Saturday, March 29, 2014

የምስጋና መጎናጸፊያ




March 29, 2014
የምስጋና መጎናጸፊያ

እለቱ ሰኞ ነበር፡፡ከስራ አድሬ ቤት የደረስሁት ማለዳ ጧት ነበርና ለአምስት ሰዓታት ገደማ ተኝቼ ነበር ካልጋዬ የተነሳሁት፡፡እንደተነሳሁም ቤት ያፈራውን ቀማምሼ ኮምፒዩተሬ ፊት ካለው ወንበር ላይ ተቀመጥሁ፡፡በቀደሙት ሰሞናት ያለምኳቸውና ያሰብኳቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ተከናውነው አላለቁምና ድንገት ትዝ ብለውኝ በሀይል አስተከዙኝ፡፡ምኑም አልጥመኝ ብሎኝ እጅግ ተጫጭኖኛል፡፡መግለጽ የማልችለው ስሜት ከብቦኝና ማሰብ አቅቶኝ ደንዝዤ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ዳዊት ይህንን የኔን ስሜት በመዝ 43፡2 ላይ እንዲህ ብሎ ገልጾታል፡-

‹‹አንተ አምላኬ ሀይሌም ለምን ትተወኛለህ ? ጠላቶቼ ሲያስጨንቁኝ ለምን አዝኜ እመላለሳለሁ?››

በእንደዚህ አይነት ስሜት ውስጥ ስከበብ የሚታየኝ ነገር መጸለይ ነው፡፡ነገር ግን መጸለይ አቅቶኛል፤አስጠልቶኛልም፡፡በቅጽበት አንድ የእግዚአብሔር ሰው የተናገሩት ነገር ትዝ አለኝ፡፡እንዲህ ነበር ያሉት ፡-

‹‹የመጸለይ ፍላጎት ስታጣና መጸለይ ሲያቅትህ ራስህን ካገኘኸው መጸለይ ያለብህ ያኔ ነው››

አዎ ትክክል ነበር የተናገሩት፡፡ከሰውየው ሀሳብ ጋር በመስማማት እንደምንም ሸርተት ብዬ ለጸሎት በጉልበቴ ተንበረከክሁ፡፡የምተነፍሰው ነገር ግን አንደበቴ ላይ አልነበረም፡፡ለረጅም ጊዜ ጸጥታ ሆነ፡፡ከብዙ ጸጥታ በኋላ አንድ አምልኮ መዝሙር ከፍቼ አብሬ በጸሎት መንፈስ መዘመርና መፍሰስ ጀመርሁ፡፡በመሀልም በልሳን ረዘም ላሉ ደቂቃዎች መጸለዬን ቀጠልሁ፡፡እላዬ ላይ የነበረው የከበደኝ ጉም እስኪገፈፍ ላልነሳ ጨከንኩ፡፡ታምኜ በእምነት እንጂ በማየት ላለመላላስ(2 ቆሮ 5፡6) በመንፈስ አይኖቼን ወደ ጌታዬ አነሳሁ፡፡ብዙ ሰዓታትን በመቃተት አሳልፌ ለደቂቃ ከተንበረከኩበት ተነስቼ መብራት ላበራ ስል የሆነ ለየት ያለ ቀድሞ ያልነበረ ጉልበትና መታደስ ወደ ውስጤ እንደመጣ ታወቀኝና ደነቀኝ፡፡

ከዚያም ሁኔታው ገርሞኝ የበለጠ እየተነቃቃሁ ለረጅም ጊዜ ጸለይሁ፡፡ግሩምና ድንቅ የሆነ የተለቀቀ አምልኮና ውዳሴም ውስጥ እራሴን አገኘሁት፡፡ከዚያ የጸሎት ሰአት ጅምሮ ይህንን መልእክት እስከጻፍኩበት ጊዜ ድረስ የማያቋርጥ የዝማሬ፣የደስታና የሰላምን መንፈስን ተጎናጽፌአለሁ፡፡ይህንን የእኔን ሁኔታ የሚገልጽ ቃል ኢሳ 61፡1-3 ላይ እናገኛለን፡፡እንዲህ ዘርዝሬ ባቀርበው ይፈቀድልኝ፡፡

