ለነፍሴ ያደረገላትን ልንገራችሁ
ጌታን እንደ ግል አዳኜ አድርጌ
ከመቀበሌና መሪ አድርጌ ከመሾሜ በፊት ህይወቴ እንደ አይን የጠፋና የተበላሸ ነበር፡፡ሀይለኛ የሱስ ቀንበር እላዬ ላይ ነበርና
የየቀኑ ኑሮዬ የስቃይና የመከራ ነበር፡፡መጠጣት ነበረብኝ፤መቃም ነበረብኝ፤ማጨስ ነበረብኝ፡፡ከዚህም የተነሳ ማህበራዊ ህይወቴ
የተበላሸ ነበር፡፡
የክፉ ተጽእኖ እንደ ነበር በሕይወቴ ቅንጣት አልጠራጠርም፡፡አሁን ላይ
ቆሜ ሳየው ባሁኑ ሰአት መኖሬ እራሱ ተአምር ነው፡፡ሞቴ ይፈጥናል የሚል ግምት በኔም በአቅራቢያ ባሉ ሰዎች ሁሉ የሚታሰብ ጉዳይ
ነበር፡፡እንደዚህ አይነቱ ህይወት ከ 15 አመት በላይ አሸኝ፡፡ከዚህ ስቃይ ገፍትሮ ለመውጣት ብሞክርም ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› አይነት
ኑሮ ለረጅም ዘመን ገፋሁ፡፡ውስጤ ስቃይ ነበር፤ለቅሶ ነበር፤ሀዘን ነበር፤ተስፋ መቁረጥ ነበር፤ሞትን በሀይል መመኘት ሁሉ ነበር፡፡
እያንዳንዱን ቀን በመጠጥ ለመሰወር የመጠጥ ባሪያ ብሆንም እንዳውም
የነበሩብኝ ውስብስብ ችግሮች እየገጠጡ መጡ፡፡ችግሮቹን የሚያባብሱ ሰዎች ነበሩ፤እኔም አባብሰው ነበር፤የነበርኩበት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ
ሁኔታዎች ያባብሱት ነበር፡፡ስለዚህ በአጭር ቃል ረግረግ ጭቃ ውስጥ (መዝ 40፡2) ነበርሁ ማለት ይቻላል፡፡
የዘወትር የውስጥ ስቃዬና ጩኸቴ ‹‹ማን ያወጣኛል›› የሚል ነበር፡፡ወደ
ቤ/ክ በጣም አልፎ አልፎ ሄጄ ከነበርኩበት ጉድ ለመውጣት ብሞክርም ውስጤ በሚገባ ስላልተለወጠ ታይታዊ የሆኑ ጊዜያዊ ለውጦች ስለ
ነበሩ አንድ መጥፎ ክስተት ሲገጥመኝ የነበረኝ የሱስ ቀንበር እጥፍ ድርብ ያገረሽ ነበር፡፡
ከላይ በጠቀስኳቸው ውስብስብ ሁኔታዎቸ ሁሉ ነገሬ ተበላሽቶ በቃልኝ
ከዚህ በኃላ ሰው አልሆንም፤ዳግመኛ አልነሳም ፤ብሩህ ቀናትን አላይም ብዬ ደመደምኩ፡፡ዘመድ፣ወዳጅና ቤተሰብ ሁሉ ራቀኝ፡፡መዝ
31፡2 ላይ ‹‹እንደ ሞተ ሰው ከልብ ተረሳሁ፤እንደ ተበላሸ እቃም ሆንሁ›› የሚለው የመዝሙረኛው ዳዊት አገላለጽ በሚገባ የነበርኩበትን
ማጥ የሚገልጸው ይመስለኛል፡፡በሰው ሁሉ ዘንድም ተረሳሁ፡፡
በእንደዚህ ውስብስብ ታሪክ ውስጥ እያለፍኩም ቢሆን የእግዚአብሔር ቃል
በውስጤ ያለ ማቋረጥ ይዘራ ነበር፡፡ይህ ዘር በቅሎም ፍሬ ማፍሪያው በጌታ ጊዜ ደረሰ፡፡እናም ተስፋዬ ተሟጦ ውሀ የሚያጠጣኝ ዘመድ
ወገን ሙሉ በሙሉ ሳጣ ወደ አምላኬ ሙሉ በሙሉ የመመለስ ጉዳይ በአንድ ድንቅዬ ቀን የዛሬ 15 አመት በግማሽ ቀን ገፍቶ አየለ፡፡በዚህ
