Friday, November 29, 2013

የመከራ እሳት እና መፍትሄው



የመከራ እሳት እና መፍትሄው

ወደ ህይወታችን የማይመጣ የፈተናና የመከራ አይነት የለም፡፡መጽሀፍ ቅዱስን ስናጠና አብዛኛዎቹ የእግዚአብሔር ሰዎች በብዙ ፈተናና መከራ ውስጥ እንዳለፉ እናስተውላለን፡፡እያንዳንዱን ፈተና በእግዚአብሔር ጸጋ እና ምሪት ተደግፈን እና ኢየሱስን እያየን ከተጋፈጥነው እምነታችን እየጠነከረና ወደ ፊት ተመሳሳይ ነገሮች ሲገጥሙን የምንመክትበትን አቅምና ጥበብ እየጨመርን እንመጣለን፡፡


በአዲስ ኪዳን መጻህፍት ውስጥ ሃዋርያው ጳውሎስ ስለ ወንጌል እጅግ ከፍ ያሉ መስዋእቶችን እንደከፈለ በጽሁፎቹ ውስጥ እናስተውላለን፡፡እነዚህንም መከራዎች በእግዚአብሔር ጸጋ ተቋቁሟቸውም እንዳለፈ ጽፎልናል፡፡2 ቆሮ 4፡7-10 በውስጣችን እግዚአብሔር ካስቀመጠው መዝገብ የተነሳ የሚደርሱብንን መከራዎች ዘርዘሮ አስቀምጧቸዋል፡፡እነርሱም እንዲህ ይነበባሉ፡-

  • እንገፋለን

  • እናመነታለን

  • እንሰደዳለን

  • እንወድቃለን

  • የኢየሱስን ሞት በስጋችን ተሸክመን እንዞራለን

  • ዘወትር ለሞት አልፈን እንሰጣለን

ክርስትያን ከመሆናችን የተነሳ ብዙ ነገሮች ይደርሱብናል፡፡የመከራው እና የፈተናው መጠን እንደ እንቅስቃሴያችን መጠን ይወሰናል፡፡ብዙ ለወንጌል የምንሮጥ ከሆነ የተግዳሮቱና የስቃዩ ብዛት እንደዛው ያይላል፡፡ጌታን ለማገልገል ደፋ ቀና በምንል ክርስትያኖች ላይ ሰልፉ እጅግ ብርቱ ነው፡፡ጠላት በተለያየ መንገድ ተስፋ ለማስቆረጥ እና ሩጫችንን እንድናቆም የማይልከውና የማያመጣው ተግዳሮት የለም፡፡


የሃዋርያው ጳውሎስን ጽናት እንድንገረም የሚያደርገን ቃል 2 ቆሮ 4፡16-17 ላይ እናገኛለን፡፡እንዲህ ይላል፡-‹‹…አንታክትም ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን እለት እለት ይታደሳል››በዚህ ቃል ላይ ሀዋርያው ጳውሎስ ለውጫዊው ማንኛውም ነገር ደንታ እንዳልነበረው እናያለን፡፡ይልቁንም ውስጣዊ ማንነታችን ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለብን ያስገነዝበናል፡፡ምክንያቱም ማንኛውም ውጫዊ ነገር ጠፊ ነውና ነው፡፡‹‹የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ››የሚለው ሀረግ የሰውነታችንን መጎሳቆል ብቻ የሚወክል ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም የምናጣቸውንና የሚጎድሉብንን ማንኛውንም ውጫዊ ነገሮችን ሁሉ ይወክላል፡፡በተለያዩ ጫናዎች ውስጥ ስናልፍ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በቂ ህብረት እያደረግን ከተጣበቅን የውስጡ ሰውነታችን እየታደሰና እየጠነከረ ስለሚሄድ የጠለቀ ህብረት ውስጥ እራሳችንን እናገኘዋለን፤ጌታንም ልዩ በሆነ መንገድ እያወቅነው እንመጣለን፡፡እዚህ ዘላለማዊ ትርፍ ላይ ነው ትኩረትም ማድረግ ያለብን፡፡