‹‹የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው እግዚአብሔር ቀብቶኛልና(ስለ ኢየሱስ አገልግሎት ነው ነቢዩ የጻፈልን)፡፡ለመሆኑ ለምንድነው የተቀባው???መልሱ እንደሚከተለው ነው፡-

  • የተሰበረውን ይጠግን ዘንድ

  • ለተማረኩት ነጻነትን ለታሰሩትም መፈታትን  ይናገር ዘንድ

  • የሚያለቅሱትን ሁሉ ያጽናና ዘንድ

  • በአመድ ፋንታ አክሊልን፣በልቅሶም ፋንታ የደስታን ዘይት፤በሃዘንም መንፈስ ፋንታ የምስጋናን መጎናጸፊያ ይሰጥ ዘንድ››

የከበበኝ ጉም ተበትኖ እና ‹‹በሃዘን መንፈስ ፋንታ የምስጋና መጎናጸፊያ››ተደርቦልኝ በሚያማምሩ ድንቅ ዝማሬዎች ታጅቤ አመሻሹ ላይ ወደ ስራዬ አመራሁ፡፡ለመሆኑ ይህንን ህክምና የት አገኘው ኖሯል?እርሱን የሚወዳደር ሀኪምስ የት ይገኛል?

ዋናው መልእክቴም እንዲህ ነው፡-
ኢሳያስ 12፡3 ላይ ‹‹ውሀውንም ከመድሀኒት ምንጮች በደስታ ትቀዳላችሁ›› እንደሚል በእንደዚህ አይነት ማዕበል ውስጥ ስትገቡና ስትዳክሩ፣በነፍሳችሁ መታገሉን አቁማችሁ ወደ ጸጋው ዙፋን ኑ(ዕብ 4፡16)፡፡እናም ከዚህ ተዝቆ ከማያልቅ ፋርማሲ መድሀኒታችሁን እፈሱ!!! በመንፈሴ እንጂ በሀይልና በብርታት አይደለም(ዘካ 4፡6) ይላልና!!!

Saturday, March 22, 2014

የምናልፍባቸው ጎዳናዎች



የምናልፍባቸው ጎዳናዎች

እግዚአብሔር እኛን ለመስራት በተለያዩ የህይወት ጎዳናዎች ወደድንም ጠላንም ያሳልፈናል፡፡የለቅሶ ዘመን አለ፤የመከራ ዘመን አለ፤የጭንቅ ዘመን አለ፤የእጦት ዘመን አለ ደግሞም የእረፍት እና የበረከት ዘመን አለ፡፡ለዚህ ነው መዝ 84:6 ላይ ‹‹በለቅሶ ሸለቆ በወሰነው ስፍራ የህግ መምህር በረከትን ይሰጣልና ከሀይል ወደ ሀይል ይሔዳሉ›› በማለት የለቅሶ ጊዜ እንዳለ የሚያበስረን፡፡


እግዚአብሔር ሊሰራን፣ሊያበጃጀን(መዝ 119፡73) እና ከእኛ ላይ አላስፈላጊውን እንደ እልህ፣በገዛ ፈቃድ መሄድ እና ትዕቢትን ሊያራግፍ እና ሊያለዝበን በብዙ ነገሮች ውስጥ ያሳልፈናል፡፡ይህንን የሚገልጽ ግሩም ቃል መዝ 66፡10-12 ላይ እናገኛለን፡፡እንዲህ ይነበባል፡-


‹‹አቤቱ ፈትነኸናልና፤ብርን እንደሚያነጥሩት አንጥረኸናልና፡፡ወደ ወጥመድ አገባኸን፤በራሳችን ላይ ሰውን አስረገጥኸን፤በእሳትና በውሀ መካከል አለፍን፤ወደ እረፍትም አወጣኸን››


አዎ የፈተና፣የንቀት፣የስድብ እና የመከራ ዘመን አለ፡፡የጌታ ጊዜ ሲደርስ ደግሞ ግሩም የሆነ የእረፍት ጊዜ አለ፡፡የፈተናው እና የመከራው ዘመን ያማል፣አንገትን ያስደፋል፣ያስለቅሳል፣ግራ ያጋባል ወዘተ፡፡በእንደዚህ አይነቱ ጊዜ ከእርሱ ጋር ተጣብቀንና አጥብቀን የጌታን ፊት የምንፈልግ ከሆነ እግዚአብሔር እንደሚደግፍ፣እንደሚያጽናና፣እንደሚረዳ በተግባር ደረጃ የምናውቅበት ጥሩ አጋጣሚ ይሆንልናል፡፡


