እግዚአብሔርን ማወቅ
እግዚአብሔርን ለማወቅ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ወሳኝ ነው፡፡ያዕቆብ 4፡7 ላይ ‹‹ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም
ይቀርባል›› የሚል ቀላል አባባል የሚመስል ግን የጠለቀ እውነት ያለውን ቃል እናገኛለን፡፡በዚህ ቃል ላይ የእኛ የልብ ተነሳሽነት
እና የመቅረብ ፈቃደኝነት እንደሚቀድምም እናስተውላለን፡፡አዎ ወደ እግዚአብሔር በቀረብን ቁጥር ከእርሱ በምናገኘው ብርሀን መንፈሳዊውን
አለም እየተረዳንና የእግዚአብሔር መለኮታዊ ማንነት እየተገለጠልንና ታላቅነቱ፣ገናናነቱ፣ሀያልነቱ እና ጥበቡ እየበራልን የምንድነቅበትና
የምንገረምበት ህይወት ውስጥ እራሳችንን እናገኘዋለን፡፡ማለትም የማወቃችንን መጠን የመቅረባችንን ልክ ይወስነዋል፡፡
እግዚአብሔርን ማወቅ ስል ዝም ብሎ ስለ ቀለም እውቀት መናገሬ ሳይሆን በጸሎትና ከቃሉ ጋር በሚደረግ ህብረት እና ግንኙነት
የሚገኝ እውቀትን (intimate relational knowledge) መናገሬ ነው፡፡ይህ አይነት መረዳት ብዙ ፊቱን በመፈለግና በቂ
ጊዜ በመውሰድ የምናገኘው ነው፡፡ኤፌ 1፡17 ላይ ‹‹የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ክርስቶስን በማወቅ የጥበብንና
የመገለጥን መንፈስን እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ››በማለት ሀዋርያው ጳውሎስ የሚጸልየው ጸሎት አለ፡፡ማለትም የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ
የምናገኘው “ክርስቶስን በማወቅ” እንደሆነ ነው የሚነግረን፡፡“ክርስቶስን በማወቅ”የሚለው ቃል የጠለቀ ግንኙነትን (deeper
intimacy) ነው የሚጠቁመን፡፡“ክርስቶስን በማወቅ” የጥበብና የመገለጥን መንፈስ ሲበዛልን ደግሞ የልባችን አይኖች እንደሚበሩና
ሌሎች መረዳቶች እንደሚከተሉ ያስረዳናል፡፡ስለዚህ በዳር ዳር ወይም በነካ ነካ ሕይወት እግዚአብሔርን ማወቅ ሊታሰብ አይገባም፡፡ይልቁንም
በጽኑነት ፊቱን መፈለግ ይገባል፡፡
እግዚአብሔርን ማወቅ ዋነኛ ነገር ነው፡፡የመንፈሳዊ በረከቶች ሁሉ ምንጭም ነው፡፡ኤር 9፡23-24 ላይ እርሱን በማወቅ
ዙሪያ የተጻፈልን እጅግ ጥልቅ የሆነ ሚስጥር ያለው ቃል እናገኛለን፡፡እንዲህ ይነበባል፡-ጠቢብ በጥበብ አይመካ ኃያልም በኃይሉ አይመካ
ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ ነገር ግን የሚመካው፡-ምህረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን
በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና ይላል እግዚአብሔር፡፡››ይህ ቃል እግዚአብሔርን በማወቅና በማስተዋል
ሊኖረን ስለሚገባ ትምክህት ነው የሚናገረው፡፡አዎ እርሱን ስናውቅ የሚመጣ እምነት አለ፣መደገፍ አለ እራስን መስጠት አለ፡፡ይህ “እውቀትና
ማስተዋል” ግን በቂ ጊዜን በፊቱ በማሳለፍ የሚመጣ ነው፡፡እንዲህ በማድረግም እኛን ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርንም እንደምናስደስት
እንወቅ፡፡ባለም እንዳሉ እርሱን እንደማያውቁ ሰዎች በዚች አለም ጥበብ፣ሀይል እና ብልጥግና እንዳንመካም ያስገነዝበናል፤ለጊዜው ቢጠቅምም
ጠፊና ሀላፊ ነውና!