ሮሜ 5፡3-5 ላይ ያለው ቃል የመከራን መለኮታዊ ጥቅም እንዲህ ባለ ተዋረድ ያስቀምጠዋል፡-
ፈተና-------›ጽናት----------›መገለጫ ባህርይ---------›ተስፋ
በምናልፋቸው መከራዎች የጌታ የማዳን ክንድ እና አብሮነቱ እየታወቀንና እምነታችን እና ተስፋችን እየጨመረ ይሄዳል፡፡ተስፋ የምናደርገው ዘላለማዊ ህይወት ደግሞ ማስረጃ እና የሚጨበጥ ነገር በሚገባ አለው፡፡ተስፋው በፍጹም የሚያሳፍር አይደለም ለምን ቢባል ለተስፋው ማረጋገጫ የሚሆን የመንፈስ ቅዱስ ፍቅር በሚገባን እና በሚታወቀን መልኩ በልባችን ስለፈሰሰ ነው፡፡


ወደ ህይወታችን የሚመጣው ፈተናና ተግዳሮት ያለንን እምነትና ጽኑነት በሚገባ ይፈትሸዋል፡፡ወርቅ በእሳት እንደሚነጥር እና እላዩ ላይ ያሉት የማይረቡ ነገሮች እንደሚወገዱ ሁሉ የሚመጣው የመከራ እሳት አላስፈላጊ ነገሮችን እየጣል ከጌታ ጋር የበለጠ እንድንጣበቅ ያደርገናል፡፡ከዚህ የተነሳ ለጌታ ያለን ምስጋናና አምልኮ ልዩ ነው የሚሆነው-የማዳን እና የማጽናናት ክንዱን በሚገባ እንቀምሳለንና!ይህንን ሀሳብ በሚገባ የሚገልጽ ቃል 1ጴጥ 1፡6-7 ላይ እናገኛለን፡፡እንዲህ ይነበባል፡፥‹‹በእሳት ምንም ቢፈተን ከሚጠፋው ወርቅ ይልቅ አብልጦ የሚከብር የተፈተነ እምነታችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ ለምስጋናና ለክብር ለውዳሴም ይገኝ ዘንድ አሁን ለጥቂት ጊዜ ቢያስፈልግ በልዩ ልዩ ፈተና አዝናችኋል››እጅግ የሚገርም ቃል ነው፡፡ፈተናው እምነታችን እንዲጠነክር እና ከጌታ ጋር እንድንጣበቅ ትልቅ አጋጣሚን ፈጥሮልን ያልፋል፡፡ስለዚህ ያለው መለኮታዊ ትርፍ ቀላል አይደለም፡፡ስለዚህ ፈተናን በዚህ እይታ(perspective) ነው መመልከት ያለብን፡፡ፈተናው ለጊዜው ያሳዝነናል፣ልባችን ይሰበራል እንዳውም የማንነሳ እስኪመስለን ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን ነገር ግን መከራው ለህይወታችን አስፈላጊ የህይወት ቅመሞችን ሰጥቶን ያልፋል፡፡


በእራሴ ህይወት አንገት የሚያስደፉ ብዙ ችግሮች ደጋግመው ደርሰውብኛል፡፡በእነዚያ ጊዜዎች እንደ ሰው በሀይል አዝኛለሁ፡፡ተስፋ እስከ መቁረጥ የደረስኩባቸውም ጊዜዎችም ነበሩ፡፡ወደ ልቤ ተመልሼ እርሱ የመፍትሄ አምላክ መሆኑን እና ከእነዚያ ጉዶች ሊያወጣኝ እንደሚችል በመረዳቴና እራሴን በጸጋው ዙፋን ፊት በመጣሌ እና ችግሩ እስኪያልፍ በጸሎት መንፈስ ውስጥ በመሆኔ የሚገርመውን የማጽናናት ክንዱን፣ቸርነቱንና ምህረቱን በሚገባ አይቻለሁ፡፡እርሱን ማን ይመስለዋል?እንደርሱስ አጽናንቶና ህይወትን አድሶ እንደገና የሚያቆም ማን አለ?


