ውስጥን የሚለውጥ መንፈሳዊ እርምጃ
በህይወታችን እውነተኛ መንፈሳዊ ለውጥ እንዲመጣ ካስፈለገ ከምር መወሰን ይኖርብናል፡፡ብዙ ጊዜ ውጫዊ ነገሮች በመቀየራቸው
ብቻ እውነተኛ መንፈሳዊ እድገት ላይ ያለን እየመሰለን ልንታለል እንችላለን፡፡እንደ ያእቆብ ማንንም እያታለልንና እያስመሰልን ዘመናችንን
ልንጨርስም እንችል ይሆናል፡፡የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ሀሳብ ግን ውስጣችን በትክክል ተለውጦ እና እርሱን አንግሶ ከዚህ በሚመነጭ
ፍሬ እርሱን በዙሪያችን አስከብረን እንድናልፍ ነው፡፡ለዚህ አይነት ውጤት የጨከነ ማንነት እና ሁለንተናችንን በጸጋው ዙፋን ፊት
መጣል ይኖርብናል፡፡እንደዚያ ስናደርግ ብቻ ነው እውነተኛ ፍሬን በህይወታችን ማየት የምንችለው፡፡
ከላይ ለተጠቀሰው የለውጥ እርምጃ እንደ ሞዴል የሚሆነን ዘፍ 32፡22-32 ላይ ያለው ያእቆብ በህይወቱ የወሰደው እርምጃ
እና ውጤቱ ነው፡፡ለዚህ ክፍል ዳራ የሚሰጠን በዘፍጥረት መጽሀፍ የተለያዩ ክፍሎች ያእቆብ ያሳለፋቸው ውጣ ውረዶች ናቸው፡፡በነዚያ
የህይወት ውጣ ውረዶቹ ፡-
- ያእቆብ አታላይ ነበር
- ያእቆብ ከማናኛውም አይነት ሁኔታ ላይ ማትረፍ የሚወድ ራስ ወዳድ ሰው ነበረ
- ያእቆብ አስቸጋሪ ነገሮችን ከመጋፈጥ ይልቅ ይሸሽ ስለነበር እውነተኛ ሕይወት አልነበረውም
- ያእቆብ በራሱ በመደገፍ ማንኛውንም ጉዳይ በእራሱ የመፍታት አካሄድ ነበረው
- በመጨረሻም ያእቆብ በምድራዊ ሀብት ደረጃ ባለጸጋ ሆኗል ነገር ግን ያልተፈቱ ችግሮች ነበሩት
በዚህ ክፍል ያእቆብ ወደ እናት አባቱ ምድር ለመመለስ ጉዞ እያደረገ ነው፡፡ከፊት ለፊቱ ኤሳው ወንድሙ እንደ ትልቅ ጋሬጣ
በመንገዱ ላይ አለ፡፡ይህንንም ጋሬጣ እንዴት እንደሚያልፍ ጭንቅ ስለሆነበት በዘፍጥረት ምእራፍ 32 ላይ አንዴ ይጸልያል፣አንዴ በእጅ
መንሻ ለማምለጥ ይዘይዳል፣አብረውት ያሉትን ባሪዎቹንና ንብረቶቹን ለሁለት ከፍሎ ይህንን አስቸጋሪ ሁኔታ ለማለፍ የሚችለውን ያህል
መፍትሄ እያበጀ ነው ያለው፡፡ግን ይህ ሁሉ ዝየዳ መጨረሻ ላይ እንደማይጠቅመው ከተረዳ በኋላ አስደናቂ እርምጃዎችን ማድረግ ጀመረ፡-
- አብረውት ያሉትን ሁሉ ከፊት አስቀድሞ የያቦቅን ወንዝ አሻግሮአቸው ለብቻው ቀረ፡፡ያቦቅ ማለት እራስን ባዶ ማድረግ ማለት ነው-በእንግሊዝኛው በቀጥታ ሲተረጎም እንዲህ ነው፡-‘emptying’
