Wednesday, August 19, 2015

የእግዚአብሔርን እንጂ የሰው አናስብ


በማቴዎስ ምዕራፍ 16፣ጌታችን ኢየሱስ “ብዙ መከራ ይቀበል…..እንዲገባው” (ቁ.11) ለደቀ መዛሙርቱ በነገራቸው ጊዜ፣ጴጥሮስ ወደ ነበረበት ጠጋ ብሎ “አይሁንብህ ጌታ ሆይ ይህ አይደርስብህም”(ቁ.22) ብሎት ነበር፡፡ጌታ ኢየሱስም ወዲያው “ወደ ኋላዬ ሂድ አንተ ሰይጣን የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል” (ቁ.23)ብሎ ገሥጾታል፡፡

አዎ፣ጴጥሮስ በዛ ጊዜ የእግዚአብሔርን አልነበረም ያሰበውና ያደረገው፡፡ቢሆንም ከኢየሱስ ትንሣኤ በኋላና ታላቁን ተልዕኮ ተቀብለው ከተሰማሩ በኋላ፣ብዙ መከራን ተቀብሎ ያለፈ ትልቅ ሐዋርያና የእምነት ጀግና እንደ ነበር ታሪክና መጽሐፍ ቅዱስ ዘክረውታል፡፡ይህ ሐዋርያ የክርስቶስን መከራ በመካፈል ዙሪያ ጠንካራ መልእክቶችን መጻፉም ይታወቃል፡፡ከነዚህ መልእክቶቹ በሁለት ክፍሎች ላይ እንዲህ ብሏል፡-

“ወዳጆች ሆይ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ ድንቅ ነገር እንደ መጣባችሁ አትደነቁ፤ነገር ግን ክብሩ ሲገለጽ ደግሞ ሐሤት እያደረጋችሁ ደስ እንዲላችሁ በክርስቶስ መከራ በምትካፈሉበት ልክ ደስ ይበላችሁ”(1የጴጥሮስ 4፡12-13)

“በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ ፍጸማን ያደርጋችኋል፣ያጸናችኋል፣ያበረታችኋል”(1ጴጥሮስ 5፡10)

ልብ በሉ፤እነዚህን ጠንካራ መልእክቶች “አይሁንብህና አይድረስብህ” ያለው ጴጥሮስ ነው የጻፋቸው፡፡አይገርምም! በበኩሌ ሁሌ እነዚህን መልእክቶች ባነበብኩና ባሰላሰልኩኝ ቁጥር ይህንን ሰው ያገኘው ለውጥ ይደንቀኛል፡፡እንዲህ ሊል የቻለበት ምን ዓይነት ጥልቅ መንፈሳዊ ለውጥና መረዳት እንዳገኘው ገና በሚገባ ጥርት ብሎ አልገባኝም፡፡ነገር ግን ከጌታው ጋር የነበረው እጅግ የተጣበቀ ሕይወት ይኼንን ድፍረትና ትምክህት እንዳመጣለት አልጠራጠርም፡፡

ጌታ ኢየሱስ ጴጥሮስን ከገሠጸው በኋላ አስተሳሰባቸውንና አመለካከታቸውን ለማስተካከል ይመስላል፣ወዲያውኑ የክርስትያኖች ዋና ማገር የሆነውነንና ዘመን የማይሽረውን መልእክት የሰጣቸው፡፡መልእክቱ እንዲህ የሚል ነው፡-

“እኔን መከተል የሚወደ ቢኖር ራሱን ይካድ፤መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ፡፡ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል”(ማቴዎስ 16፡22)

በዚህ ዘመን በዚህ ቃል ዙሪያ ብዙ ስብከትና ትምህርት እምብዛም አይሰማም፡፡ዛሬ ላይ የምንገኝ አማኞች(ብዙዎቻችን) በግብራችን እንደ ጴጥሮስ(ከመለወጡ በፊት) ዓይነት አመለካከትና አስተሳሰብ ያለን ይመስለኛል-“አይሁንብህና አይድረስብህ” የምንል፤የመስቀሉን መንገድ የምንሸሽ!
በፍጹም ዋጋ የሚያስከፍሉ፣ሕመም ያለባቸውንና መከራን የሚያመጡ ነገር ግን ክርስቶስ የሚከብርባቸውን ነገሮች አቋራጭ እየፈለግን እየሸሸንና እያመለጥን ያለን ይመስለኛል፡፡