አዎ በእርግጠኝነት መከራው ያልፋል፡፡በዚህ ጊዜ ውስጥ ምን እናድርግ የሚለው ነው ትልቅ ዋጋ ሊሰጠው የሚገባ ቁም ነገር ነው፡፡በዚህ ጊዜ የመጽናናት አምላክ እንደ ሀሳቡ ከነገሩ ውስጥ እስኪያወጣን ድረስ ሙሉ በሙሉ የጸሎት ክተት ማወጅ አለብን ብዬ አምናለሁ፡፡እኔም የማደርገው እንደዚያ ነው፡፡በዚህ ጊዜ ጠንከር ያሉ ጸሎቶችን ለረጅም ሰአታት መጸለይ እጅግ ይጠቅመናል፡፡ለምን ቢባል በስጋችን እና በነፍስ ትግል ፈተናውን መቋቋም ስለማንችል ነው፡፡ለእኛ የሚያስፈልገን የእግዚአብሔር ጸጋ ነው፡፡የእግዚአብሔር ጸጋ ደግሞ በችግር ውስጥ ተከበንም ቢሆን  ቅንጣት ሳይሰማን ደግፎ ሊያቆመን ይችላል፡፡ክርስትናን ልዩ የሚያደርገውም የእግዚአብሔር ጸጋ ነው፡፡ለዚህ ነው ማቴ 11፡28 ‹‹እናንተ ሸክማችሁ የከበደ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ›› የሚለው፡፡እዚህ ቃል ውስጥ ያለው በረከት ታላቅ ነው፡፡በትንሹም ቢሆን ቀምሸዋለሁና እጅግ ደጋግሜ የማነሳውና የምወደው ቃል ነው፡፡አዎ ማሳረፍ ብቻ ሳይሆን ይገላግል፡፡ስለዚህ በእራስ ከመታገል እና ሰዋዊ መፍትሔዎችን በመዘየድ የእረፍት ዘመናችንን ከማርዘም በልዑሉ መጠጊያ ውስጥ መጥተን እንረፍ፤ሁለንተናችንንም ለእርሱ እንስጥ!


Friday, November 22, 2013

ውስጥን የሚለውጥ መንፈሳዊ እርምጃ



ውስጥን የሚለውጥ መንፈሳዊ እርምጃ

በህይወታችን እውነተኛ መንፈሳዊ ለውጥ እንዲመጣ ካስፈለገ ከምር መወሰን ይኖርብናል፡፡ብዙ ጊዜ ውጫዊ ነገሮች በመቀየራቸው ብቻ እውነተኛ መንፈሳዊ እድገት ላይ ያለን እየመሰለን ልንታለል እንችላለን፡፡እንደ ያእቆብ ማንንም እያታለልንና እያስመሰልን ዘመናችንን ልንጨርስም እንችል ይሆናል፡፡የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ሀሳብ ግን ውስጣችን በትክክል ተለውጦ እና እርሱን አንግሶ ከዚህ በሚመነጭ ፍሬ እርሱን በዙሪያችን አስከብረን እንድናልፍ ነው፡፡ለዚህ አይነት ውጤት የጨከነ ማንነት እና ሁለንተናችንን በጸጋው ዙፋን ፊት መጣል ይኖርብናል፡፡እንደዚያ ስናደርግ ብቻ ነው እውነተኛ ፍሬን በህይወታችን ማየት የምንችለው፡፡
ከላይ ለተጠቀሰው የለውጥ እርምጃ እንደ ሞዴል የሚሆነን ዘፍ 32፡22-32 ላይ ያለው ያእቆብ በህይወቱ የወሰደው እርምጃ እና ውጤቱ ነው፡፡ለዚህ ክፍል ዳራ የሚሰጠን በዘፍጥረት መጽሀፍ የተለያዩ ክፍሎች ያእቆብ ያሳለፋቸው ውጣ ውረዶች ናቸው፡፡በነዚያ የህይወት ውጣ ውረዶቹ ፡-

  • ያእቆብ አታላይ ነበር

  • ያእቆብ ከማናኛውም አይነት ሁኔታ ላይ ማትረፍ የሚወድ ራስ ወዳድ ሰው ነበረ

  • ያእቆብ አስቸጋሪ ነገሮችን ከመጋፈጥ ይልቅ ይሸሽ ስለነበር እውነተኛ ሕይወት አልነበረውም

  • ያእቆብ በራሱ በመደገፍ ማንኛውንም ጉዳይ በእራሱ የመፍታት አካሄድ ነበረው

  • በመጨረሻም ያእቆብ በምድራዊ ሀብት ደረጃ ባለጸጋ ሆኗል ነገር ግን ያልተፈቱ ችግሮች ነበሩት

በዚህ ክፍል ያእቆብ ወደ እናት አባቱ ምድር ለመመለስ ጉዞ እያደረገ ነው፡፡ከፊት ለፊቱ ኤሳው ወንድሙ እንደ ትልቅ ጋሬጣ በመንገዱ ላይ አለ፡፡ይህንንም ጋሬጣ እንዴት እንደሚያልፍ ጭንቅ ስለሆነበት በዘፍጥረት ምእራፍ 32 ላይ አንዴ ይጸልያል፣አንዴ በእጅ መንሻ ለማምለጥ ይዘይዳል፣አብረውት ያሉትን ባሪዎቹንና ንብረቶቹን ለሁለት ከፍሎ ይህንን አስቸጋሪ ሁኔታ ለማለፍ የሚችለውን ያህል መፍትሄ እያበጀ ነው ያለው፡፡ግን ይህ ሁሉ ዝየዳ መጨረሻ ላይ እንደማይጠቅመው ከተረዳ በኋላ አስደናቂ እርምጃዎችን ማድረግ ጀመረ፡-

