Tuesday, December 10, 2013

ንስሓ እና ጥቅሙ





ንስሓ እና ጥቅሙ


ንስሓ ማለት ወደ እግዚአብሔር በሚገባ በመመለስ እንደገና ወደ ኋላ ላለመመለስ መወሰንና መሰጠት ነው፡፡ከዚህ ሀሳብ ጋር የሚስማማ የእንግሊዝኛ ትርጉም፡-

“Repentance is the act of turning from sin and making a commitment not to return. Doing a complete turn around changing directions making a decision to put away the old man.”(David Wilkerson)


ንስሓን በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡የመጀመሪያው የንስሓ አይነት ስር ነቀል ዋጋ ከፍለን ወደ ጌታ ለመመለስ የምንከፍለው እርምጃ ነው፡፡ይህ መንፈሳዊ እርምጃም ከጨለማ ወደ ሚደነቅ ብርሐኑ እንድንገባ ያዘጋጀናል፡፡ከነበርንበት ማጥ አውጥቶ ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግስት እንድንገባ ልባችንን ያመቻቻል፡፡ይህ የንስሓ አይነት በህይወታችን ትልቅ እና ወሳኝ እርምጃ ከመሆኑም የተነሳ ጨክነን ካደረግነው ወደ ህይወታችን የሚመጣው የሰላም፣የደስታ እና የእረፍት ለውጥ ቀላል አይደለም፡፡
ሁለተኛው አይነት ንስሓ ወደ ጌታ ከላይ በተጠቀሰው እርምጃ ወደ ቤቱ ከመጣን በኋላ ወደ እርሱ እስከምንሄድበት ቀን ድረስ እለት እለት የምናከውነው የክርስትናችን የጀርባ አጥንት ነው፡፡አንድ የእግዚአብሔር ሰው እግዚአብሔር የሚከተሉት ሁለት ነገሮች ያሉትን ሰው በእጅጉ እንደሚባርክ የተናገሩት ነገር ውስጤ ታትሞ ቀርቷል፡፡እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፡-

  • ንስሓ የሚገባ ልብ(repentant heart)

  • ፈውስን የሚጠባበቅ ልብ(expectant heart)

እውነተኛ ንስሃን የሚለማመድ ሰው በሕይወቱ ለሚገርም በረከት የእግዚአብሔርን ልብ ያዘነብላል፡፡እውነተኛ ንስሓም ህይወትን አድሶ ለማቆም ዋነኛ መንገድ ነው፤የእግዚአብሔርን የማጽናናትና የመደገፍ ክንዱን የምንቀምስበት!መኪና እንደልብ እንዲንሸራሸር የተደፈኑት የዘይት ቧንቧዎቹ መጠረግ እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ ከተጠላለፍንባቸው እግዚአብሔርን ከሚያሳዝኑ ሀጢያቶች እና ርኩሰቶች የምንጠራበት መንገድ ንስሀ ነው 1ዮሐንስ 19 አስረግጦ እንደሚነግረን -“በኃጢአታችን ብንናዘዝ ጢአታችንን ይቅር ሊለን ከአመጻም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው”::እጅግ የሚደንቅ ቃል ነው፡፡ከአመጻም ሁሉ ሊያነጻንየሚለው ቃል ላይ እንድታሰምሩልኝ እፈልጋለሁ፡፡እጅግ የሚደንቅ የተስፋ ቃል ነው፡፡ከአንዳንድ ኃጢአት ሳይሆን እግዚአብሔርን ካሳዘንባቸው ማንኛውም ነገሮች ሁሉ እንደሚል ልናስተውል ይገባል፡፡ሊያነጻንየሚለው ቃል ሊያጥበን፣ሊፈውሰን ፣ሊያጠራን ወዘተ የሚል ትርጉም ይዟል፡፡ይህ የመንፈስ ቅዱስን ውስጥን የማጽዳትን ኃይል እና የማሳመር ስራን በሚገባ ያሳየናል፡፡አዎ ከልብ በእውነትና በመንፈስ የተጸለየ የንስሓ ጸሎት ውስጥን በሚገባ ያነጻል፣ያድሳል፣እንደገናም ያቆማል፡፡


ኢሳይያስ 118 “ኑና እንዋቀስ ይላል እግዚአብሔር ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነጻለች እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለችይላል፡፡ይህ ቃል የንስሓን ውስጥን በፍጹም የመለወጥ ኃይል ምሳሌያዊ በሆነ መልኩ የሚገልጽ ሲሆን ሁለት በምንም መልኩ የማይገናኙ ነገሮችን እያወዳደረ እናያለን፡፡እንደዚህ አስቀምጫቸዋለሁ፡-
  • አለላ (ደማቅ ቀይ በስሱ ከቢጫ ቀለም ጋር የተደባለቀ ቀለም-scarlet) ----------›አመዳይ(እንደ በረዶ ነጭ)

