Saturday, November 15, 2014

የመንፈሳዊ ራብ በረከት



የመንፈሳዊ ራብ በረከት

መንፈሳዊ ራብ ጌታን መናፈቅን፣እሱን ለማግኘት መጓጓትን፣ወደ እሱ ለመጠጋት ማሰብን ወዘተ ያመለክታል፡፡

በግለሰብ ይሁን በወል ደረጃ መንፈሳዊ ራብና ጥማት ለእግዚአብሔር መለኮታዊ ጉብኝት እጅግ ወሳኝ ናቸው፡፡አውነተኛ የሆነ መንፈሳዊ ራብና ጥማት እግዚአብሔርን እንድንሻው፣እንድንፈልገውና እንድንጠጋው ኃይል ይሆኑናል፡፡ ቃሉ “ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው” (ማቴዎስ 5፡6) የሚለን ለዚህ ነው፡፡ “ብፁዓን” የሚለውን ቃል ድረ-ገጽ ላይ ያገኘሁት አምሊፋይድ መጽሐፍ ቅዱስ ደስተኞች፣በመንፈስ ባለጸጋ የሆኑ፣የረኩ፣የተባረኩ ወዘተ ብሎ ነው የሚገልጸው፡፡በነዚህ ቃሎችም መንፈሳዊ ራብ ሊያመጣ የሚችለውን የበረከት ሰፊነት ተገንዝቤአለሁ፡፡

ሐና መንፈሳዊ ራብ ያላቸው ሰዎች በጌታ ፊት ዋጋ ያላቸውና የማይረሱ እንደ ሆነ ስትናገር “ተርበው የነበሩ ከራብ አርፈዋል” (1 ሳሙኤል 2:5) ብላለች፤ አምላኳ የሚያረካ፣የሚያጠግብና የሚያሳርፍ መሆኑን በማወደስ፡፡

መንፈሳዊ ራብ በራሱ ትልቅ በረከት ነው፤ወደ ፊት እንድንዘረጋ፣እንድንቃትት፣ፊቱን አንድንፈልግ ያደርገናል፡፡የምር የሆነ መንፈሳዊ ራብ የሚመነጨው ደግሞ ያለንበትን ሁኔታ የእግዚአብሔር መንፈስ ሲያሳየንና ያለንበትን አዘቅት ስንጠላው ነው፡፡መንፈሳዊ ራብ ይጐተጉተናል፣አያስተኛንም፤ቃሉ“የሠራተኛ ራብ ለርሱ ይሠራል አፉ ይጐተጉተዋል” (ምሳሌ 16፡26) ይላልና ፡፡“ለርሱ ይሠራል” የሚለውን አስምሩልኝ፡፡ለማን? ለርሱ! አያስተኛውማ! ሳያገኝ አያሳርፈውማ! ለዚህ ነው መንፈሳዊ ራብ በራሱ የሚጓጓለት በረከት የሆነው፡፡

መንፈሳዊ ራብ ልክ እንደ ኤርምያስ ጌታን በትጋት እንድንፈልገው ያደርገናል፡፡ኤርምያስ ከብዙ ፍለጋ በኋላ ሕይወት የሚሰጠውን፣መንፈስ የሆነውን፣የጊዜውን ቃል ሲያገኝ እንዲህ ብሎ ተናገረ፡-

“ቃልህ ተገኝቷል እኔም በልቼዋለሁ፤አቤቱ የሠራዊት ጌታ ሆይ በስምህ ተጠርቻለሁና ቃል ሐሤትና የልብ ደስታ ሆነኝ” (ኤርምያስ 15፡16)

ከዚህ ምንባብ በጥቂቱ እንደምንረዳው፣ኤርምያስ ቃሉን በትጋትና በተራበ መንፈስ ሲፈልግ የቆየ ይመስላል፡፡ባገኘውም ጊዜ ከነበረው ናፍቆት የተነሣ ለመብላት ፋታ ያገኘም አይመስልም፡፡እናም እስከሚረካና በሐሤት እስኪጥለቀለቅ ድረስ በላው፡፡

ንጉሥ ዳዊት እውነተኛ መንፈሳዊ ራብ ያላቸውን ሰዎች እግዚአብሔር እንዴት እንደሚባርክ ሲገልጽ፣ የተራበችን ነፍስ አጥግቦአልና፤የተራቈተችንም ነፍስ በበረከት ሞልቶአልና (መዝ 107፡9) ብሎ ተናግሯል፡፡አዎ መንፈሳዊ ራብ የገባበት ሰው ሲቆፍር፣ሲፈልግ፣ሲቃትት ወዘተ ያድራል፤ዕረፍት አይኖረውም ያንን ራብ ሳያስታግስ፡፡ራቡ ጐትጓች ነውና፣አያስተኛውምና፡፡