  • አብረውት ያሉትን ሁሉ  ከፊት አስቀድሞ የያቦቅን ወንዝ አሻግሮአቸው ለብቻው ቀረ፡፡ያቦቅ ማለት እራስን ባዶ ማድረግ ማለት ነው-በእንግሊዝኛው በቀጥታ ሲተረጎም እንዲህ ነው፡-‘emptying’

  • ካንድ ሰውም ጋር  እስከ ንጋት ይታገል ነበር፡፡ብዙ የመጽሀፍ ቅዱስ አዋቂዎች ይህ ሰው ኢየሱስ ነው ይላሉ

  • ሊነጋ አቀላልቶአልና ልቀቀኝ ሲለው ያእቆብ “ካልባረክኸኝ አልለቅህም ”አለ-እጅግ በህይወታችን የሚያስፈልገን ድንቅ ውሳኔ እና ጸሎት

  • ለመጀመሪያ ጊዜ እውነተኛ ማንነቱን ተናገረ፡፡ሰውየው  ስምህ ማን ነህ ሲለው ያእቆብ ነኝ አለ ያእቆብ ማለት አታላይ ማለት ነው-እውነተኛ ለውጥ ፈላጊም እንደሆነ አስመሰከረ

ይህ ያእቆብ የታገለው ትግል ኢየሱስ በጌተሰማኒ ከጸለየው እና እራሱ ለሀጥያት መስዋእት አድርጎ ለመስጠት ካማጠበት እና ከቃተተበት የጸሎት ትግል ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው የመጽሀፍ ቅዱስ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡ከዚህም ምጥና መስዋእት በኋላ ያፈራውን ፍሬ ኢሳ 53፡11 እንዲህ ይገልጸዋል፡-‹ነፍሱን ስለ ሀጢያት መስዋእት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል እድሜውም ይረዝማል የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል፡፡ከነፍሱ ድካም ብርሀን ያያል ደስም ይለዋል…..›› 

ያእቆብ ከዚህም መንፈሳዊ ትግል የተነሳ ስሙ ተለወጠ፡፡እስራኤል ማለት “ከእግዚአብሔር ታግሎ ያሸነፈ” ማለት ሲሆን በእንግሊዝኛው እንዲህ ይተረጎማል፡- "Triumphant with God" ወይም “who prevails with God”ከዚያ አስደናቂ ትግል በኋላ ሲመሰክርም “እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየሁት ሰውነቴም ድና ቀረች”ብሎ ውጤቱን ተናገረ፡፡ምእራፍ 33 ላይ እንደምናየው ከኤሳውም ጋር በሰላም ነው ተሳስመው የተተላለፉት-ከእግዚአብሔር ጋር ስንስማማ ጠላቶቻችን እንኳ ከእኛ ጋር እንዲስማሙ ማድረግ ይችላልና ነው፡፡

ያእቆብ የወሰዳቸው እርምጃዎች እግዚአብሔርን በህይወቱ ፊት ለፊት እንዲያይ አድርገውታል፡፡በእኛም ህይወት እንዲህ አይነት ጊዜዎች እንዳይኖሩን እራሳችንን መከልከል የጠለቀ ግንኙነት እንዳይኖረን ያደርጋል፡፡ያለ እውነተኛ መንፈሳዊ ትግልም ለውጥ የለም፡፡በእርሱ ፊት እራሳችንን ባዶ የምናደርግበት ፣በፊቱ ወድቀን እውነተኛ መዳሰስ እንዲመጣ ፊቱን ከምር የምንፈልግባቸው ጊዜያት ያስፈልጉናል-አንዴ ሳይሆን በርከት ያሉ ጊዜያት!