  • ደም (ደማቅ ቀይ-crimson) --------------› ባዘቶ(እንደ ሀር ነጭ)
ከላይ ያሉት ንጸጽሮች በምንም መልኩ እጅግ የተራራቁ እንደሆነ ሁሉ ከልብ የተደረገ ንስኃም ውስጣችን  በእንዴት አይነት ሁኔታ ሊቀይር እንደሚችል ነው የሚያስገነዝበን፡፡አዎ ንስሓ ውስጣችንን የማሳመርና ከጌታ ጋር ያለንን ሕብረት በሚገባ የማደስ ኃይል አለው፡፡ 


ንስሓ ማለት ምን ማለት ነው ተብዬ ብጠየቅ መዝሙር 51 ነው ብዬ የምመልስ ይመስለኛል፡፡መዝሙር 51 በመግቢያ ላይ እንደተገለጸውንጉሥ ዳዊት ወደ ቤርሳቤህ ከገባ በኋላ ነቢዩ ናታን ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ የዳዊት መዝሙርብሎ ነው የሚጀምረው፡፡ዳዊት ያንን የዝሙት ኃጢአት ካከናወነና እና የግድያ ወንጀልን በኦርዮ ላይ ከፈጸመ በኋላ ኃጢአቱን ሳይናዘዝ ከአንድ ዐመት በላይ እንደ ቆየ የተወለደው ልጅ ዕድሜ ይነግረናል፡፡እግዚአብሔር ነቢዩ ናታንን የላከው ንጉሥ ዳዊት ኃጢአቱን የመናዘዝ አቅም ስላጣ ነው፡፡ዳዊት በኃጢአት ውስጥ ሆኖ ያለውን ሕይወት አስቀያሚና ጎጂነት በመዝሙር 384-10 ላይ እንዲህ ብሎ ይናገራል፡-
  
አቤቱ በቍጣህ አትቅሠፈኝ፥ በመዓትህም አትገሥጸኝ።
ፍላጾችህ ወግተውኛልና፥ እጅህንም አክብደህብኛልና።
ከቍጣህ የተነሣ ለሥጋዬ ጤና የለውም፤ ከኃጢአቴም የተነሣ ለአጥንቶቼ ሰላም የላቸውም።
ኃጢአቴ በራሴ ላይ ከፍ ከፍ ብሎአልና፥ እንደ ከባድ ሸክምም በላዬ ከብዶአልና።
ከስንፍናዬ የተነሣ ቍስሌ ሸተተ በሰበሰም፤
እጅግ ጐሰቈልሁ ተዋረድሁም፥ ሁልጊዜም በትካዜ እመላለሳለሁ።
ነፍሴ ስድብን ተሞልታለችና፥ ለሥጋዬም ጤና የላትምና።
ታመምሁ፤ እጅግም ተቸገርሁ፥ ከልቤ ውዝዋዜም የተነሣ ጮኽሁ።
አቤቱ፥ ፈቃዴ ሁሉ በፊትህ ነው፥ ጭንቀቴም ከአንተ አይሰወርም።
ልቤ ደነገጠብኝ፥ ኃይሌም ተወችኝ፥ የዓይኖቼም ብርሃን ፈዘዘ።

 
አዎ ኃጢአት ጉስቁልና አለው፣እፍረትና የውርደት ስሜት አለው፣ጭንቀት አለው፣ትካዜ አለው፣ድካም አለው፣ሕመምድንጋጤ አለው(እነዚህን ችግሮች ጥቅሶቹ ውስጥ አንድ ባንድ ማየት ይቻላል)፡፡ባጠቃላይ ሁከት ነው፡፡ከላይ እንደጠቀስሁት ዳዊት ለብዙ ወራት በእንደዚህ ያለ ስሜት ውስጥ ሰንብቷል፡፡እግዚአብሔር የምህረት አምላክ ስለሆነ ነቢዩ ናታንን ላከበትና ጉዱን ገለጠበት፡፡ከዚያም ዳዊት በእንዴት አይነት የልብ መሰበር ውስጥ እንዳሳለፈ ነው መዝሙር 51 የሚነግረን፡፡የጸለየውም ጸሎት ወደር የለውም እጅግ የእግዚአብሔርን ልብ የሚያዘነብል ነበር፡፡ይህን ክፍል ከመቶ በላይ አንብቤዋለው፡፡በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ስሆን መጀመሪያ የማነበውም ክፍል ነውና በኃይል እወደዋለሁ፡፡
በዚህ መዝሙር ንስሓ ውስጥን ለማንጻት እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ የሚያሳየን ቁጥር 7 ነው፡፡እንዲህ ይላል፡-“በሂሶጵ እርጨኝ እነጻማለሁ እጠበኝ ከበረዶ ይልቅ ነጭ እሆናለሁ፡፡ይህ ቃል ከኢሳይያስ 118 ተመሳሳይነት አለው፡፡አዎ በቅንነት እና እግዚአብሔርን በመፍራት የተጸለየ እውነተኛ ጸሎት ከብዙ የክፋት ትርፍ ይገላግላል፤ውስጥን ይቀይራል ያሳምራልም፡፡


