Saturday, February 1, 2014

ልብን የሚለውጥ ቃል



                  

ልብን የሚለውጥ ቃል


የሰው ልብ የሰው ሁለንተናው ወይም ማንነቱ  ነው፡፡ስለዚህ ከልባችን አዘውትሮ የሚወጣው ነገር መገለጫችን ይሆናል፡፡በልባችን ላይ የምንዘራው ነገርና ጊዜ የምናጠፋለት ነገር ውጫዊ ድርጊታችንንም በሚገባ ይወስነዋል፡፡ልባችን እና አንደበታችን የተገናኙ ነገሮች ናቸው፡፡አዘውትረን የምንተነፍሰውና የምንናገረው ማንኛውም ሀሳብ በልባችን በዋናነት ቦታ የያዘውን ነገር ነው ምሳሌ 16፡23 ላይ ‹‹የጠቢብ ልብ አፉን ያስተምራል››ይላልና፡፡በዚህ ቃል ላይ አፍና ልብ የተገናኙ መሆናቸውን እናስተውላለን፡፡


ልባችን ላይ የሚዘራው ዘር ውስጣችንን እየለወጠው ሲመጣ የቃላት አመራረጣችንን አስተሳሰባችንንና ከሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነታችንን በእጅጉ ይቀይረዋል፡፡ስለዚህ በውጫዊ ነገሮች ላይ በሀይል ከመጨነቅ ይልቅ በልባችን ላይ ለምንዘራው ዘር ልንጠቀቅ ይገባል፡፡ለዚህ ነው ምሳሌ 4፡23 ላይ ‹‹አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ የህይወት መውጫ ከእርሱ ነውና››የሚለን፡፡አጥብቀን ልባችንን የምንጠብቅበት መንገድም በልባችን ላይ የእግዚአብሔርን ቃል በመዝራት፣በማጥናት እና በማሰላሰል ነው፡፡ከዚህ ሀሳብ ጋር የሚስማማ ሀሳብ ያለው ዘዳ 11፡18 ሲሆን ቃሉ ጠንከር ያለ ጥረትን እንደሚጠይቅም ያሳየናል፡፡ቃሉ እንዲህ ይነበባል፡-

‹‹እንግዲህ እነዚህን ቃሎች በልባችሁና በነፍሳችሁ አኑሩ፤እነርሱንም ለምልክት በእጃችሁ ላይ እሰሩአቸው፤በዓይኖቻችሁም መካከል እንደ ክታብ ይሁኑ፡፡››

ቃሉን በነፍሳችን ውስጥ እንዲኖር የምናደርግባቸው መንገዶች ሁለት ናቸው፡፡የመጀመሪያው መንገድ ቃሉን ያለማሰለስ ማጥናትና ማሰላሰል ሲሆን ሁለተኛው መንገድ ቃሉን በተግባር በኑሮአችን መለማመድ ነው፡፡እነዚህን ሁለት ነገሮች ሳናቋርጥ ስናደርግ ህይወትን የሚለውጠው ቃል በማይረሳን ሁኔታ በልባችን ላይ ይታተማል፡፡


ዘዳግም ላይ ካለው ቃል ጋር የሚመሳሰል ቃል መዝ 119፡11 ላይ እናገኛለን፡፡ይህም ቃል እንዲህ ይላል፡-‹‹አንተን እንዳልበድል ቃልህን በልቤ ሰወርሁ››አዎ እርሱን ላለመበደል ባለቀ ሰአት መሯሯጥ ሳይሆን አስቀድሞ ቃሉን በልብ መሰወር ነው የሚጠቅመን፡፡ቃሉን በልባችን መሰወሪያውም ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱ መንገዶች ናቸው፡፡‹‹መሰወር››የሚለው ቃል በውስጣችን ትርጉም አግኝቶ የተዋሀደውንና የራሳችን ያደረግነውን ቃል ወይም ሬማ የሆነልንን ቃል ያመለክታል፡፡በጥሩ ሁኔታ የተጠናና ጊዜ ሰጥተን ያሰላሰልነውን ቃል ብቻ ነው በውስጣችን መሰወር የምንችለው፡፡ቃሉን የምንሰውረውም ገና ቃሉን ሳናስተውል ባለበት ሁኔታ ላይ ሆነን ሳለን የሚነጥቅ ሌባ ስላለ ነው፡፡በአእምሮአችን ያላስተዋልነው ቃልም ወደ ልባችን አይገባም፤በሩ አእምሮአችን ነውና፡፡እንዲህ በውስጣችን የተሰወሩ ቃሎች በልባችን ሲበዙልን ጌታን የምናሳዝንበት እና የምንበድልበት መጠን እያነሰ እና እርሱ በህይወታችን እየከበረ ይመጣል፡፡በሌላ አገላለጽ እየተለየን እየተለወጥንና እርሱን እየመሰልን እንሄዳለን ማለት ነው፡፡