በዚህ ዙሪያ የነበረኝን ልምድ ቢጠቅም ላካፍል፡-
አንደኛ፡-ወደ ጌታ ከመምጣቴ በፊት በዛው ህይወት እንዳልቀጥል ህይወቴ እንደ አይን ጠፍቷል ወደ ጌታ እንዳልመጣ እና እንዳላርፍ ብዙ የታሰርኩባቸው ነገሮች ጠላልፈውኛል፡፡በዚህ አይነት ሁኔታ ሆኜ እየዋዠቅሁ ለመወሰን ያሳለፍኩት ወደ ስድስት ሰአት የሚጠጋ የትግል ወቅት ትዝ ይለኛል፡፡ልክ ስወስን እና እራሴን በጌታ ላይ ስጥል ክፍሉ በብርሀን ተሞላ፣የደስታ መንፈስ አጥለቀለቀኝ ብዙ ሳልቆይ ትልቅ ለውጥ ወደ ህይወቴ መጣ

ሁለተኛ፡-ሀይለኛ የቀለም እልህ ነበረኝ፡፡እንዳሰብኩት ነገሮች ሳይሰምሩ ዘመኔ ሄደ በማለትም የውስጥ ሀዘን ነበረኝ፡፡ወደ አሜሪካ ከመጣሁ በኋላ በህክምና ሙያ ለመቀጠል የህክምና ቦርድ ፈተና መውሰድ ነበረብኝና የመጀመሪያ ፈተናዬን በጥሩ ውጤት አልፌ ለሁለተኛው ፈተና እየተዘጋጀሁ ነበር ያለሁት፡፡ጌታ ግን እየሄድኩበት ያለው መንገድ እርሱ ያሰበው መንገድ እንዳልሆነ እና እርሱን እንዳገለግለው በተለያዩ መንገዶች ሲናገረኝ ኖሯል፡፡አንድ የመጨረሻ ሌሊት ግን ማጥናት እና ማንበብ በማልችልበት ሁኔታ የጸሎት መንፈስ ወደቀብኝ፡፡ንባቡን ወደ ጎን አድርጌ ሌሊቱን ሙሉ በሚገርም ሁኔታ ስጸልይና ስቃትት እና ከእራሴ ጋር ስታገል አድሬ ወደ ንጋቱ ላይ ግልጽ በሆነልኝ መንገድ ሙሉ በሙሉ መንፈሳዊ አገልግሎት ላይ ብቻ ዘመኔን እንድጨርስ እንደሚፈልግ ገብቶኝ ልክ ከእርሱ ጋር ስስማማ እንዴት እንደተነፈስኩ አትጠይቁኝ፡፡ያንን ቀን እግዚአብሔርን ፊት ለፊት የአየሁት ያህል ነበር የተሰማኝ፡፡ልዩ ጊዜ ነበር፡፡አሁን የምኖርለት አላማ ገብቶኝና ሁለመናዬን አስረክቤ በምሪቱ ውስጥ ለመሆን ሌት ተቀን እየተጋሁ እገኛለሁ፡፡በዛ ቀን ውስጤ የገባው ብርሀንና የጌታ ድምጽ በማይረሳ መልኩ ልቤ ላይ ታትመው ቀርተዋል፡፡

ሁላችንም የምንታገልባቸው ብዙ ነገሮች አሉን፡፡ያብዛኞቻችን ህይወት ከያእቆብ ጋር በሚገባ ይመሳሰላል፡፡የያእቆብ ልቡ፣አካሄዱ እና ስሙ እንደተለወጠ ጌታ ሊለውጠንና የፍሬ ሰዎች ሊያደርገን ይፈልጋል፡፡ግን አንድ ነገር ከእኛ ይፈልጋል ብዬ አምናለሁ-በበቂ ሁኔታ መገኘታችንን!!

ያእቆብ ከእግዚአብሔር ጋር ታግሎ አሸነፈ የሚለው ሀሳብ እግዚአብሔርን ማሸነፉ ሳይሆን ለእግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ መሰጠቱ እና መገዛቱ ነው እንደ ማሸነፍ የተቆጠረለት፡፡እውነተኛ መንፈሳዊ ለውጥን ፈለገ!እግዚአብሔር በህይወታችን የበላይ መሆኑም የአሸናፊነታችን ሁሉ ምንጭ ነውና ያእቆብ ከሰውም ከእግዚአብሔርም ጋር ታግለህ አሸነፍክ ተባለ፡፡የወሰዳቸው እርምጃዎቹ እና ያሳለፈው ያ ድንቅ የሌሊት ትግል እግዚአብሔርን ፊት ለፊት እንዲያይ አደረገው፡፡