ያለንበት ዘመን ከመቼውም ዘመን ይልቅ እርሱን ለማወቅ ለሚፈልግ ሰው እጅግ የተመቻቸ ይመስለኛል፡፡በተለያዩ መንገዶች
የሰውን ልብ የሚነኩ ከመጽሀፍ ቅዱስ ጨምሮ ብዙ መንፈሳዊ መጽሀፍት አሉ፡፡በዙሪያችንም እግዚአብሔርን በህይወታቸው ያዩና መንፈሳዊውን
አለም በሚገባ የተገነዘቡና ከጌታ የተማሩ ብዙ ሰዎች አሉልን፡፡ስለዚህ ቀናችን በችኮላ ሳያልቁ የዚህ የበረከት ተካፋይ ለመሆንና
እርሱን ለማወቅ ይሉኝታን ሰብረን መነሳት አለብን ብዬ እመክራለሁ፡፡
በነገራችን ላይ እርሱን ማወቅ ቀላል ነው ብዬ አላስብም፤የምንከፍላቸው ብዙ ዋጋዎች ይኖራሉ፡፡ግን ይህ የሚሆነው ከብዙ ውስጣዊ ሰላምና ጸጥታ ጋር ነው፤በቀረብነው ቁጥር
ህልውናው ያገኘናልና፡፡ለትምህርታችን የተጻፈ ፊሊ 3፡9-11 ላይ የሚገኝ ሀዋርያው ጳውሎስ ‹‹ክርስቶስን ለማወቅ›› የከፈለውን መስዋእትነት
የሚገልጽ ግሩም መልእክት እናገኛለን፡፡እንዲህ በማለት፡-‹‹አዎን በእውነት
ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቆጥረዋለሁ፡፡ስለ እርሱ ሁሉን ተጎዳሁ
ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ በክርስቶስ በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከህግ ለእኔ ያለው
ሳይሆንልኝ በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጉድፍ እቆጥራለሁ›› በዚህ በተጠቀሰው ቃል ላይ ሀዋርያው ጳውሎስ አላማ የነበረው(focused
) ሰው እንደ ነበረ እናያለን፡፡ሌላውን ነገር ሁሉ እንዲንቅ አቅም የሰጠው ሀይለኛ ብርሀንና መንፈሳዊ መረዳት እንደ ነበረ ምንም
አያጠራጥርም፡፡ ሀዋርያው ጳውሎስ በህይወቱ መሰጠት የነበረው ሰው ሲሆን ቅዱስ አለመርካት (holy dissatisfaction)መገለጫ
ባህርይውም ነበር፡፡ይህንን ህይወት ግን በብዙ ትጋት እንዳገኘው ልናስተውል ይገባናል፡፡የከፈላቸው ብዙ መስዋእቶች ነበሩ፡፡በእነዚያም
በወሰዳቸው እርምጃዎች እና ጽናቱ እግዚአብሔርን ከሚገባው በላይ አውቋል፡፡በእኛም ህይወት እንዲህ ነው የሚሆነው፡፡ወደ እርሱ በቀረብን ቁጥር ማንነቱ እየገባንና እየተገለጠልንና
ለሌሎች ነገሮች ያለን ዋጋና ክብር እያነሰና እርሱ ግን እየተለቀና እየላቀ ይመጣል፡፡
ጌታን አውቆ ሰው ድሮ እንደ ነበረው መሆን አይችልም፡፡ጌታን በማወቅ እምነታችን ያድጋል፣ደስታችን ይጨምራል፣ሰላማችን
ይበዛል፣መረጋጋታችን ይልቃል ወዘተ፡፡ለአለም ያለን አመለካከት፣ለእራሳችን ያለን አመለካከት ፣ለሰዎች ያለን እይታ ወዘተ ሁሉ በሚገባ
ይቀየራል፡፡ያካሄድ ለውጥ ይመጣል፤ያስተሳሰብ ለውጥ ይመጣል፤የንግግር
ለውጥ ይመጣል፤የምርጫ ለውጥ ይመጣል፤የእይታ ለውጥ ይመጣል፤ሌላም ሌላም!በጥቅሉ ብዙ ለውጦች ይመጣሉ፡፡እያንዳንዱም አዎንታዊ ለውጥ
ለበለጠና ለጨመረ ለውጥ ይገፋፋናል እኛ ወደ ስጋዊ ነገር ተመልሰን እስካላቆምነው ድረስ፡፡
ሆሴ 6፡3 ላይ ‹‹እንወቅ እናውቀውም ዘንድ እግዚአብሔርን እንከተል እንደ ወገግታ ተዘጋጅቶም እናገኘዋለን›› የሚል
እግዚአብሔርን ስለማወቅ የተጻፈ ድንቅ መርህ ያለው ቃል እናገኛለን፡፡እዚህ ቃል ላይ ሁለት ግልጽ ቁም ነገሮች ተቀምጠዋል፡፡እነርሱም፡-
