Friday, October 25, 2013

በፊቴ ገበታን አዘጋጀህ



በፊቴ ገበታን አዘጋጀህ

አይናችን ተከፍቶ ስላልታየን ነው እንጂ እረኛችን በፊታችን ድል ያለ ግብዣን አዘጋጅቶልናል፡፡መዝ 23፡5 ላይ ‹‹በፊቴ ገበታን አዘጋጀልኝ በጠላቶቼ ፊት ለፊት ራሴን በዘይት ቀባህ ጽዋዬ የተረፈ ነው፡፡››የሚል ዘወትር የሚገርመኝ እና የሚያጓጓኝ ቃል እናገኛለን፡፡ከዚህ ቃል አንድ የምረዳው ነገር በሚገባ ይህንን ግብዣ እንዳናስተውልና የእምነት እጃችንን ዘርግተን በረከታችንን እንዳናፍስ የጠላት አዚምና ከበባ እንዳለ ነው፡፡

ዳዊት መንፈሳዊ አይኑ የተከፈተ ሰው ስለነበር በዚህ ቃል መሰረት አራት ነገሮችን በመንፈሳዊ አይኖቹ እንዳየ ጽፎልናል፡፡እነርሱም፡-

  • በፊቱ መንፈሳዊ ገበታ መዘጋጀቱ

  • ጠላት እንደ ከበበው

  • የመንፈስ ቅዱስ ቅባት እላዩ እንዳለ

  • ጽዋው ሞልቶ መትረፍረፉ(ለሌሎች የተረፈ በረከት እላዩ ላይ እንዳለ)


ዳዊት በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን ሀሳብ በተሳካ ሁኔታ አገልግሎ ያንቀላፋው በፊቱ የተዘጋጀለትን ማእድ በሚገባ ማየቱና ሳያቋርጥ መውሰዱ ነው፡፡ይሄ የእንዳንዳችን ሀላፊነት ሲሆን ጥሩ መረዳት እና ዲሲፕሊን የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡መዝ 85፡13 እና 16 ላይ ‹‹ሕዝቤ ሰምቶኝ ቢሆን እስራኤልም በመንገዴ ሄደው ቢሆን ከስንዴ ስብ ባበላቸው ነበር ከአለቱም ማር ባጠገባቸው ነበር››የሚል ከመዝ 23፡5 ጋር ተመሳሳይ ሀሳብ ያለው ቃል እናገኛለን፡፡እኔ “ከስንዴ ስብ ባበላቸው ነበር ከአለቱም ማር ባጠገባቸው ነበር” የሚለውን  ሀሳብ ባነበብሁት ቁጥር ጉጉቴን ይጨምረዋል፡፡ይህ ቃል የእግዚብሔርን ድምጽ መስማታችንና እና ምሪቱን መከተላችን ያለውን መንፈሳዊ በረከት ነው የሚያሳየን፡፡በሁለቱም በተጠቀሱ ቃሎች ላይ የእግዚአብሔርን መልካም እረኝነት እና የእኛ ለምሪቱ መሰጠት የሚያመጣውን በረከት ነው የምናየው፡፡

አዎ እርሱ ቸር ነው ገበታን አዘጋጅቶልናል፡፡ኢሳ 25፡6 ላይም ‹‹የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ለህዝብ ሁሉ በዚህ ተራራ ላይ ታላቅ የሰባ ግብዣ ያረጀ የወይን ጠጅ ቅልጥም የሞላባቸው የሰቡ ነገሮች የጥሩና ያረጀ የወይን ግብዣ ያደርጋል››የሚል ክርስቶስ ከመምጣቱ ከብዙ ዘመናት በፊት የተተነበየ ትንቢት የምናገኝ ሲሆን ይህም የትንቢት ቃል በክርስቶስ መሞት እና ትንሳኤ በከፊል የተፈጸመ እንደሆነ የመጽሀፍ ቅዱስ አዋቂዎች ይስማማሉ፡፡በዚህ ቃል ላይ ያሉ አገላለጾች እጅግ የሚያጓጉ ሲሆኑ ከእግዚአብሔር መንፈስ ጋር በሚኖረን የጠለቀ ህብረት ስለምናገኘው ድል ያለ በረከት የሚናገር የተስፋ ቃል ነው፡፡እንዴት ታዲያ ይህን የመሰለ ድንቅ ተስፋ ሳለን ዳር ዳር እያልን ዘመናችን እንደምንፈጅ አይገባኝም፡፡ኢሳ 55፡2 ላይም ‹‹አድምጡኝ በረከትንም ብሉ ሰውነታችሁም በጮማ ደስ ይበለው፡፡ጆሮአችሁን አዘንብሉ ወደ እኔ ቅረቡ ስሙ ሰውነታችሁም በሕይወት ትኖራለች ››በማለት ግብዣውንና የግብዣውን ውጤት ያሳየናል፡፡