እኛም በእንደዚህ አይነት ውሳኔና ረሀብ በፊቱ ብንሆን እና ሳናቅማማ እራሳችንን በፊቱ ብንጥል እናየውና ተለውጠን እንቀራለን ብዬ አምናለሁ፡፡አለበለዚያ ግን ህይወት የሌለን፣ሀይማኖተኛ፣ግብዝ፣አስመሳይ እና ከእውነት የራቅን ነው የምንቀረው፡፡በላይ በተጠቀሱት መንፈሳዊ ሂደቶች ውስጥ ስናልፍ ግን እምነታችን ይጠነክራል ያድጋል ብሎም ግትረኝነት እልህ ከህይወታችን ይወገዳል፤እውነተኛ የልብ መሰበርና ትህትናም መገለጫችን ይሆናል፡፡

አሳዛኙ ነገር በህይወታችን ብዙ ጊዜ ዋናው ፍላጎታችን “ኤሳው”እንዲለወጥ ነው የምንፈልገው ቢሆንም አንዱ “ኤሳው” ከህይወታችን ቢወገድ ሌላው ይመጣል በምድር እስካለን ድረስ፡፡ነገር ግን እግዚአብሔር በማንኛውም የህይወት ውጣ ውረድ ነጥሮ የሚወጣ ማንነትን ሊሰጠን ስለሚፈልግ እኛን ከውስጥ መለወጥ ነው የሚፈልገው፡፡ለዚህ ደግሞ የእኛን ፈቃደኝነት ይፈልጋል፡፡ስለዚህ እሺ እንበለው፡፡እጆህ ይስሩኝ ያበጃጁኝ እንበለው መስራትና መለወጥ ያውቅበታልና!‹‹እንዳላሸነፈውም ባየ ጊዜ የጭኑን ሹልዳ ነካው››እንደሚል ሰባብሮ የራሱ ሊያደርገን እና ትሁት አድርጎ የሚጠቅም የክብር እቃ ሊያደርገን ይመኛልና እንፍቀድለት፡፡

በመጨረሻም እጅግ ለጸሎት ህይወቴ መሰረት የሆነኝ ሀሳብ ላይ ልናገር እና ጽሁፌን ልጨርስ፡፡ያእቆብ ካደረጋቸው እርምጃዎች እጅግ የሚያስደስተኝ “ያእቆብም ለብቻው ቀረ”የሚለው ሀሳብ ነው፡፡በዛች አመሻሽ ቀን በሀሳብ እና በጉልበት ሊረዱት የሚችሉ ሰዎችን ሁሉ አሻግሮ ለብቻው ሆነ፡፡እውነተኛ ውስጣዊ ለውጥን ፈልጎአልና ውጫዊ ከበባን አስወገደ፡፡አዎ በዚህ ግርግር በበዛበት እና የሰውን ቀልብ በተለያየ መልኩ የሚስቡ ነገሮች በበዙበት አለም ብቻን በመሆን ለጌታ መገኘት የሚቻልባቸው አጋጣሚዎች የጠበቡ ቢሆንም እንደ አጋጣሚ እንደዚህ አይነት ጊዜዎች ሲገኙ መታለፍ የለባቸውም ባይ ነኝ፡፡በነዚህ ጊዜዎች የምናሳልፋቸው በርከት ያሉ ሰኣታት ወደ ፊት የሚኖረን ህይወትና አገልግሎት በእጅጉ ይወስኑታልና ያለመሰሰት እራሳችንን እግሩ ስር እንጣል፡፡እግዚአብሔር ሆይ እንደ ያእቆብ በፊትህ የከበረን ጊዜን ስጠን!!