- ካንድ ሰውም ጋር እስከ ንጋት ይታገል ነበር፡፡ብዙ የመጽሀፍ ቅዱስ አዋቂዎች ይህ ሰው ኢየሱስ ነው ይላሉ
- ሊነጋ አቀላልቶአልና ልቀቀኝ ሲለው ያእቆብ “ካልባረክኸኝ አልለቅህም ”አለ-እጅግ በህይወታችን የሚያስፈልገን ድንቅ ውሳኔ እና ጸሎት
- ለመጀመሪያ ጊዜ እውነተኛ ማንነቱን ተናገረ፡፡ሰውየው ስምህ ማን ነህ ሲለው ያእቆብ ነኝ አለ ያእቆብ ማለት አታላይ ማለት ነው-እውነተኛ ለውጥ ፈላጊም እንደሆነ አስመሰከረ
ይህ ያእቆብ የታገለው
ትግል ኢየሱስ በጌተሰማኒ ከጸለየው እና እራሱ ለሀጥያት መስዋእት አድርጎ ለመስጠት ካማጠበት እና ከቃተተበት የጸሎት ትግል ጋር
ተመሳሳይነት እንዳለው የመጽሀፍ ቅዱስ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡ከዚህም ምጥና መስዋእት በኋላ ያፈራውን ፍሬ ኢሳ 53፡11 እንዲህ ይገልጸዋል፡-‹ነፍሱን
ስለ ሀጢያት መስዋእት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል እድሜውም ይረዝማል የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል፡፡ከነፍሱ ድካም ብርሀን
ያያል ደስም ይለዋል…..››
ያእቆብ ከዚህም መንፈሳዊ
ትግል የተነሳ ስሙ ተለወጠ፡፡እስራኤል ማለት “ከእግዚአብሔር ታግሎ ያሸነፈ” ማለት ሲሆን በእንግሊዝኛው እንዲህ ይተረጎማል፡- "Triumphant
with God" ወይም “who
prevails with God”ከዚያ አስደናቂ ትግል
በኋላ ሲመሰክርም “እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየሁት ሰውነቴም ድና ቀረች”ብሎ ውጤቱን ተናገረ፡፡ምእራፍ 33 ላይ እንደምናየው ከኤሳውም
ጋር በሰላም ነው ተሳስመው የተተላለፉት-ከእግዚአብሔር ጋር ስንስማማ ጠላቶቻችን እንኳ ከእኛ ጋር እንዲስማሙ ማድረግ ይችላልና ነው፡፡
ያእቆብ የወሰዳቸው
እርምጃዎች እግዚአብሔርን በህይወቱ ፊት ለፊት እንዲያይ አድርገውታል፡፡በእኛም ህይወት እንዲህ አይነት ጊዜዎች እንዳይኖሩን እራሳችንን
መከልከል የጠለቀ ግንኙነት እንዳይኖረን ያደርጋል፡፡ያለ እውነተኛ መንፈሳዊ ትግልም ለውጥ የለም፡፡በእርሱ ፊት እራሳችንን ባዶ የምናደርግበት
፣በፊቱ ወድቀን እውነተኛ መዳሰስ እንዲመጣ ፊቱን ከምር የምንፈልግባቸው ጊዜያት ያስፈልጉናል-አንዴ ሳይሆን በርከት ያሉ ጊዜያት!