ምንም እንኳን በተለያዩ ብዙ የመጽሀፍ ቅዱስ ክፍሎች ይህንን ድል ያለ ግብዣ እስክንጠግብ እንድንበላ ተደጋግሞ ብንጋበዝም ምላሻችን አሳዛኝ እየሆን ነው ያለው፡፡መዝ 106፡15 እንደሚናገር የለመንነውን (ረብ እና ዘለቄታ የሌላቸውን ነገሮች) እየሰጠን ለነፍሳችንን ግን ክሳት እየላከ ያለ ይመስለኛል፡፡በዚህ አካሄዳችን ምን ያህል ነፍሱ እንደምታዝን በጭላንጭልም ቢሆን እገምታለሁ፡፡የማያጠግቡ፣የማይረቡ እና ወንዝ የማያሻግሩ ነገሮች ልባችንን ቀሙን፡፡ጉልበታችንን እንግዶች በሉት፡፡ግብዣው ላይ በሚገባ መገኘት ደከምን፡፡አቃተን………..

በመፍትሄ ዙሪያ ጥቂት ልበልና ጽሁፌን ልቋጭ፡፡ማቴ 5፡6 ላይ ‹‹ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብጹአን ናቸው ይጠግባሉና›› የሚለው የጌታችን የተስፋ ቃል  የተዘጋጀውን ግብዣ ለማፈስ ቁልፍ ቃል ነው፡፡‹‹ረሀብና ጥማት›› ለመንፈሳዊ ለውጥና እድገት ትልቅ ሚናን ይጫወታሉ፡፡እነዚህ ሁለቱ ሞተሮች ከሌሉንና ረብ በሌላቸው ነገሮች አእምሮአችንን እና ውስጣችንን የምንሞላ ከሆነ ለመንፈሳዊ ነገር ያለን ጉገት ስለሚደበዝዝ እና ስለሚጠፋ ከዚህ መለኮታዊ ግብዣ ተቋዳሽ እና ባለ እድል መሆን ያቅተናል፡፡እውነተኛ መንፈሳዊ ለውጥን የምንፈልግ ከሆነና እረፍትና በረከትን የምንፈልግ ከሆነ በመሰረታዊ ደረጃ ይህ ረሀብና ጥማት ወደ ህይወታችን እንዲመጣ ትጉህ መሆን ያስፈልገናል፤የትጉ ነፍስ ትጠግባለች ይላልና፡፡ስለዚህ ይህ ረሀብና ጥማት እንዲመጣ የሚከተሉትን ነገሮች እናድርግ፡-


  • የክብርን ጌታ ያለማሰለስ እንሻ

  • ረዘም ያሉ የጾም ጊዜዎች ይኑሩን

  • ቢሰማንም ባይሰማንም የጸሎት ዲሲፕሊን ይኑረን

  • ከቃሉ ጋር ጠንከር ያለ ህብረት ይኑረን(እናጥናው እናሰላስለው)

  • አዚምንና ድንዛዜን (የክፉን ስራና ተጽእኖ) እየተቃወምን እንጸልይ

  • ከጌታ ጋር ያለንን ህብረት የሚያደበዝዙ ነገሮችን በመጨከን ከሕይወታችን እናባር


ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራዊ እርምጃዎች ሳናሰልስ ረዘም ላሉ ጊዜዎች ስናደርጋቸው በውጤት ሂደት የሚከተለው ኡደት ውስጥ እራሳችንን ልናገኝ እንደምችል (ቀምሼ አይቼዋለሁና) በድፍረት እናገራለሁ፡-

እግዚአብሔርን በጽኑ መሻት-------›መንፈሳዊ ረሀብና ጥማት--------›የጠለቀ ጸሎት------›መንፈሳዊ መረዳት-----›የጨመረ መንፈሳዊ ረሀብና ጥማት----------›መንፈሳዊ በረከት-------›የጨመረ መንፈሳዊ ረሀብና ጥማት-----›የጨመረ መንፈሳዊ መረዳት-----›የጨመረ መንፈሳዊ በረከት ---------›ይቀጥላል(ማብቂያ የለውም)