መጽሀፍ ቅዱስ በተለያየ ቦታ ልባችን ላይ ትልቅ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብን ይናገራል፡፡ኤር 17፡9 ላይ ‹‹የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኮለኛ እጅግም ክፉ ነው ማንስ ያውቀዋል?››በማለት የልባችንን ማንነት በሚገርም ሁኔታ ይነግረናል፡፡የሚገርም ነው፡፡የልባችንን የክፋት መጠንና ስፋት እግዚአብሔር እንጂ እኛ በፍጹም አናውቀውም፡፡ከዚህም የተነሳ ነው በእራሳችን ላይ ምንም መተማመን የሌለብን፡፡ይህ ቃል ምን ያህል የጌታ ረድኤት እና ጥበብ በህይወታችን እንደሚያስፈልገንም ያሳያል፡፡ስለዚህ ቃል በእንግሊዝኛ መጽሀፍ ቅዱሶች ላይ ጠንከር ያሉ ሀሳቦችን አይቻለሁ፡፡ሲተነተን ልባችን የሚከተሉትን ባሕርዮች ይዟል፡-

  • Deceitful of all things:-እጅግ አሳች/አደገኛ አሳሳች(መዝ 95፡10 ያንቡ)
  • Desperately wicked ፡-ለክፋት የማይመለስ/ለክፋት የተሰጠ


አዎ የሰውን ልብ ማንም አያውቀውም፡፡ይህንን ለክፋት የተሰጠ ማንነት መለወጥ የሚችል የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው፡፡ሌሎች ምንጮች ታይታዊ ወይም ውጫዊ እንጂ ዘለቄታዊ ለውጥን በፍጹም አይሰጡንም፡፡ስለዚህ ነው እራሳችንን እንደ ህመምተኛ አይተንና አምነን ወደዚህ የመድሀኒቶች ሁሉ ምንጭ መምጣት የሚገባን፡፡በማርቆስ 7፡21-23 እንደምናየው ከሰው ልብ ብዙ የሚያረክስ እና ብዙ ግንኙነታዊ እና ማህበራዊ ቀውስ የሚያመጡ ነገሮች ይወጣሉ፡፡ስንዘረዝራቸው፡-

------›ክፉ ሀሳብ፣ዝሙት፣መስረቅ፣መግደል፣ምንዝርነት፣መጎምጀት፣ክፋት፣ተንኮል፣መዳራት፣ምቀኝነት፣ስድብ፣ትዕቢትና ስንፍና 


ገራሚ ነው፡፡እነዚህ ሁሉ ከልባችን ይወጣሉ፡፡እጅግ አስፈሪም ነው፡፡ለዚህ ነው እላይ ኤር 17 ላይ በተጠቀሰው ቃል ላይ ‹‹የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኮለኛ እጅግም ክፉ ነው ማንስ ያውቀዋል?››በማለት የሚናገረው፡፡‹‹ክፉ ሀሳብ›› የሚለው ቃል በተለይ ሰፋ ያለ ቃል ሲሆን ብዙ ክፉ ነገሮችን የማሰብ ዝንባሌዎች እንዳለን ይጠቁመናል፡፡ለዚህ ነው ሀዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 7፡24 ላይ ‹‹እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ፤ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል? ብሎ ጠይቆ በሚቀጥለው መስመር ቁጥር 25 ላይ መፍትሄውን የሚያስቀምጠው፤እንዲህ በማለት‹‹በኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን››አዎ መፍትሄው አንድ ነገር ብቻ ነው ፡-‹‹የህይወት መንፈስ ህግ››(ሮሜ 8፡2)