በዚህ ዙሪያ የነበረኝን
ልምድ ቢጠቅም ላካፍል፡-
አንደኛ፡-ወደ ጌታ
ከመምጣቴ በፊት በዛው ህይወት እንዳልቀጥል ህይወቴ እንደ አይን ጠፍቷል ወደ ጌታ እንዳልመጣ እና እንዳላርፍ ብዙ የታሰርኩባቸው
ነገሮች ጠላልፈውኛል፡፡በዚህ አይነት ሁኔታ ሆኜ እየዋዠቅሁ ለመወሰን ያሳለፍኩት ወደ ስድስት ሰአት የሚጠጋ የትግል ወቅት ትዝ ይለኛል፡፡ልክ
ስወስን እና እራሴን በጌታ ላይ ስጥል ክፍሉ በብርሀን ተሞላ፣የደስታ መንፈስ አጥለቀለቀኝ ብዙ ሳልቆይ ትልቅ ለውጥ ወደ ህይወቴ
መጣ
ሁለተኛ፡-ሀይለኛ የቀለም
እልህ ነበረኝ፡፡እንዳሰብኩት ነገሮች ሳይሰምሩ ዘመኔ ሄደ በማለትም የውስጥ ሀዘን ነበረኝ፡፡ወደ አሜሪካ ከመጣሁ በኋላ በህክምና
ሙያ ለመቀጠል የህክምና ቦርድ ፈተና መውሰድ ነበረብኝና የመጀመሪያ ፈተናዬን በጥሩ ውጤት አልፌ ለሁለተኛው ፈተና እየተዘጋጀሁ ነበር
ያለሁት፡፡ጌታ ግን እየሄድኩበት ያለው መንገድ እርሱ ያሰበው መንገድ እንዳልሆነ እና እርሱን እንዳገለግለው በተለያዩ መንገዶች ሲናገረኝ
ኖሯል፡፡አንድ የመጨረሻ ሌሊት ግን ማጥናት እና ማንበብ በማልችልበት ሁኔታ የጸሎት መንፈስ ወደቀብኝ፡፡ንባቡን ወደ ጎን አድርጌ
ሌሊቱን ሙሉ በሚገርም ሁኔታ ስጸልይና ስቃትት እና ከእራሴ ጋር ስታገል አድሬ ወደ ንጋቱ ላይ ግልጽ በሆነልኝ መንገድ ሙሉ በሙሉ
መንፈሳዊ አገልግሎት ላይ ብቻ ዘመኔን እንድጨርስ እንደሚፈልግ ገብቶኝ ልክ ከእርሱ ጋር ስስማማ እንዴት እንደተነፈስኩ አትጠይቁኝ፡፡ያንን
ቀን እግዚአብሔርን ፊት ለፊት የአየሁት ያህል ነበር የተሰማኝ፡፡ልዩ ጊዜ ነበር፡፡አሁን የምኖርለት አላማ ገብቶኝና ሁለመናዬን አስረክቤ
በምሪቱ ውስጥ ለመሆን ሌት ተቀን እየተጋሁ እገኛለሁ፡፡በዛ ቀን ውስጤ የገባው ብርሀንና የጌታ ድምጽ በማይረሳ መልኩ ልቤ ላይ ታትመው
ቀርተዋል፡፡
ሁላችንም የምንታገልባቸው
ብዙ ነገሮች አሉን፡፡ያብዛኞቻችን ህይወት ከያእቆብ ጋር በሚገባ ይመሳሰላል፡፡የያእቆብ ልቡ፣አካሄዱ እና ስሙ እንደተለወጠ ጌታ ሊለውጠንና
የፍሬ ሰዎች ሊያደርገን ይፈልጋል፡፡ግን አንድ ነገር ከእኛ ይፈልጋል ብዬ አምናለሁ-በበቂ ሁኔታ መገኘታችንን!!