ውስጣዊ ትንቅንቅ እኔነቴ ለሁለት ተከፍሎ ትግል ሆነ፡፡ይሉኝታ፣የሰው ፍርሀት፣የሱስ ተጽእኖው እስራት፣የብቸኝነቱ መከራ ሁሉ እንደ
ዛፍ እያወዛወዘኝ በሌላ በኩል ወደ እርሱ ብመለስ የማገኘውን እረፍት እያሰብኩ ለ 6 ሰአታት ያህል የታገልሁት ትግል በሕይወቴ አይረሳኝም፡፡
ወደ ልቤም ተመልሼ(ሉቃ 15:17) ስወስንና ከነገ ጀምሮ ወደ አባቴ
ቤት እሄዳለሁ፤አለምን እክዳለሁ፤ሰይጣንንና አገዛዙን እክዳለሁ፤የስጋን መንገድ አልከተልም፤እስከ መጨረሻ የእርሱ ባሪያ እሆናለሁ
ብዬ በልቤ ልክ ቃል ኪዳን ስገባ፡-
- ቤቱ በብርሀን ተሞላ
- የደስታ መንፈስ በውስጤ ፈሰሰ
- ልዩ የሆነ የሰላም መንፈስ አጥለቀለቀኝ
- ከጨለማ ወደ ብርሀን እንደ ተሸጋገርሁ ታወቀኝ(ቆላ 1፡14)
ከዚያ ድንቅ ውሳኔ በኃላ የጫት፣የሲጋራ እና የመጠጥ ሱስና
ቀንበር ባንድ ቀን ሙሉ በሙሉ ተሰበሩ፡፡የሚገርመው ነገር እነዚህን ሱሶች ባቆምኩ የመጀመሪያዎቹ ቀናትና ሳምንት ውስጥ እራስ ምታት
እንኳን አልነበረኝም፡፡ይሄ ሁኔታ ሁልጊዜ ይገርመኛል፡፡ከዛ ሁሉ ቀንበር ተላልቄ የነጻነት አየር እየተነፈስሁ እነሆ አሁን 15 አመት
አልፎኛል፡፡ኢሳ 61፡1-3 እንደሚል ፡-
- ብዙ የልብ ስብራት ነበረኝ ተጠግኛለሁ
- ምርኮኛ ነበርሁ ነጻ ሆኛለሁ
- ታስሬ ነበር ተፈትቻለሁ
- አለቅስ ነበር የደስታ መንፈስ በማያቋርጥ ሁኔታ በውስጤ ፈሷል
- በአመድ ፋንታ አክሊል በሀዘን ፋንታ የምስጋና መጎናጸፊያ ተደርቦልኛል
- የጉዳቴ መጠን ትንሽ አልነበረም የካሳዬ ብዛትም ከአእምሮ በላይ ሆኗል
- ብዙ ድንቅ ነገሮችን አሳየኝ ፡፡ህይወቴን በመንፈሱ ዘይት አለመለመው(መዝ 92፡10)፡፡
ስለዚህም እንዲህ ብዬ አንድ ህይወቴን በሚገባ በመግለጹ የምወደው መዝሙር
አለና እንዲህ ብዬ አዜማለሁ፡-
አየሁ ጌታዬ ከንዱን አንስቶ
የጠላቴን ራስ ሲቀጠቅጠው
እስራቴንም ሲበጣጥሰው
ሞት ሞት የሸተተውን ህይወት
በአዲስ መአዛ ሲለውጠው!!
እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁና ምስክርነቴን ልቋጭ፡-
ለመሆኑ እርሱን የሚመስል ፈዋሽ፤አለምልሞ አድሶና አበርትቶ የሚያቆም
ከወዴት ይገኛል?የተጣለንስ የሚያነሳ ማን ነው?
ለኔ መልሱ ፡-የለም ነው!!
እርሱ ብቻውን ከዘላለም እስከ ዘላለም የተባረከ ይሁን !!!!!!
ይህንን ምስክርነት በቅርብ ጊዜ በመጽሀፍ መልክ ላወጣው በቂ ዝግጅት
እያደረግሁ ነውና ሙሉውን ታሪኬን ታነቡታላችሁ፡፡ተባረኩ!!
በቀለ በላቸው(ዶ/ር)
beke_abay@yahoo.com
240-330-5004
Jan 1,2014