1ኛ፡-የእግዚአብሔር ለመታወቅ ዝግጁነቱ
ጌታ እራሱን ለሰው ልጆች ለመግለጥ ዝግጁ ነው፡፡ፊሊ 4፡6 ላይ ይህንኑ የሚያጸና ቃል አለልን፡፡እርሱም ፡-‹‹ጌታ ቅርብ
ነው››የሚል ነው፡፡አዎ ለማወቅ ለፈለገ ሰው ጌታ ከእስትንፋሳችን ይልቅ የቀረበ አምላክ ነው፡፡ይህንን ቃል በህይወቴ ስላየሁት በቂ
ምስክር ነኝ፡፡ደግሜም እላለሁ፡-‹‹እጅግ ቅርብ ነው››በተለያዩ የመጽሀፍ ቅዱስ ክፍሎችም ለመታወቅ እጁ የተዘረጋ፤በብዙ ግብዣ እና
ዝግጁነት የሚገኝ መሆኑን ተገልጾልናል፡፡ለአብነት ያህል ትንሽ የግብዣ ማስረጃዎችን ላቅርብ፡-
ማቴ 11፡28 ላይ
‹‹እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ ወደ እኔ ኑ››ብሎ ይጣራል
ምሳሌ 8፡4 ላይ
‹‹እናንተ ሰዎች እናንተን እጠራለሁ፤ድምጼም ወደ ሰዎች ልጆች ነው››የሚል ግልጽ መልእክትም አለን
ኢሳ 55፡1 ላይ
‹‹እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ ወደ ውኃ ኑ፤ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ ብሉም ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅምና ወተት ግዙ››እያለ
ወድ ወደ ሆነ ግን የተከፈለበት ነጻ ግብዣ ይጋብዘናል
ሮሜ 10፡21 ላይ
‹‹ቀኑን ሁሉ ወደማይታዘዝና ወደሚቃውም ሕዝብ እጆቼን ዘረጋሁ››በማለት አሁንም ዝግጁነቱን ይነግረናል
አዎ እጁ እንደተዘረጋች
ነው፡፡ለመታወቅም እጅግ ዝግጁ ነው፡፡ስለዚህ የምናመካኘው ነገር አይኖረንም፡፡
2ኛ፡-እግዚአብሔርን ለማወቅ ‹‹መከተል›› ማስፈለጉ
“እንከተል” የሚለው ቃል ዲሲፕሊን የሚያስፈልገው፤ጽናትን የሚጠይቅ፤ትእግስትን የሚሻ፤ንቁነትንና ትጉህ መሆንን የሚጠይቅ እንደሆነ ቃሉ እራሱ ይጠቁመናል፡፡በእንደዚህ አይነት ጠበቅ ያለ
ውሳኔና ጉጉት ውስጥ ስንሆን ብሎም በትእግስት ፊቱን ስንፈልግና እንደ ማርያም እግሩ ስር ስንቀመጥ በራሱ መንገድና አሰራር ተገልጾ
በቃላት መግለጽ በሚያቅተንና በሚያስደንቅ ሁኔታ እራሱን ይገልጥልናል፡፡ይህን አባባል ስጽፍ በራሴ ህይወት የተከሰተውንና እራሱን
የገለጠልኝን ሁኔታዎች እያስታወስኩ እንደሆነ ልብ እንድትሉልኝ እፈልጋለሁ፡፡ማለትም ዝም ብዬ ተረት እየጻፍኩ አይደለም፡፡በቅንነት ከፈለግነው በእርግጠኝነት እንደሚገኝ ማብሰሬ ነው፡፡
ስለዚህ ይህንን የነገስታት
ንጉስ በማወቅ ፍጻሜያችን እንዲያምር ከተኛንበት እንነሳ እንከተለው፡፡ለምን ቢባል በርሱ ዘንድ እረፍት አለ፣ሞገስ አለ፣ ብዙ በረከትም
አለ፡፡ ምሳ 8፡34-35 እንዲህ ይላል ፡-‹‹የሚሰማኝ ሰው ምስጉን ነው ዕለት ዕለት በቤቴ መግቢያ የሚተጋ፤የደጄንም መድረክ የሚጠብቅ፡፡እኔን
ያገኘ ህይወትን ያገኛልና፤ከእግዚአብሔርም ሞገስን ያገኛልና፡፡››አዎ እርሱን መከተል ሕይወት ነው እረፍትም ነው፡፡ስለዚህ እርሱን
ለማወቅ እንነሳ፣እንከተለው፣እንትጋ!እንዲህ ብናደርግ በእራሱ ጊዜ ተገልጦ ያስደንቀናል!!!
አሜን አሜን አሜን ተባረክ/ኪ
ReplyDeleteአዎን ጌታን በማወቃችን ፍፃምያችን እንድያምር ያደርገዋል አሜን አሜን አሜን ነው
ReplyDelete