የልባችንን ምንነት በመንፈስ ማየት ልናደርገው የሚገባንን ጥንቃቄ እና የምንወስዳቸውን እርምጃዎች በሚገባ ይወስኑታል፡፡ዮሀ 8፡31 ያመኑትን አይሁዶች ኢየሱስ እንዲህ ነው ያላቸው፡-‹‹እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም ታውቃላችሁ እውነተም አርነት ያወጣችኋል›› አዎ ይህ መንፈስ የሆነው ቃል ልባችን ውስጥ በተዘራውና ስፍራ ባገኘው ልክ ነጻነታችን እየጨመረ እና እየተለቀቅን እንሄዳለን፡፡በህይወታችንም ብዙ መንፈሳዊ ፍሬዎች መታየታቸው የማይቀር ይሆናል፡፡ሀሳቤም ነጻነታችንና መንፈሳዊ ፍሬዎች ከቃሉ ጋር የምናደርገው የቁርኝት መጠን ውጤቶች መሆናቸውን ለመግለጽ ነው፡፡


ልባችን ላይ ያለማሰለስ የሚዘራው መንፈስ የሆነው ቃል የልባችንን አይን ስለሚያበራው መንፈሳዊውን አለምና ማንነታችን እያወቅን እንመጣለን፡፡ከምን አይነት ጉድም እየወጣን እንዳለም በሚገባ እንረዳለን፡፡ኤፌ 1፡15-19 ይህንን ሀሳብ በሀይል የሚገልጽ ግሩም ቃል አለ፡፡እንዲህ ይነበባል፡-


‹‹የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ፡፡ይህም የልባችሁ አይኖች ሲበሩ የመጥራቱ ተስፋ ምን እንዲሆን በቅዱሳን ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለጠግነት ምን እንዲሆን ለምናምንም ከሁሉ የሚበልጥ የሀይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን ታውቁ ዘንድ ነው››


ይህ ቃል እጅግ ድንቅ ሀሳብ የያዘ ቃል ነው፡፡‹‹እርሱን በማወቅ›› የሚለው ሀረግ ስለ ቀለም እውቀት አይደለም የሚናገረው፡፡በጸሎትና መንፈስ ከሆነው ቃል ጋር በሚኖረን ህብረት ስለምናገኘው እውቀት ነው የሚናገረው፡፡በእንግሊዝኛው ‹‹relational knowledge›› ይሉታል፡፡ስለዚህ በሂደት ባስቀምጣቸው፡-


  •         ክርስቶስን በጸሎትና በቃሉ ማወቅ-------›የጥበብና የመገለጥ መንፈስ--------›የልባችን አይኖች መብራት


የልባችን አይኖች ሲበሩ ምርጫዎቻችን፣የህይወት ምልልሳችን፣ድርጊታችን እና ግንኙነታችን በሚገርም ሁኔታ ይቀየራሉ፡፡ከዚህ የተነሳ ሕይወታችን በሁሉም መስክ ትርጉም ያገኛል፡፡ለምን እንደምኖር ፤ለምን ጉዳይ ቅድሚያ መስጠት እንዳለብን እና የትኛው ነገር ዋናው የልባችንን ክፍል መያዝ እንዳለበት በሚገባ እንገዘባለን፡፡ከዚህም የተነሳ በኑሮአችን ስራ መፍታት እና በተራ ነገሮች ጊዜን ማባከን የሚባሉ ነገር ያበቃላቸዋል፡፡በሕይወታችንም እውነተኛ እርካታን እናገኛለን፡፡ስለዚህ እንደ እግዚአብሔር ሀሳብ የሆነ የልብ ለውጥ በማምጣት የፍሬ ሰዎች እንድንሆን ለቃሉ ያልተከፋፈለ ልብን እንስጥ!!