Friday, November 8, 2013

በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ



በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ

ይህ ጽሁፍ ዮሀ 15፡1-11 ላይ የሚያተኩር ሲሆን ኢየሱስ በዚህ ምእራፍ ላይ ሊገባን በሚችል ምሳሌያዊ ቋንቋ በመጠቀም ከእርሱ ጋር የምናደርገው የጠበቀ ህብረት እና ግንኙነት በክርስትና ህይወታችን ወሳኝ እንደሆነ ያሳየናል፡፡ዮሀ 15፡4 ላይ ‹‹በእኔ ብትኖሩ እኔም በእናንተ››የሚል ድንቅ መርህ እናገኛለን፡፡አያይዞም እዛው ቁጥር 4 ላይ ‹‹ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም››በማለት ከእርሱ ጋር ያለን ህብረት እና ግንኙነት ለፍሬ ማፍራታችንም ወሳኝ እንደሆነም ያስገነዝበናል፡፡አዎ በህይወታችን ትልቅ ቦታ ሊይዝና እንቅስቃሴዎቻችንን ሁሉ ሊቆጣጠር የሚገባው ‹‹በእኔ ብትኖሩ እኔም በእናንተ›› የሚለው የፍቅር መርህ ነው፡፡ቁጥር 7 ላይ እንደገና አስረግጦ እንዲህ ይላል፡-‹‹በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል››ስለዚህ አንድ የማያሻማን ነገር የስኬታችን ቁልፍ ሚስጥር ያለው በእርሱ ህልውና ውስጥ መኖራችን ሲሆን የሚጨበጥ ፍሬ ያለው ክርስትና ለመኖር የሚከተሉት ሁለት የፍቅር መርሆዎች በሚገባ መተግበር አለባቸው፡-

  • በእርሱ መኖር

  • ቃሎቹ በእኛ ውስጥ መኖር

‹‹በእኔ ብትኖሩ››የሚለው ሀሳብ በዳግመኛ ልደት መንፈስ ከሆነው ቃል በመወለድ ይጀምራል፡፡ይህ አስደናቂ መንፈሳዊ ለውጥ በውስጣችን ከተከናወነ በኋላ ህልውናው ውስጥ እንድንኖር የሚያደርገን ከቃሉ ጋር የምናደርገው ህብረት እና ቀጣይነት ያለው ጸሎት ነው፡፡በትጋት እየጸለይን በፊቱ በቂ ጊዜን ስናሳልፍ እያወቅነውና ከእርሱ ጋር እየተጣበቅን እና ጸጋው በሕይወታችን እየበዛልን ይመጣል፡፡ከዚህም የተነሳ ከአለም እየተለየንና መንፈሱን ከሚያሳዝኑ ነገሮች እየራቅን ስለምንመጣ ህልውናው በሚገባ እየታወቀን እና አብሮነቱን እየተሰማን መዋል ማደር እንጀምራለን፡፡ይህ በረከት ወደ እኛ እንዲመጣ የሰው ሀላፊነት መኖሩ ምንም አያጠያይቅም፡፡ማለትም አዘውትረን በጸጋው ዙፋን ስር መውደቅና ፊቱን መፈለግ ይኖርብናል፡፡


‹‹ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ››የሚለውን ሀሳብ እንደዚህ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡በተለያየ መንገድ ማለትም በስብከት፣መጽሀፍ ቅዱስን በማጥናትና የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸውን መጽሀፍት በማንበብ ወደ ውስጣችን የሚገቡት የእግዚአብሔር ቃሎች መጀመሪያ በአእምሮአችን በኩል ነው ወደ መንፈሳችን ወይም ወደ ውስጥ ማንነታችን የሚገቡት፡፡በአእምሮአችን የተቀበልነው ቃል ወደ ውስጥ ማለትም ወደ መንፈሳችን የሚወርደውም ቃሉን ስንረዳውና ስናስተውለው ነው፡፡ያስተዋልነውና የተረዳነው በብዙ ትጋት ከውስጣችን ጋር ያዋሀድነው ቃል ነው ውስጣችን ሊቆይና ሊኖር  የሚችለው እንደዚህ እንደሚል፡-‹‹በማያስተውል ላይ ሌባው ይመጣል››፡፡ ያስተዋልነውን ቃል ሌባው በፍጹም ሊነጥቀን አይችልም፡፡ስለዚህ እዚህ ጋ ጥሩ ዋጋ መክፈል ይኖርብናል፡፡እብራውያን ምእራፍ ሶስት ላይም ‹‹የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሀደ አልጠቀማቸውም››የሚል ገራሚ ሀሳብ እናገኛለን፡፡አእምሮአችን ውስጥ የሚዘሩት ቃሎች ወደ ውስጣችን ዘልቀው እንዲዋሀዱ ብዙ ማሰላሰል፤ብዙ ጥናት እና በህይወታችንም በተግባር መፈጸም ይገባናል፡፡እንዲህ ስናደርግ ነው ቃሉ በእኛ ውስጥ የሚኖረው፡፡በተለይ ያነበብነውን ቃል በተግባር ማዋል ውስጣችን በማይረሳ መልኩ እንዲታተም ስለሚያደርገው በልባችን ላይ በማይፋቅ መልኩ ይጻፋል፡፡