ለማጠቃለል እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚደንቅ ግብዣ እንዳዘጋጀልን እጅግ ብዙ ማስረጃዎች አሉን፡፡ይህንን ግብዣ ዝም ብለን መካፈል አንችልም፡፡ቆላ 1፡12 ‹‹በቅዱሳን ርስት በብርሀን እንድንካፈል ያበቃንን›› እንደሚል ከዚህ በረከት የምንካፈለው በብርሀንና በብዙ መረዳት ነው፡፡ስለዚህ ከላይ ባለ ጥቅስ ላይ ‹‹ጆሮአችሁን አዘንብሉ ወደ እኔ ቅረቡ ስሙ ሰውነታችሁም በሕይወት ትኖራለች›› እንደሚል ወደ እርሱ ያለማሰለስ እንቅረብ!!



Sunday, October 20, 2013

የድብርት መድሀኒት(Medicine to depression)



                                                        የድብርት መድሀኒት

በአለማችን በተለይ በምእራቡ ምድር እንደምናየው ብዙ ሰዎች በተለያዩ የአእምሮ በሽታዎች ሲጠቁ እናያለን፡፡ዋነኛው የአእምሮ ችግርም ድብርት (depression) እንደሆነ በዚህ ዙሪያ ጥናት ያደረጉ ጠበብቶች ይስማማሉ፡፡የድብርት (depression) መንስኤው እንደቦታው እና እንደሰው አይነትና አኗኗር ይለያያል፡፡ሁሉንም የሚያመሳስላቸው ግን የችግሩ ስሜቶች እና ምልክቶች ናቸው፡፡ማለትም ሁሉም ሰዎች ላይ ደስታ ማጣት እና ሀዘን ይኖራል መጠኑ ቢለያይም፡፡ይህ ችግር ጌታ ኢየሱስን የማያውቁ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን እሱን በሚገባ የሚያውቁ ሰዎችን ላይ ሳይቀር ይስተዋላል፡፡አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ጊዜያዊ ጭንቀት እና ድብርት ማናችንም ላይ በተለያየ ምክንያት ሊመጣ ይችላል ነገር ግን እላያችን ላይ ቤቱን ሰርቶ እንዲረጋጋ እና መጫወቻ እንዲያደርገን መፍቀድ የለብንም፡፡


መጽሀፍ ቅዱስ ይህ ችግር ወደ ህይወታችን እንዳይመጣ ጥሩ መከላከላያ መድሀኒት ያለው ሲሆን ይህ ችግር ካገኘንም በኋላ ባስተማማኝ ሁኔታ የምንወጣበት መፍትሄም በውስጡ የያዘ ነው፡፡መጽሀፍ ቅዱስ ትክክለኛ እና የጠለቀ ህብረት ያለው ክርስትያን ዝቆ እና ቀድቶ የማይጨርሰው የደስታ ምንጭ እንዳለው እኔም በህይወቴ ስላየሁ በድፍረት እመሰክራለሁ፡፡


ዳዊት በእንደዚህ ነፍስን ግራ በሚያጋባ አጣብቂኝ እና ሀዘን ውስጥ ከማናችንም በላይ ያለፈ ሲሆን ችግሩንም መፍትሄውንና የመፍትሄውን ውጤት በመዝ 422-4 ላይ በሚደንቅ ሁኔታ ጽፎልናል፡፡ይህ ቃል አስገራሚ ሚስጥር ያለው ቃል ሲሆን በሚገባ በህይወታችን ከተገበርነው ድንቅ ህይወት ውስጥ እንደሚከተን አምናለሁ፡፡ይህንን ክፍል ወደ ጌታ ከመጣሁ በኋላ ከመቶ ጊዜ በላይ አንብቤዋለሁ፡፡አሁንም ደጋግሜ አነበዋለሁ፡፡እንዳውም በጸሎት ጊዜ ወደ እራሴ ህይወት ቀይሬ(by personalizing it) ሁሉ እጸልየዋለሁ፡፡ቃሉ እንዲህ ይነበባል፡-

 ‹‹አንተ አምላኬ ሀይሌም ለምን ትተወኛለህ?ጠላቶቼ ሲያስጨንቁኝ ለምን አዝኜ እመላለሳለሁ?ብርሀንና እውነትህን ላክ እነርሱም ይምሩኝ ወደ ቅድስህናህ ተራራ እና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ፡፡ወደ እግዚአብሔር መሰዊያ ጎልማስነቴንም ደስ ወዳሰኛት ወደ አምላኬ እገባለሁ››