በሆሴዕ ምእራፍ ሁለት ላይ እግዚአብሔር እስራኤልን ከነበረችበት የሞራል ውድቀት ለመመለስ ወደ መከራ ውስጥ እንደሚከታት እናያለን፡፡ በሆሴ 2፡16 ላይ እንዲህ ይላል ፡-


‹‹ አባብላታለሁ ወደ ምደረ በዳም አመጣታለሁ፤ለልብዋም እናገራለሁ››


እዚህ ቃል ላይ እንደምናየው ‹‹ለልብዋም እናገራለሁ››የሚለው ቃል ያስደንቀኛል፡፡ቃሉ በመከራ ውስጥ ከእግዚአብሔር ጋር በመሆንና ጊዜን በማሳለፍ ስለሚመጣ ድንቅ ህብረትና በረከት ነው የሚናገረው፡፡በእኛም ህይወት እንዲሁ ነው የሚሆነው፡፡የእግዚአብሔር ድምጽ ሲመጣ በብዙ ክብር ነው የሚመጣው(መዝ 29፡1-11 ያንቡ)፡፡ድምጹ ሲመጣና ለልባችን ሲናገረን ደግሞ እምነታችን ያድጋል፣ይጠነክራል፤ሰላማችን ይበዛል፤ሕይወታችን ይታደሳል፤መንፈሳዊ ህይወታችን ይለወጣል ያድግማል፡፡


በዚሁ በሆሴዕ 2፡17-19 ላይ እግዚአብሔር ወደ ምድረ በዳ አባብሎ እስራኤልን ከከተታት በኋላ በእስራኤል ላይ ስለሚመጣው አስገራሚና አስደናቂ መንፈሳዊ ለውጥ(transformation) እንዲህ ብሎ ይናገራል፡-
‹‹ከዚያም የወይን ቦታዋን የተስፋ በርም እንዲሆንላት የአኮርን ሸለቆ እሰጣታለሁ፤በዚያም ከግብጽ ምድር እንደ ወጣችበት ቀን እንደ ህጻንነትዋ ወራት ትዘምራለች፡፡በዚያ ቀን ባሌ ብለሽ ትጠሪኛለሽ እንጂ ዳግመኛ በኣሌ ብለሽ አትጠሪኝም ይላል እግዚአብሔር፤የበአሊምን ስም ከአፍሽ አስወግደዋለሁና በስማቸውም እንግዲህ አይታሰቡምና››


አዎ ከቃሉ እንደምንረዳው ያ ምድረ በዳ እና የመከራ ቦታ ለእስራኤል ትልቅ መንፈሳዊ ለውጥንና በረከትን እንዳመጣላት እንገነዘባለን፡፡ህብረቷ፣አምልኮዋ፣ይዞታዋና ከጌታዋ ጋር ያላት ህብረት እና ግንኑነት እንደታደሰና እንደጠለቀም እናያለን፡፡


ከድሎት ዘመን ይልቅ በዚህኛው ዘመን ውስጥ ብዙ ጸሎትና ፊቱን መፈለግ ይስተዋላል፡፡ጊዜው መርዘሙ ቢያታክተንም ለመንፈሳዊ እድገት ግን ትልቅ አጋጣሚ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ለዚህም ነው በያዕ 1፡1-4 ላይ እንዲህ ብሎ ሀዋርያው ያዕቆብ ገራሚ ምክርን የሚመክረን፡-


‹‹ወንድሞቼ ሆይ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግስትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት፡፡ትዕግሥትም ምንም የሚጎደላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም››


ይህ የፈተናና የመከራ ወቅት የምንሰራበት፤ጌታን በግል በሚገባ የምናውቅበት፤ግንኙነታችን የሚጠልቅበትና ዕውቀታችንን ወደ ጥበብ ለመለወጥ ጊዜ የምናገኝበት መልካም አጋጣሚ ነው፡፡፡በዚህ አይነት ሁኔታ ከጌታው ጋር ተስማምቶ በጌታ መንፈስ እና ምሪት ይህንን የፈተና ጊዜ ዘልቆ የወጣ ሰውም ምስክርነቱ፣ህይወቱና ምልልሱ ጠንከር ያለ መልእክት ነው የሚሆነው፡፡