ይህን መንፈሳዊ ራብ የሚያቀጣጥሉ ሦስት የታወቁ ነገሮች አሉ፡፡እነሱም፡-

  • የአግዚአብሔር ቃል አብዝቶ ማጥናትና ማሰላሰል
  • ደጋግሞ ለረጅም ጊዜ መጾም
  • በጌታ ፊት በውሳኔ መውደቅ

ጌታ እንደ ተስፋ ቃሉ መንፈሳዊን ነገር በሚራቡና በሚጠሙ ሰዎች ሕይወት፣ ከብዙ መሻት በኋላ ሲገለጥ አስደናቂ ነገር የሚሆነው፡፡ለዚህ ነው ሰፋ ካለ መንፈሳዊ መነቃቃት በፊት በቤተ ክርስትያን እርሱን የሚራቡና የሚጠሙ፣እናም በጓዳ እሱን የሚሹና የሚፈልጉ ሰዎች አስቀድሞ የሚያስነሣው፡፡

አንድ ክርስትያን ይህ ራብ በውስጡ ለረጅም ጊዜ ከጠፋ፣ለመውደቅ እየተንሸራተተ እንደ ሆነ ሊያስብ ይገባዋል የሚል አመለካከት አለኝ፡፡በግሌ ይህ ራብ ከውስጤ ሲጠፋ ግራ ይገባኛል፡፡እናም ሁሉን ነገር አቁሜ ወደ ቦታዬ ለመመለስ ብዙ ነገሮች አደርጋለሁ፡፡ከወትሮውም ብዙ እጸልያለሁ፤ብዙ መንፈሳዊ መጽሐፍትን በማንበብ ራሴን አነቃቃለሁ፤እንዳስፈላጊነቱም ጾምንም እጨምራለሁ፡፡

በጌታ ቤት በቆየሁበት ዘመን መንፈሳዊ ራብ የሚያስደንቅ ኡደት (positive cycle) እንዳለው ተገንዝቤአለሁ፡፡መንፈሳዊ ራቡ ልባችንን ባሰፋነው መጠን ያድጋል፡፡ አብዝተን እንድንቃትት ያደርገናል፡፡አብዝተን ስንጸልይ ደግሞ ጸሎቱ ሌላ ከፍ ያለ መንፈሳዊ ራብን ይወልዳል፡፡የሚመጣው መንፈሳዊ ራብ ደግሞ አብዝተን እንድንጸልይ ያደርገናል፡፡ወገኖቼ አንዱ አንዱን እየጨመረ ማብቂያ የሌለው አስደናቂ ነገር ውስጥ ነው የምንገባው፤እኛ በሥጋዊ አካሄዶች መንፈስን እስካላጠፋን ድረስ፡፡

ጌታ ሆይ ከፍ ያለ አንተን የሚሻና የሚፈልግ ልብ ስጠን !  