ያእቆብ ከእግዚአብሔር
ጋር ታግሎ አሸነፈ የሚለው ሀሳብ እግዚአብሔርን ማሸነፉ ሳይሆን ለእግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ መሰጠቱ እና መገዛቱ ነው እንደ ማሸነፍ
የተቆጠረለት፡፡እውነተኛ መንፈሳዊ ለውጥን ፈለገ!እግዚአብሔር በህይወታችን የበላይ መሆኑም የአሸናፊነታችን ሁሉ ምንጭ ነውና ያእቆብ
ከሰውም ከእግዚአብሔርም ጋር ታግለህ አሸነፍክ ተባለ፡፡የወሰዳቸው እርምጃዎቹ እና ያሳለፈው ያ ድንቅ የሌሊት ትግል እግዚአብሔርን
ፊት ለፊት እንዲያይ አደረገው፡፡
እኛም በእንደዚህ አይነት
ውሳኔና ረሀብ በፊቱ ብንሆን እና ሳናቅማማ እራሳችንን በፊቱ ብንጥል እናየውና ተለውጠን እንቀራለን ብዬ አምናለሁ፡፡አለበለዚያ ግን
ህይወት የሌለን፣ሀይማኖተኛ፣ግብዝ፣አስመሳይ እና ከእውነት የራቅን ነው የምንቀረው፡፡በላይ በተጠቀሱት መንፈሳዊ ሂደቶች ውስጥ ስናልፍ
ግን እምነታችን ይጠነክራል ያድጋል ብሎም ግትረኝነት እልህ ከህይወታችን ይወገዳል፤እውነተኛ የልብ መሰበርና ትህትናም መገለጫችን
ይሆናል፡፡
አሳዛኙ ነገር በህይወታችን
ብዙ ጊዜ ዋናው ፍላጎታችን “ኤሳው”እንዲለወጥ ነው የምንፈልገው ቢሆንም አንዱ “ኤሳው” ከህይወታችን ቢወገድ ሌላው ይመጣል በምድር
እስካለን ድረስ፡፡ነገር ግን እግዚአብሔር በማንኛውም የህይወት ውጣ ውረድ ነጥሮ የሚወጣ ማንነትን ሊሰጠን ስለሚፈልግ እኛን ከውስጥ
መለወጥ ነው የሚፈልገው፡፡ለዚህ ደግሞ የእኛን ፈቃደኝነት ይፈልጋል፡፡ስለዚህ እሺ እንበለው፡፡እጆህ ይስሩኝ ያበጃጁኝ እንበለው መስራትና
መለወጥ ያውቅበታልና!‹‹እንዳላሸነፈውም ባየ ጊዜ የጭኑን ሹልዳ ነካው››እንደሚል ሰባብሮ የራሱ ሊያደርገን እና ትሁት አድርጎ የሚጠቅም
የክብር እቃ ሊያደርገን ይመኛልና እንፍቀድለት፡፡
በመጨረሻም እጅግ ለጸሎት
ህይወቴ መሰረት የሆነኝ ሀሳብ ላይ ልናገር እና ጽሁፌን ልጨርስ፡፡ያእቆብ ካደረጋቸው እርምጃዎች እጅግ የሚያስደስተኝ “ያእቆብም
ለብቻው ቀረ”የሚለው ሀሳብ ነው፡፡በዛች አመሻሽ ቀን በሀሳብ እና በጉልበት ሊረዱት የሚችሉ ሰዎችን ሁሉ አሻግሮ ለብቻው ሆነ፡፡እውነተኛ
ውስጣዊ ለውጥን ፈልጎአልና ውጫዊ ከበባን አስወገደ፡፡አዎ በዚህ ግርግር በበዛበት እና የሰውን ቀልብ በተለያየ መልኩ የሚስቡ ነገሮች
በበዙበት አለም ብቻን በመሆን ለጌታ መገኘት የሚቻልባቸው አጋጣሚዎች የጠበቡ ቢሆንም እንደ አጋጣሚ እንደዚህ አይነት ጊዜዎች ሲገኙ
መታለፍ የለባቸውም ባይ ነኝ፡፡በነዚህ ጊዜዎች የምናሳልፋቸው በርከት ያሉ ሰኣታት ወደ ፊት የሚኖረን ህይወትና አገልግሎት በእጅጉ
ይወስኑታልና ያለመሰሰት እራሳችንን እግሩ ስር እንጣል፡፡እግዚአብሔር ሆይ እንደ ያእቆብ በፊትህ የከበረን ጊዜን ስጠን!!
No comments:
Post a Comment