝ እኔን ላከኝ” ( ቁ.8) የሚል ትሕትና የተላበሰ ቋንቋ  ከአንደበቱ ወጣ፡፡


 
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያየናቸው ነቢያትና ጸሐፍት ክብሩን አይተው ደንግጠውና ተለውጠው ቀርተዋል፡፡እውነት ለመናገር በበኩሌ “እባክህ ተገለጥና ትንሽ አስደንግጠን” የሚል ጸሎትም እየዳዳኝ ነው፡፡ሐዋርያው ዮሐንስ የጌታን ክብር ሲያይ “ባየሁትም ጊዜ እንደ ሞተ ሰው ሆኜ ከእግሩ በታች ወደቅሁ” (ዮሐንስ 1፡17)ብሎ ተናግሯል፡፡ነቢዩ ዳንኤል እግዚአብሔርን በክብሩ ሲያየው“ኃይልም አልቀረልኝም፤ደም ግባቴም ወደ ማሸብሸብ ተለወጠብኝ፤ኃይልም አጣሁ፡፡የቃሉንም ድምፅ ሰማሁ፤የቃሉንም ድምፅ በሰማሁ ጊዜ ደንግጬ በምድር ላይ በግምባሬ ተደፋሁ” (ዳንኤል 10፡8-9) ብሏል፡፡ነቢዩ ሕዝቅኤል ያንን አስገራሚ የእግዚአብሔር ክብር ምሳሌ ሲመለከት፣ “ባየሁም ጊዜ በግምባሬ ተደፋሁ”(ሕዝቅኤል 1፡28) ብሎ ነበር ክስተቱን የገለጸው፡፡ነቢዩ ዕንባቆ የእግዚአብሔር ክብር መምጣቱን በመንፈሱ አውቆ የተናገረው ነገር እጅግ ያስደንቀኛል፡፡እንዲህ ነበር ያለው፡-

 
“እኔ ሰምቻለሁ፣ልቤም ደነገጠብኝ፤ከድምፁ የተነሣ ከንፈሮቼ ተንቀጠቀጡ፤መንቀጥቀጥ ወደ አጥንቶቼ ውስጥ ገባ፤በስፍራዬ ሆኜ ተናወጥሁ” (ዕንባቆ 3፡16)

 
የእግዚአብሔር ሰማያዊ ጉብኝት አስደናቂም አስፈሪም ነው፡፡እኔ ሳስበው፣እግዚአብሔርን የተዳፈርንበትና ኃጢአትን አቅለን ያየንበት ምክንያት፣ጌታን በትክክል ስላልተረዳነውና በዚህ መልኩ(ትንሽም ቢሆን) በመንፈስ ሰላላየነው ይመስለኛል፡፡ታዲያ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል ? ብናየው ሁኔታዎች ይቀየራሉ የሚል እሳቤ አለኝ፡፡

 
የሚያገለግሉንና የሚያስተምሩን ሰዎች እግዚአብሔርን በእንደዚህ ዓይነቱ ሁኔታ (በትንሹም ቢሆን) ያላዩ ሰዎች ስለሆኑ፣ትክክለኛው የጌታችን ስዕል በብዙዎቻችን ዘንድ ጠፍቶብናል፡፡ስለዚህም እግዚአብሔርን መፍራት ከየት ይመጣል? ለዚህም ነው ብዙ ያገጠጡ ችግሮች በመካከላችን የሚታዩት፡፡

 
በግሌ በራሴ ሕይወት ደጋግሜ ማፈሬን አልደብቃችሁም፡፡እግዚአብሔርን እንደሚገባኝ አለመፍራቴን መንፈስ ቅዱስና ሕሊዬ ይመሰክሩልኛል፡፡የቅርብ ጊዜ ጸሎቴም እሱን በሚገባ መፍራት ወደ ሕይወቴ እንዲመጣ ነው፡፡ዋናውን ጥሎ ወደ የት ?

 
የእግዚአብሔርን ክብር ያዩ ሰዎች በሕይወታቸው ትልቅ ለውጥ እንደነበራቸው መጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ቦታዎች ተርኮልናል፡፡ሐዋርያው ጳውሎስ በሚያስደነግጥና በሚያስገርም ጉብኝት ነበር ወደ ጌታው የተመለሰው(ሐ.ሥራ 9፡1-9)፡፡ለዚህም ነው “በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ መዳናችሁን ፈጽሙ”(ፊሊጵስዩስ 2፡12) ብሎ የመከረን፡፡

 
የእግዚአብሔር ቃል “ልጆቼ ኑ ስሙኝ እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችኋለሁ” (መዝሙር 34፡11) ይላል፡፡አዎ፣እግዚአብሔርን በመፍራትና በመንቀጥቀጥ ለማክበርና ለመገዛት፣ቀርበነው ከራሱ መማር ያስፈልገናል፡፡በጽኑ ጸሎት ፊቱን መፈለግ ይኖርብናል፡፡ከቃሉ ጋርም ጠንከር ያለ ቁርኝት ያስፈልገናል፡፡መንገዱ ይኸው ነው--ቀርቦ ማወቅ(relational knowledge)! ስለዚህ ጌታ አዲስ ራእይ፣አዲስ ዕይታ፣አዲስ ማስተዋልና አዲስ ምልከታ እንዲሰጠን ፊቱን እንፈልግ!
 

No comments:

Post a Comment