ከልብ የተጸለየ የንስሓ ጸሎት ውስጥን በማደስ የሚገርም መለኮታዊ ደስታ ውስጥ ይከታል፡፡በእራሴ ህይወት የእግዚአብሔርን መንፈስ በሆነ ኃጢአት ማሳዘኔ ሲገባኝ ሁለንተናው ገደል ነው የሚሆንብኝ፡፡ባዶነት ይሰማኛል ጭው ይልብኛል እደነግጣለሁም፡፡ከዚህ ስሜት የሚገላግለኝ እግሩ ስር በእውነትና በመንፈስ መደፋት ነው፡፡ሌላ አማራጭ እንደሌለ ገብቶኛል፡፡ዳዊት መፍትሄውን መዝሙር 51:7 ላይ እንዲህ በማለት ይገልጸዋል፡-“ሀሴትንና ደስታን አሰማኝ የሰበርሃቸውም አጥንቶቼም ደስ ይላቸዋል፡፡” “የሰበርሃቸው አጥንቶቼምየሚለው ሀረግ በኃጢአት የምንከፍለውን የዋጋ ከባድነት ያሳየናል-ጥልቅ መሆኑንም ጭምር!  

   
መዝ 5117 ላይየእግዚአብሔር መስዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነውእንደሚል ዳዊት በተሰበረ መንፈስ የእግዚአብሔር ፊት ፈለገ፣አነባ፣ቃተተ፣ጾመ፣በእግዚአብሔር ፊት እራሱን ጣለ፡፡ስለዚህም ዳዊት ደጋግሞ በቀደመው ዘመን በጌታ ፊት ያገኝ የነበረውን የመታደስ በረከት በጸሎት ቋንቋ ሲገልጸው ነው የምንገነዘበው፡፡አንዴ ብቻ ሳይሆን የጌታን የማዳን፣የማጽናናት፣የማደስና ደግፎ የማቆም ጉልበት በህይወቱ መቅመሱን በዚህ መዝሙር ውስጥ ያሉ አገላለጾች በሚገባ ያሳዩናል፡፡


በዚህ ጽሁፌ እኔም ላሳይ የፈለግሁት ዋናው ቁም ነገር ለትምሕርታችን የተጻፉትን የንስሓ መርሆዎች በማስተዋልና ተግባራዊ በማድረግ ግልብ ከሆነ የንስሓ ህይወት ወደ ጠለቀ ህብረትና ግንኙነት የሚከት የንስሓ ህይወት እንዲኖረን ለማሳሰብ ነው፡፡ስለዚህ በተለያዩ ከጌታ መንገድ ወጣ ያሉና መንፈሱን የሚያሳዝኑ ነገሮችን ስናደርግ ማንኛውንም ነገር አቁመን በሚገባ ለመመለስ መንፈሱ እንደሚመራን በመሆን እርምጃዎችን እንውሰድ፡፡በንስሓ ዙሪያ የተጻፉ የእግዚአብሔር ቃሎችን በማሰላሰልና በማጥናት በጸጋው ዙፋን ፊት ሆነን ልባችንን እናፍስስ፡፡ካስፈለገም እንደ ጴጥሮስ ምርር ብለን እናልቅስ እናንባ፡፡ማር 529 “ከስቃይዋ እንደዳነች በሰውነቷ አወቀችእንደሚል በውስጡ መንፈሳችን የጌታ ፈውስ እስኪታወቀን ፊቱን እንፈልግ ከወደቅንበትም አንነሳ፡፡ኃጢአቶቻችንንም ስም ሰጥተን እያንዳንዱን ጉድ በእውነትና በቅንነት እንናዘዝ፤እናም ሙሉ በሙሉ ለመመለስ እንወስን፡፡ያኔ በሚያስደንቅ ምህረቱ ከተፍ ብሎ ይፈውሰናል፤ይጠግነናል ያስደንቀናልም፡፡የእንደገናአምላክ ነውና እንደገና ሌላን እድል ይሰጠናል፡፡ፍቅሩ እጅግ ታላቅ ነውና እንደገና ጸጋን ጸጥቶ ያቆመንና ካሰብነውና ከለመንነው በላይ የፍሬ ሰዎች ያደርገናልና ፊቱን እንፈልግ!አሜን!                                                                                                                                                                                                                                                                      
                                                       




             

No comments:

Post a Comment