በተፈጥሮአችን ድሎተ-አፍቃሪ ስለሆንን በፍጹም እንዲህ አይነቱን ነገር ስንሸሽ ነው የምንኖረው፡፡በጣም ነው የምንፈራውም፡፡ምክንያቱም አንድ ነገር ነው-ሰለሚያመን!ስለዚህ ነው ጌታ ወዳልጠበቅነው የህይወት ሁኔታ ውስጥ እያባበለና እየከተተ ለእጆቻችን ሰልፍን የሚያስተምረን(መዝ 18፡34)፡፡ከድሎት ሰፈር ወደ ተግዳሮት ሰፈር እየወሰደ የሚቀርጸን!


በመከራና በተግዳሮት ውስጥ ሳለን ደስ የሚለው ነገር የአጽናኙ የመንፈስ ቅዱስ ድጋፍ አለን፡፡በፍጹም ለደቂቃም ቢሆን አይለየንም፡፡በተለይ በጸሎት በሚገባ ለምንተጋ ሰዎች ተግዳሮቱን የምንጋፈጠው የጌታ ህልውና በሚታወቀን መጠን ስለሆነና ልባችን በእግዚአብሔር ሰላም እየተጠበቀ ስለሆነ በተገላቢጦሽ በሕይወታችን የማይረሳ የበረከት ጊዜ ሁሉ ሊሆልንን ይችላል የሚል መረዳት አለኝ፡፡እንዲህም አይነት ምስክርነት ያላቸው ብዙ ሰዎችንም አውቃለሁ፡፡


በእንደዚህ አይነት የፈተና ሰአት ሰዋዊ፣ስጋዊ፣እና ኢ-መጽሀፋፍ ቅዱሳዊ ስልቶችንና አካሄዶችን በመጠቀምና ከእግዚአብሔር መለኮታዊ አጀንዳ እንዳናፈነግጥና የበረከታችን ዘመን እንዳይረዝም ከጌታ ጥበብና ጸጋ እንዲበዛልን ብዙ መቃተትና መጮህ ያስፈልገናል፡፡ወደ ኮምፎርት ዞን የሚመልሱ አቋራጮችን ተጠቅመን ከመለኮታዊ አሰራሩ ሾልከን እንዳንወጣም በሀይል ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡


በመጨረሻ በተግባር ደረጃ እንዲህ እናድርግ፡-

  • በእርሱ ፊት ያለማቅማማት ጨክነን እንውደቅ

  • እንጹም  

  • በተመሳሳይ የህይወት ሁኔታ ካሉና ካለፉ ሰዎች ጋር አብረን በመሆን የጌታን ፊት እንፈልግ

  • ከቃሉ ጋር ያላሰለሰ ቁርኝት እናድርግ

ያለንበትን የህይወት ሁኔታ በድል እስክንወጣው ድረስ ክእርሱ ጋር እንጣበቅ!!


በቀለ በላቸው(ዶ/ር)
beke_abay@yahoo.com
240-330-5004

Saturday, March 8, 2014

የሀጢያት ስርና መፍትሄው




የሀጢያት ስርና መፍትሄው

ሀጢያት ውስጣችን ያለና የሚኖር መርዝ ነው፡፡እንደዚያም ሆነን ነው የተፈጠርነው(መዝ 515)፡፡ልክ እንደ ማግኔት ህግ ሁለንተናችንን ወደ ክፋት በማዘንበል ከእግዚአብሔር  እንድናፈነግጥ ይስበዋል፡፡እንግሊዝኛው ‹‹indwelling sin›› ብሎ ነው የሚገልጸው-አብሮን ነዋሪነቱን ለመግለጽ፡፡ለዚህ ነው በጎን ከማድረግ ይልቅ ክፋትን ማድረግ የሚቀለን፡፡