ብዙዎቻችን በራስ ወዳድነት፣በስስትና በራስ ተኮር የኑሮ ዘይቤ ተጠላልፈን እራሳችኑኑ ስናስብና ስንከባከብ ነው ውለን የምናድረው(ምናልባት ተሳስቼ ከሆነ ልታረም እችላለሁ)፡፡የሕይወት ዘይቤአችን ይህንን ያለ ምንም ችግር የሚያሳብቅም ይመስለኛል፡፡እውነተኛና የምር የሆነ የክርስትና ሕይወትና ሩጫ ግን ይህንን አካሄድ በፍጹም አያስተምርም፣አያደፋፍርም፡፡ሕይወቱ በሚገባ ይተግበር ከተባለ “ለሌሎች የመኖርና ለሌሎች የመቆረስ ሕይወት”፣እንዲሁም "የመስቀል መንገድ" መሆኑ ሊታወቅና ሊሰመርበት ይገባዋል፡፡

በነገራችን ላይ ይህ ጽሑፍ ሰዎችን ለመውቀስ ታስቦ ሳይሆን፣በዚህ ዙሪያ ያለንን አመለካከትና አስተሳሰብ እንድናርቅ ሊረዳን ይችላል ብሎ ከማሰብ የመነጨ እንደ ሆነ እንዲታሰብልኝ እፈልጋለሁ፡፡

ሕይወት በምርጫዎችና በፈተናዎች የተሞላች ናትና በመንገዳችን ላይ ኢየሱስ የሚከብርባቸው ለጊዜው ግን የሚያሳምሙን ብዙ ጉዳዮች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ለምሳሌ በእነዚህ የፈጠራ ምሳሌዎቼ ላይ ብትገኙ ምን ታደርጋላችሁ?

• ሰው ታሞ በመኪናችሁ እንድታደርሱት ቢጠይቃችሁና የተጠራችሁበትና የማትቀሩበት ሠርግ ቢኖር
• በእጃችሁ ያላችሁ 200 ብር ብቻ ነው፡፡ነገር ግን ያንን 200 ብር እጅግ በጣም ለአንገብጋቢ የሕይወት ጉዳይ የሚፈልግ ወንድም አጠገባችሁ ቢኖር
• እጅግ ግሩም የሆነ ሰው ሁሉ ተጠራርቶ እየሄደበት ያለበት ኮንፈረስ ላይ ለመሄድ እያሰባችሁ፣የታመመና የእናንተ ጉብኝት የሚያስፈልገው ወንድም ቢኖር

እናንተ ከነዚህ የበለጡ ብዙ ምሳሌዎችን ልትጨምሩ ትችላላችሁ፡፡በእያንዳንዱ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች የምንወስዳቸው እንደ ጌታ ፈቃድ ያሉ ርምጃዎች ጌታችን እንዲከብርና እንዲታይ ያደርገዋል፡፡ጌታ ኢየሱስም “መስቀል መሸከም” ብሎ የሚናገረው ስለ እንደዚህ ዓይነት ተመሳሳይ ርምጃዎች ነው፡፡ቢያምም የራስን ምርጫዎች ለሱ ክብር መተው! ቢያምም ረጅሙንና ፈታኙን ጎዳና ከሱ ጋር ተስማምቶ መጠብጠብ!

ከላይ ከጠቀስኳቸው ፈተናዎች ጠንከር ያሉ ብዙ ፈታኝ መከራዎችና መንገላታቶች ሊመጡ ይችላሉ፡፡እነዚህ ክስተቶች በየትኛውም መንገድ ወደ እኛ ይምጡ ውስጣችንን የሚፈትሹ ለመሆናቸው ምንም ጥርጥር ሊገባን አይገባም፤ጌታ ላይ መደገፋችንንና አለመደገፋችንን ይመሰክራሉና፡፡

በእንደዚህ ዓይነት ጊዜያት ከጫናው የተነሣ ስፍራችንን ሳንለቅ፣በጌታ ፊት በመሆን፣ጸጋን በመለመንና ለሥጋችን የሚመቸውን አካሄድ ሳንመርጥ፣እንደ ጌታ ፈቃድ በመሄድ እሱን በሕይወታችን ማሳየት ትልቅ አስተዋይነት ነው፡፡ከዛ ፈተና ስንወጣም የሚኖረን ምስክርነት ጠንካራ ይሆናል፡፡

ሰይጣን ይህ እንዳይሆንና እንደ ጴጥሮስ ዓይነት ለስጋ የሚመቹ አቋራጮችን ያሳየናል፣ያቀርባልም፡፡ስለዚህ በመንፈስ እያስተዋልን፣ “ወደ ኋላዬ ሂድ አንተ ሰይጣን የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብም”(ማቴዎስ 16፡23) ልንለው ይገባል፡፡

ጌታ ይርዳን!
Bekele Belachew
Write a comment...

No comments:

Post a Comment