ቁጥር 5 ላይ እንደገና አስረግጦ ያለ እርሱ ምንም አይነት እመርታ እና ስኬት እንነደማይኖረን እንዲህ በማለት ይነግረናል፡-‹‹ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል››፡፡‹‹ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም›› የሚለው በህይወታችን ሬማ ካልሆነ እና ካልበራልን ያለ እርሱ ብዙ ልንኳትን እንችላለን፡፡እግዚአብሔር በህይወቴ ይህንን ቃል በሚገባ እስካየውና እስክታዘዘው ድረስ ጉልበቴን ገንዘቤን እና ጊዜዬን ጨርሻለሁ፡፡አሁን ጌታ ይመስገን ጌታ በጥሩ ሁኔታ መልሶኛልና ያለ እርሱ ምንም ማድረግ እንደማልችል ገብቶኛል፡፡በእንቅስቃሴዎቼ ሁሉ እርሱን ለማስቀደም ወስኛለሁ፡፡
በነገራችን ላይ በእነዚህ በላይ በተጠቀሱት የቃል መርሆዎች ህይወታችን ሲለካ ያለነው እታች እንደሆነ በመንፈሴ አስተውላለሁ፡፡ለምን ቢባል፡-

  • በቂ የሆነ የጸሎት ህብረት የለንም

  • ቃሉን በቂ ጊዜ ሰጥተን አናነብም አናጠናውም አናሰላስለውም(ጊዜያችንን የሚቀሙ ብዙ ነገሮች አሉ)

  • ቃሉን በተግባር ደረጃ አንለማመደውም

ከዚህ የተነሳ በአካባቢያችንና በህብረተሰባችን ላይ ተጽእኖ የሚያመጣ ፍሬ አይታይብንም፡፡የሰማዩ አባታችን በህይወታችን እንዲከብር እና በእኛ ህይወት እርሱን እንዲያዩና ወደ እርሱ ዘወር እንዲሉ ካስፈለገ ከላይ ወደ ተጠቀሱት ትእዛዞችና መርሆዎች በሚገባ መመለስ ይናርብናል፡፡አለበለዚያ ዝም ብለን ልናስመስል እንችል ይሆናል እንጂ እነዚህን መሰረታዊ የሆኑ ነገሮችን ሳንተገብር በፍጹም ፍሬ የሚባል ነገር እንደማይኖረን ልናውቅ ይገባል፡፡

ስለዚህ ሁለቱ ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች ሲሟሉ (በእርሱ ስንኖር እና ቃሎቹ በእኛ ውስጥ ሲኖሩ) ፡-

  • አንድ ክርስትያን ከግንዱ ጋር ተጣበቀ ማለት ይቻላል

  • እውነተኛ ፍሬም የማፍራት ችሎታ ይኖረዋል

ይህንን ፍሬ በሶስት ከፍለን ልናየው እንችላለን ምንም እንኳ አንድ የሚያመሳስል ግብ ቢኖራቸውም (ክርስቶስን ማሳየት)

  • የመንፈስ ፍሬዎች (ገላ 5፡22 እንደሚል፡-‹‹የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው››)

  • በበጎ ስራ የምናፈራቸው ፍሬዎች(ቆላ 1፡10-11 እንደሚል ‹‹በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ››)-ማህበራዊ የሆኑ ስራዎችን ይወክላል

  • የወንጌል ስራ ፍሬዎች


ወረድ ብሎም ‹‹በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ ››የሚለውን የፍቅር ትእዛዝ ስንተገብር ስለሚገጥመን በረከት እንዲህ በማለት ይገልጻል፡-
1.የምትወዱትን ለምኑ ይሆንላችኋል(ቁጥር 7 ላይ)
2.ደስታችሁም ሙሉ ይሆናል(ቁጥር 11 ላይ)

እነዚህን ሁለት በረከቶች ሳስብ ይገርመኛል፡፡ምን አይነት መታደል ነው፤የሚደንቅ ህይወት!!ወደ እንደዚህ አይነት መንፈሳዊ ህይወትና ልምምድ ውስጥ እግዚአብሔር ሊከተን ይፈልጋል ግን እንደሚገባኝ መጀመሪያ ግን ለእርሱ በሚገባ መገኘት ያስፈልገናል ብዬ አምናለሁ፡፡ስለዚህ ይህንን  መንፈሳዊ በረከት በሕይወታችን ለማየት ሳንታክት በትጋት ፊቱን እንፈልግ !!!