እግዚአብሔር በምህረቱ አስቦን ካልሳበን በስተቀር በውስጣችን እግዚአብሔርን የሚፈልግ ነገር የለንም(ሮሜ 311)፡፡ቃሉ እንዲህ ይነበባል፡-

‹‹ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤አስተዋይ የለም፤እግዚአብሔርን የሚፈልግ የለም፤ሁሉም ተሳስተዋል በአንድነት የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ቸርነት የሚያደርግ የለም አንድ ስንኳ የለም››

ይህ ነው ትክክለኛ ማንነታችን፡፡ውጫችን ሀይማኖተኛ ቢመስልም፤ውጫችን የሞራል ሰው ቢመስልም እግዚአብሔር በቸርነቱ ካልጠራን እና ካላወጣን በስተቀር ከዚህ ማጥ የመውጣት አቅሙም ሆነ ዝንባሌውም የለንም(ዮሀ 644)፡፡አንድ የእግዚአብሔር ሰው ‹‹በግብዣ ብቻ ወደ እርሱ እንድንመጣ ብንጋበዝ ሁላችንም እንጠፋ ነበር›› ብለዋል፡፡በእዝራ 11-3 እና ቁጥር 5 ላይ ‹‹የህዝቡን መንፈስ አነሳሳ››እንደሚል ‹‹መፈለግንም ማድረግንም በእኛ ውስጥ የሚሰራው››(ፊሊ 213) እራሱ ነው፡፡የተወደደችው ሰአት ስትመጣ ልባችን ለጥሪው ያነሳሳል፡፡ይህም የሚያሳየን ሰው ወደ ጌታ ለመምጣት ያለበትን የተጋረጠ የውስጥ አደጋ ነው፡፡ምህረቱ ብዙ ነው እንጂ ብዙዎቻችን የት ነበርን? ይህ በሚገባ ሲገባን በሀይል አመስጋኞች እንሆናለን፡፡


ሀጢያት ብዙ ውጤቶች አሉት፡፡መዝ 38 ስታጠኑ በእያንዳንዱ ጥቅስ ላይ የተዘረዘሩትን ትኩረት ሰጥታችሁ ብታይዋቸው ያሉብንን አደጋዎች በሚገባ መገንዘብ ትችላላችሁ፡፡መዝ 383-10 ላይ ብዙዎቹ የሀጢያት መዘዞች ተጠቅሰዋል፡፡ዳዊት በዚህ ክፍል ውስጥ፡-

  • ለአጥንቶቼ ሰላም የላቸውም ይለናል
  • ቁስሌ ሸተተ በሰበሰም በማለት የውስጥ መንፈሳዊ ሁኔታውን ይነግረናል
  • ጎሰቆልሁ ተዋረድሁም በማለት የሀጢያትን የማሸማቀቅና የመከራ መዘዝ ያሳየናል
  • በማህበራዊ ህይወቱ ስድብን እንደጠገበ ይነግረናል
  • ጤና እንደሌለውም ይገልጽልናል
  • በድንጋጤ ውስጥ እንዳለ ይነግረናል
  • ሀይል እንዳልቀረለት ገልጾልናል
  • ማየት እንደተሳነውም ሁሉ ጽፎልናል
  • ከነዚህም የተነሳ ማህበራዊ ህይወቱ እንደተበላሸ እና ዘመድ አዝማድ እና ጓደኛ እንደራቀው እናያለን
የዚህን መዝሙር ሙሉ ምእራፍ ስናነብ የምንገነዘበው ሀጢያትንና የሚያመጣውን መዘዝ ነው፡፡ማለትም ሀጢያት -
  • ነፍስን ያደክማል
  • ሀይልን ያሳጣል
  • ስብራትን ወደ ህይወታችን ያመጣል
  • መንፈሳዊ እይታችንን ይጋርዳል(መዝ 4012)
  • ማህበራዊ ህይወታችንን ያበላሻል
ሰው በተፈጥሮው የሀጢያት ባሪያ ነው(ዮሐ 836)፡፡ለዚህ ነው ዳግመኛ መወለድ የሚያስፈልገን(ዮሀ 33-8)፡፡ለዚህ ነው የልብ መገረዝ የሚያስፈልገን(ቆላ 211-13፡፡ለዚህ ነው ሀዋርያው ዮሐንስ በዮሐ 39 ላይ ‹‹ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ሀጢያትን አያደርግም ዘሩ በእርሱ ይኖራልና ከእግዚአብሔር ተወልዶአልና ሀጢያትን ሊያደርግ አይችልም››ብሎ የሚነግረን፡፡ስለዚህ ነው ዳግመኛ ስንወለድ ድንገት ተሳስተን እንጂ ወድደን፣ተስማምተን እና ደስ ብሎን ያለምንም ወቀሳ ሀጢያትን መስራት የምናቆመው፡፡ትልቅ ለውጥ በህይወታችን ስለሚኖር እርሱን ደስ ለማሰኘትም እንቀናለን፡፡