Saturday, November 8, 2014

የድብርት መድሐኒት



የድብርት መድሐኒት

በዓለማችን በተለይ በምዕራቡ ምድር እንደምናየው ብዙ ሰዎች በተለያዩ የአእምሮ በሽታዎች ሲጠቁ እናያለን፡፡ዋነኛው የአእምሮ ችግርም ድብርት (depression) እንደሆነ በዚህ ዙሪያ ጥናት ያደረጉ ጠበብቶች ይስማማሉ፡፡የድብርት (depression) መንስዔው እንደ ቦታው እና እንደ ሰዉ አይነትና አኗኗር ይለያያል፡፡ሁሉንም የሚያመሳስላቸው ግን የችግሩ ስሜቶች እና ምልክቶች ናቸው፡፡ማለትም ሁሉም ሰዎች ላይ ደስታ ማጣት እና ሐዘን ይኖራል መጠኑ ቢለያይም፡፡ይህ ችግር ጌታ ኢየሱስን የማያውቁ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን እሱን በሚገባ የሚያውቁ ሰዎችን ላይ ሳይቀር ይስተዋላል፡፡አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ጊዜያዊ ጭንቀት እና ድብርት ማንኛችንም ላይ በተለያየ ምክንያት ሊመጣ ይችላል፤ነገር ግን እላያችን ላይ ቤቱን ሰርቶ እንዲረጋጋ እና መጫወቻ እንዲያደርገን መፍቀድ የለብንም፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ችግር ወደ ሕይወታችን እንዳይመጣ ጥሩ መከላከላያ መድሐኒት ያለው ሲሆን፣ይህ ችግር ካገኘንም በኋላ ባስተማማኝ ሁኔታ የምንወጣበት መፍትሔም በውስጡ ይዟል፡፡ ከቃሉ ጋር ትክክለኛ እና የጠለቀ ሕብረት ያለው ክርስትያን፣ዝቆ እና ቀድቶ የማይጨርሰው የደስታ ምንጭ እንዳለ እኔ በተግባር በሕይወቴ አይቻለሁና በድፍረት እመሰክራለሁ፡፡
ንጉሥ ዳዊት በእንደዚህ ነፍስን ግራ በሚያጋባ አጣብቂኝ እና ሐዘን ውስጥ ከማናችንም በላይ ያለፈ ሲሆን ችግሩን፣መፍትሔውንና የመፍትሔውን ውጤት በመዝ 42፡2-4  በሚደንቅ ሁኔታ ጽፎልናል፡፡ይህ ክፍል እጅግ ግሩም ትምሕርት ያዘለ ሲሆን፣ በሚገባ በሕይወታችን ከተገበርነው ትልቅ በረከት እንዳለው አምናለሁ፡፡ይህንን ምንባብ ወደ ጌታ ከመጣሁ በኋላ ከመቶ ጊዜ በላይ አንብቤዋለሁ፡፡አሁንም ደጋግሜ የማነበው ክፍል ነው፡፡እንዳውም በጸሎት ጊዜዬ ክፍሉን ወደ ራሴን እያስገባሁ የምጸልይበትም ጊዜ አለ ፡፡ቃሉ እንዲህ ይነበባል፡-

‹‹አንተ አምላኬ ኃይሌም ለምን ትተወኛለህ?ጠላቶቼ ሲያስጨንቁኝ ለምን አዝኜ እመላለሳለሁ?ብርሀንና እውነትህን ላክ እነርሱም ይምሩኝ ወደ ቅድስህናህ ተራራ እና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ፡፡ወደ እግዚአብሔር መሰዊያ ጎልማስነቴንም ደስ ወዳሰኛት ወደ አምላኬ እገባለሁ››

ንጉሥ ዳዊት በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ የቆየበት ጊዜ ባይታወቅም ትንሽ እንደቆየ መገመት ይቻላል፡፡ይህንን የሚጠቁመን ‹‹ለምን አዝኜ እመላለሳለሁ››የሚለው ሐሳብ ነው፡፡እንደዚህ ዓይነት በደል፣ሐዘንና ጭንቀት የሚያደርሱበት ደግሞ ጠላቶቹ(አጋንንቶች-የሰው ጠላት የለንምና)እንደሆኑ ይናገራል፡፡ከዚያም መፍትሔውን ራሱ ያቀርባል እንዲህ ብሎ ‹‹ብርሃንህንና እውነትህን ላክ››፡፡በዚህ ሐረግ ዳዊት መፍትሔው ከእግዚአብሔር አፍ የሚወጣ ቃል እንደሆነ ነው የሚነግረን፡፡ባጭሩ ክፍሉ በጸሎት መንፈስ ሆነን ፊቱን እየፈለግን፣እየቃተትን፣ቃሉን እያሰላሰልን በጽናት ስንጠብቀው መድሐኒት እንደሚላክልን ይጠቁመናል፡፡ዳዊት ክፋት ወደሌለበት ‹‹ወደ ቅድስና ተራራውና ወደ ሕልውናው (His presence)›› ደጋግሞ ሄዶ ተሰውሮ ያውቃልና፣ያንን በመሻትና በመጠማት ነው አምላኩን እየተማጸነ ያለው፡፡እንደምናውቀው በሕልውናው ውስጥ ደግሞ ሰላም አለ፤ደስታ አለ፤እረፍት አለ፤መረጋጋት አለ፡፡በሱ ፊት ጨለማ መቆም አይችልምና፣ትካዜና ሐዘንም ይሸሻሉ፡፡እኔም ይህንን ደጋግሜ በሕይወቴ ስላየሁኝ ሕያው ምስክር ነኝ፡፡ክርስትናን ውብና ልዩ የሚያደርገው ታዲያ ሌላ ምንድነው ?

ስለዚህ በራሳችን መታገል ስለማይጠቅመን፣ያንን አቁመን ሙሉ በሙሉ ራሳችንን ለእሱ እንስጠውና በፊቱ እንውደቅ! “በመመለስና በማረፍ እንድናለንና በጸጥታና በመታመን (በፊቱ በመሆን) ኃይል ይሆንልናልና” (ኢሳይያስ 30፡15 አጽንዖት የእኔ) መጥተን በፊቱ ምንም ሳናቅማማ እንረፍ!