·       የዳዊት ችግር-----የመተው/የመገፋት ስሜት ከዚህም የተነሳ የደረሰበት ጭንቀት እና ሀዘን
·       መፍትሄው--------የእግዚአብሔር ብርሀንና እውነት(ከአፉ የሚወጣው ቃል /ሬማ የሆነው የጊዜው ቃል)
·       የመፍትሄው ውጤት------ደስ መሰኘቱ፤‹‹ጎልማስነቴን ደስ ወዳሰኛት›› የሚለው ሀረግ ይህንን ያመለክታል

ዳዊት በእንደዚህ አይነት ሁኔታ የቆየበት ጊዜ ባይታወቅም ትንሽ እንደቆየ መገመት ይቻላል፡፡ይህንን የሚጠቁመን ቃል ደግሞ ‹‹ለምን አዝኜ እመላለሳለሁ››የሚለው ሀሳብ ነው፡፡እንደዚህ አይነት በደል ሀዘንና ጭንቀት የሚያደርሱበት ደግሞ ጠላቶቹ(አጋንንቶች-የሰው ጠላት የለንምና)እንደሆኑ ይናገራል፡፡ከዚያም መፍትሄውን እራሱ ያቀርባል ‹‹የእግዚአብሔር ብርሀንና እውነት››ናቸው በማለት፡፡በዚህ ዙሪያ የገጠምኩት ግጥም አለ፡-

                የቃሉ ሬማ
ሽንፈት ሲያልብኝ  መነሳት ሲከብደኝ
ሁኔታው ሲያቅራራ አለቀልህ ሲለኝ
ውስጤ እንዲህ ሲስማማ እያየ ጨለማ
ግራ ተጋብቼ ስወናበድ ድንገት
በክስ ሰነድ ብዛት
እንዲህ ባረግህ ኖሮ እንዲህ ይሆን ነበር
የሚል ምክንያታዊ ስሰማ ንግግር
እራሴ ለራሴ ቃላት ሲወራወር
ከጸጸት ስሜት ውስጥ ገፍትሮ የሚያወጣኝ
የቃሉ ሬማነው የሚገላግለኝ !

ዳዊት መፍትሄው የእግዚአብሔር መንፈስ(ሀይል ያለው ከአፉ የሚወጣው ቃል) እንደሆነ በሚገባ ያሳየናል፡፡ማለቴም በጸሎት መንፈስ ሆነን ፊቱን እየፈለግንእየቃተትንቃሉን እያሰላሰልን በሀይል(aggressively)ስንጸልይና በጽናት ስንጠብቀው ከተፍ ብሎ ያስደንቀናል፤ቀንበራችንን ይሰብረዋል፤ሀዘናችንንና ድብርታችንን ያስወግደዋል፡፡እናም ክፋት ወደሌለበት ‹‹ወደ ቅድስና ተራራው ወይም ወደ ማደሪያው(His presence)›› ይወስደናል፡፡በህልውናው ውስጥ ደግሞ ሰላም አለ፤ደስታ አለ፤እረፍት አለ፤መረጋጋት አለ ወዘተ፡፡ይህንን በረከት በህይወቴ ደጋግሜ ስላየሁኝ ህያው ምስክር ነኝ፡፡ክርስትናን ውብ የሚያደርገውም እርሱ ነው፡፡ስለዚህ በራሳችን መታገል አቁመን ሙሉ በሙሉ እራሳችንን ለእርሱ እንስጥ፤በጸጋው ዙፋን ፊት እንውደቅ!በመመለስና በማረፍ እንድናለንና በጸጥታና በመታመን(በፊቱ በመሆን)ሀይል ይሆንልናልና መጥተን በፊቱ ምንም ሳናቅማማ እንረፍ!


ወደ ጌታ ያልመጣችሁ ሰዎች የዲያቢሎስን ሽንገላ ንቃችሁና ንዝነዛውን ወደ ኋላ ጥላችሁ ሸክማችሁን በኢየሱስ እግር ለመጣል ብትወስኑ የሚገርም ህይወት ውስጥ እራሳችሁን እንደምታገኙት በሙሉ እምነት እናገራለሁ፡፡የዛሬ አስራ አምስት አመት ገደማ እኔም የዲያቢሎስን ሽንገላ አሽቀንጥሬ ነው ከብዙ ሀዘንና መከራ ወጥቼ በነጻነት መኖር ምን እንደሆነ የቀመስኩትና መጥታችሁ የእግዚአብሔርን እረፍትና ቸርነት ምን እንደሚመስል ቅመሱ!!