ኤፌ 21-2 ዳግመኛ ከመወለዳችን በፊት የነበርንበት መንፈሳዊ ሀኔታ ነው የሚያሳየን፡፡እንዲህ ይነበባል፡-

‹‹በበደላችሁና በሀጢያታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤በእነርሱም በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሰራው መንፈስ አለቃ እንደሆነው በአየር ላይ ስልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ በፊት ተመላለሳችሁባቸው፡፡በእነዚህ ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ የስጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን በስጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበር እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን››

አስፈሪ ሁኔታ ውስጥ እንደነበርን አገላለጹ በሚገባ ያሳየናል፡፡የስጋችንንና የልቡናችን ፈቃድ ነበር መሪያችን፤አለቃችንም በአየር ላይ የሚሰራው የመንፈስ አለቃ፡፡ከዚህ አይነት ዘግናኝ ሁኔታ ነው መንጭቆ የሚያወጣን በትህትና እጅ ወደ ላይ ብንል፡፡


ለዚህም ነው በዋነኛነት ኢየሱስ ወደዚች ምድር የመጣልን፡፡ኢሳ 426-7 ላይ የኢየሱስን ተልእኮ ሲናገር እንዲህ ይላል፡-

‹‹እኔ እግዚአብሔር በጽድቅ ጠርቼህማለሁ፤የእውሩንም ዓይን ትከፍት ዘንድ የተጋዘውንም ከግዞት ቤት በጨለማም የተቀመጡትን ከወህኒ ቤት ታወጣ ዘንድ ለህዝብ ቃል ኪዳን ለአህዛብ ብርሀን አድርጌ እሰጥሀለሁ››

ወደ ጌታ ያልመጣ ሰው የሀጢያት ወህኒ ውስጥ እንዳለ ነው ይህ ቃል የሚነግረን፡፡እውሮችም ጭምር እንደሆንንም ይነግረናል፡፡ከእርሱ ጋር ተስማምተን ‹‹እነሆኝ›› ብለን እራሳችን ለዚህ የህይወት ብርሀን ስንሰጥ ከሀይለኛ የግዞት ሰፈር እንወጣለን፡፡አይኖቻችንም ተከፍተው የት እንደነበርን እናስተውላለን፡፡የነጻነት አየር እንተነፍሳለን፡፡ከወቀሳ እና ከእፍረት እንድናለን፡፡ማህበራዊ ግንኙነታችን ይታደሳል፡፡መለኮታዊ ሰላምና ደስታን ምን እንደሚመስል መቅመስ እንጀምራለን፡፡


ተግተን ከቀጠልንም እየተለቀቀን እና ወደ ሰፊ ስፍራ እየወጣንና(መዝ1819) እየተለወጥን እንመጣለን፡፡ዳዊት ከእንደዚህ አይነት ድል በኋላ መዝ 3011 ላይ ‹‹ክብሬ ትዘምርልህ ዘንድ ዝምም እንዳትል ልቅሶዬን ለደስታ ለወጥህልኝ፤ማቄን ቀድደህ ደስታን አስታጠቅኸኝ››ብሎ እንደሚናገር ሀዘናችን እና ቁዘማችን ሁሉ በሰላምና በደስታ ይቀየራል፡፡ይህን በህይወቴ ስላየሁ ህያው ምስክር ነኝና ሳታቅማሙ በፊቱ በትህትና ኑና ውደቁ ይገላግላችኋል፤በቃላት ሊገለጽ የማይችል ነጻነትን ያጎናጽፋችኋል!!


Bekele Belachew
240-330-5004 
beke_abay@yahoo.com