Friday, August 28, 2015

ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ (ሮሜ 12፡16)

ይህን ቃል ጊዜ ሰጥታችሁ አስባችሁትና አሰላስላችሁት ታውቃላችሁ ? በዚህ ሳምንት ለእኔ የሚገርም ቃል ሆኖ ነው የከረመው፡፡እስቲ አስቡት፡፡አንዳንዴ ግሩም ስብከት ወይም ትምህርት ታስተምሩና፣አድናቆት የተቸረው ሥራ ታከናውኑና፣ስኬት የተጐናጸፈ ክንውን ትፈጽሙና፣ራሳችሁ ለራሳችሁ ፣ “እኔ ኮ ማን ይችለኛል፣ጎበዝ እኮ ነኝ ፤ማን ይበልጠኛል ?” ብላችሁ አታውቁም ?

በግሌ ልቤ የታበየበትና እራሴን ያሞካሸሁበት ብዙ ጊዜያት እንደ ነበሩ አልደብቃችሁም፡፡ብዙዎቻችን ጌታ ማስተዋል ካልሰጠን ለጌታ ልንሰጥ የሚገባውን ምሥጋናና ክብር ሊያሳንስ የሚችል አላዋቂነት አይጠፋንም ብዬ አስባለሁ፡፡ከዚህ ስህተት ጌታ ይጠብቀን! የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ብሎ አስረግጦ ይናገራልና፡-“ያልተቀበልኸው ምን አለህ ? የተቀበልህ ከሆነ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለ ምንድን ነው ?” (1 ቆሮንቶስ 4፡7)

ወገኖቼ እስቲ ደጋግማችሁ አስቡት፡፡እስቲ ምንድን ነው ያልተቀበልነው? የራሳችን የምንለው ነገር የቱ ነው ? መጠቀሚያ ዕቃዎች ነንና! በቃ ይኸው ነን፡፡ስለዚህ እጅግ ልናስተውል ይገባል፡፡የእግዚአብሔር ቃል “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” (ያዕቆብ 4፡6) ይላልና ሁልጊዜ አመለካከታችን በትሕትና መቃኘት ይኖርበታል ብዬ አምናለሁ፡፡ምክንያቱም እግዚአብሔር በምሕረቱና በረድኤቱ በሚታመኑ ነውና ደስ የሚሰኘው፤የሚደገፉበትን ይረዳል፣ይደግፋልም፡፡

በራሳችን፣በዕውቀታችንና በማናቸውም ምድራዊ ነገሮች መደገፍና ትምክህት አይጠቅመንም፣ይጐዳናል እንጂ፡፡የሚመካ ሰው ለሚታመኑበት አስተማማኝ በሆነው የፍቅር አምላክ ነው ሊመካ የሚገባው፡፡ቃሉ እንዲህ ብሎናልና፡-

“ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፣ኃያልም በኃይሉ አይመካ፣ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ነገር ግን የሚመካው። ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፣ይላል እግዚአብሔር” (ኤርምያስ 9፡23-24)

ደግሜ እላለሁ፣ልባሞች የሆንን አይምሰለን፡፡ያለ እሱ ፈቃድ፣ድጋፍና ረድኤት፣ከፊታችን ተዘጋጅቶ የቀረበውን እንጀራ ቆርሶ ወደ አፍ ማድረግ እንኳ ከባድ ነው፡፡ስለዚህ ሁሌም በትሕትናና በምስጋና መንፈስ በፊቱ እንሁን፡፡የተደረገልን ነገሮች በመንፈስ እያየን እናክብረው፣ከፍ እናድርገው፡፡ተባረክ እንበለው፤በዚህ ደስ ይሰኛልና!

No comments:

Post a Comment